የአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት ቅድመ ምርጫ ዉጤት | አውሮጳ እና ጀርመን | DW | 26.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ እና ጀርመን

የአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት ቅድመ ምርጫ ዉጤት

ጀርመንን ጨምሮ በአውሮጳ ኅብረት 21 አባል ሃገራት ውስጥ ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ የተደረገዉ የምክር ቤት ምርጫ ቅድመ-ዉጤት መዘርዝር መዉጣት ጀምሮአል። መጀመሪያ ላይ ይፋ በሆነው ቅድመ-ዉጤት መዘርዝር መሰረት ወግ አጥባቂዎቹ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ « CDU/CSU» በ36.1 በመቶ እየመራ መሆኑ ተገልጿል።

የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ «SPD» በአንፃሩ 27.6 በመቶ ድምፅ እንዳገኘ ነዉ የተመለከተዉ።

በዚህም ጀርመን መራሂተ መንግሥት የሚመሩት የክርስቲያን ሲሞክራቲክ ኅብረትና የክርስትያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲ « CDU/CSU» የአዉሮጳ ኅብረት ምክርቤት ምርጫን በመምራት ላይ ነዉ። አረንጓዴዉ ፓርቲ 10.9 በመቶ፤ የግራዎቹ ፓርቲ 7.8 በመቶ ድምፅ ሲያገኙ በአዉሮጳ ኅብረት ላይ ጥርጣሬ ያለዉ ፓርቲ AfD 6.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት ግዜ በኅብረቱ ምክር ቤት ለመጀመርያ ግዜ መቀመጫ እንደሚያገኝ ተጠቅሶአል።ከ28ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት የሚገኘዉ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከምሽቱ አምስት ሠዓት ጠቅላላ ይፋ እንደሚደረግ ተመልክቷል።

ቅዳሜ በቼክ ሪፐብሊክ በተካሄደዉ የአዉሮጳ የምክር ቤት ምርጫ ላይ ድምፅ ለመስጠት የመጡ ነዋሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር ፕራግ መዲና የሚገኘዉ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል። ይኸዉ የአዉሮጳ የምክር ቤት ምርጫ፤ በሌትላንድ በማልታና በስሎቫክያም ተካሂዶ ነበር። አየርላንዶች የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን አርብ ዕለት መርጠዋል። ባለፈዉ ሐሙስ በኔዘርላንድ እና በብሪታንያም የአዉሮጳዉ የምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል። የኅብረት አባል ሀገራቱ ከትናንት በስትያ ሐሙስ የጀመሩት የምክር ቤት ምርጫ ዉጤት ነገ ምሽት ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በአዉሮጳ ኅብረት የምክር ቤት ምርጫ ተሳትፎ ላይ ዋነኛዉን ቦታ ይዘዉ የሚገኙት ወግ አጥባቂዎችን እና ሶሻል ዲሞክራቶችን ጨምሮ ቀኝ አክራሪዎች እና በኅብረቱ ጥርጣሬ ያላቸዉ ፓርቲዎችም ይገኙበታል።

በምርጫው አራተኛ ቀን ዛሬ የዴንማርክ፣ የፖርቹጋል እና የስፔን ነዋሪዎችም ድምፅ ሲሰጡ ነዉ የዋሉት።

ጀርመን ውስጥ ወደ 64 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች በምክር ቤቱ ለሚወክሏቸው 96 ተመራጮች ድምፅ ሲሰጡ ዉለዋል። የቅድመ-ምርጫ መጠይቆች እንደሚያመለክቱት የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ኅብረት በአውሮጳ ምክር ቤት ከፍተኛ ድምፅ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል ተብሏል። የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ እጎአ በ2009 ከተካሄደው ምርጫ በተሻለ ድምፅ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተገምቷል።በአውሮጳ ኅብረት ለምክር ቤት ምርጫ በ28ቱ የኅብረቱ አባል ሃገራት ውስጥ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች መካከል የሚወክሏቸውን 751 የምክር ቤት አባላት ይመርጣሉ ተብሎ ተጠብቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የጀርመን ዜግነት የሌላቸው የውጭ ሃገራት ነዋሪዎችም በጀርመን የውጭ ሃገራት ውህደት የምክር ቤት አባላት ተወካዮቻቸውን በዛሬው ዕለት ሲመርጡ ውለዋል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶ ስለሺ