የአዉሮጳ ኅብረትን ያወዛገበዉ የስደተኞች ጉዳይ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአዉሮጳ ኅብረትን ያወዛገበዉ የስደተኞች ጉዳይ

የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ወደአዉሮጳ ግዛት የገቡ ስደተኞችን ለአባል ሃገራት በሚያከፋፍሉበት መሠረታዊ መመሪያ ላይ መስማማት እንደቻሉ እየተነገረ ነዉ። ሆኖም ግን መሪዎቹ 40 ሺ የሚሆኑትን ጥገኝነት ጠያቂዎች በምን መልኩ ለየሃገራቱ እንደሚያከፋፍሉ ዝርዝሩን አልገለፁም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:57 ደቂቃ

የአዉሮጳ ኅብረትን ያወዛገበዉ የስደተኞች ጉዳይ

አፍሪቃና መካከለኛዉ ምሥራቅ ሃገራት ዉስጥ የሚካሄደዉ ግጭትና ጭቆና በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ከለላ ፍለጋ ወይም ለተሻለ ሕይወት ወደአዉሮጳ እንዲጎርፉ እየገፋፋ መሆኑ እየታየ ነዉ። በርካቶችም ወደአዉሮጳ እንገባለን ብለዉ መንገድ ላይ ሕይወታቸዉን አጥተዋል።

ጣሊያን ለአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ጠንከር ያለ አቤቱታና ማሳሰቢያ ማቅረብ ከጀመረች ሰነባብታለች። በትናንታዉ ዕለትም የኅብረቱ መሪዎች ለስደተኞች ጥገኝነት ስለመስጠት ለመነጋገር ማምሻዉን ሲሰባሰቡም የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ እንደአዉሮጳ ኅብረትነታችን ወይ ትብብራችሁን አሳዩን አለያም ጊዜያችንን አታባክኑ በማለት የመጨረሻ ቃል እንደሚፈልጉ አመልክተዋል። ከአባል ሀገር ጎን የማይቆም የአዉሮጳ ትብብርም በአፍንጫችን ይዉጣ ዓይነት ነዉ ሬኒዚ ለ27ቱ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ያስተላለፉት መልክዕት። ጣሊያንና ወደአዉሮጳ የሜዲትራኒያን ባህርን በጀልባ እያቋረጡ ለሚገቡ በርካታ ስደተኞች መሸጋገሪያ መሆኗ ከአቅሟ በላይ በስደተኞች እንድትጥለቀለቅ ስላደረጋት ሌሎች የኅብረቱ ሃገራት ሸክሟን እንዲጋሩ ማሳሰብ ከጀመረች ሰነባብታለች። ግሪክም በተመሳሳይ ካለባት የፋይናንስ ቀዉስ ባልተናነሰ የስደተኞች መበራከት አስጨንቋታል። ለአብዛኞቹ ስደተኞች ደግሞ ጣሊያንም ሆነች ግሪክ መሸጋገሪያቸዉ እንጂ መድረሻ ግባቸዉ አይደሉም። ድንበር አልፎ ወደሌሎቹ የአዉሮጳ ሃገራት ለመዝለቅ ግን ጥገኝነት ለመጠየቅ በመጀመሪያ የገቡበት ሀገር የሚለዉ የኅብረቱ ስምምነት ስለሚያግዳቸዉ የሁለቱ ሃገራት ዕዳ መሆናቸዉ አልቀረም።

በዚህ ምክንያትም ነዉ ያን ሕግ ወደጎን ብለዉ 40,000 የሚሆኑትን ጥገኝነት ጠያቂዎች በመላዉ የኅብረቱ አባል ሃገራት የማከፋፈሉ ሃሳብ የቀረበዉ። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የአባል ሃገራቱ ሃሳብ በመለያየቱም ከዉሳኔ ለመድረስ ጊዜ መፍጀቱ እየታየ ነዉ። የኅብረቱ የዜና ምንጮች እንደጠቆሙትም በጉዳዩ ላይ የሚከራከሩት የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ቱስክና የአዉሮጳ ኮሚሽን ኃላፊ ዣን ክላዉድ ዩንከር ስብሰባ ላይ መግባባት ተስኗቸዋል። ዩንከር ግን የተባለዉን በማስተባበል፤ የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ኮሚሽኑ ባቀረበዉ ሃሳብ መሠረት ጥገኝነት ጠያቂዎቹን ለማከፋፈል መስማማታቸዉን ጠቁመዋል። እንዲያም ሆኖ ስደተኞቹን የማስፈሩ ርምጃ ግን በፈቃደንነት ይሁን አይሁን ተግባራዊ እንዲሆን ከስምምነት መደረሱንም አመልክተዋል። በአንፃሩ ሀገራቸዉ ፖላንድ ስደተኞችን በኮታ ለየሃገራቱ ማካፈል የሚለዉን ሃሳብ የምትቃወመዉ ዶናልድ ቱስክ በበኩላቸዉ ምንም እንኳን በሀሳቡ መስማማት የተቻለ ቢሆንም የጥገኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት የሌለዉ ሕገወጥ ስደተኞች ግን አዉሮጳ ዉስጥ የመቆየት እድል እንደሌላቸዉ ነዉ ግልፅ ያደረጉት።

«ከሁሉ አስቀድሞ ሕገወጥ ስደተኝነትን መግታት ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ ቅድሚያ ልንሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ ነዉ። ዛሬ የአዉሮጳ ምክር ቤት ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ እጠብቃለሁ፤ ይኸዉም ጥገኝነት ለመጠየቅ ሕጋዊ ተቀባይነት የሌላቸዉ በሙሉ አዉሮጳ ዉስጥ ለመቆየት የሚያበቃ ምንም ማስተማመኛ አይኖራቸዉም። እናም ይህን መዕክት ግልፅ በማድረግ ብቻ ነዉ ከጣሊያንና ግሪክ ሰዎችን ወደሌሎች ሃገራት ማሻገር የምንችለዉ።»

የአዉሮጳ ኮሚሽን ባቀረበዉ ሃሳብ መሠረትም ግሪክና ጣሊያን የሚገኙ 40,000 ሶርያዉያንና ኤርትራዉያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በቀጣይ ሁለት ዓመታት ዉስጥ ወደየአባል ሃገራቱ ይከፋፈላሉ። ከዚህም ሌላ ከአዉሮጳ ዉጭ በመጠለያ ዉስጥ የሚገኙ 20ሺ ሶርያዉያን ስደተኞችም በዚሁ መሠረት በአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት እንዲሰፍሩ ለማድረግ ታስቧል። እያንዳንዱ አባል ሀገርም ስንት ተገን ጠያቂ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ እስከሐምሌ ወር መገባደጃ ድረስ ማሳወቅ ይኖርበታል። ስደተኞቹን በኮታ ማከፋፈል የሚለዉ ሀሳብ በብዙዎቹ ተቀባይነት ማጣቱን የጠቆሙት ቱስክ በፈቃደኝነት ሲባል ግን አባል ነኝ እያሉ አለመተባበር ተቀባይነት አይኖረዉም ነዉ ያሉት።

EU Gipfel zu Griechenland in Brüssel - Donald Tusk

ዶናልድ ቱስክ

«በፈቃደኝነት የሚከናወን ነዉ መባሉ ምንም ላለማድረግ ምክንያት ሊሆን አይችልም። በፈቃደኝነት የሚለዉን አሠራር የሚፈልጉት ወገኖች ለምን እንደሆነ ይገባኛል። ነገር ግን ተዓማኒ የሚሆኑት ቢያንስ እስከሐምሌ ማለቂያ ተጨባጭና የሚታይ ቃል ሲገቡ ብቻ ነዉ። ምክንያቱም መስዋዕትነት ያልታከለበት መተባበር የታይታ ብቻ ነዉ የሚሆነዉ። ስለዚህ አሁን ትብብርን አስመልክቶ ባዶ ዉሳኔዎች ብቻ አይደለም የምንፈልገዉ፤ ተግባርና ቁጥሮችን እንፈልጋለን።»

ብሪታንያ፣ ሃንጋሪ፣ እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የስደተኛ ቁጥር ይጨምርብናል በማለት ይህን ሃሳብ ተቃዉመዋል። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ ከአንድ መቶ ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች የሜዲትራኒያን ባህርን ተሻግረዉ አዉሮጳ ገብተዋል። አብዛኞቹም ጣሊያን፤ ግሪክና ማልታ ነዉ የሚገኙት። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አሁን የኅብረቱ ሃገራት በጋራ ለስደት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመወጋት ረገድ ከአንድ ዉሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

«አሁን መደረግ የሚኖርበት ዘላቂ መፍትሄ ለችግሩ መፈለግ ነዉ፤ ለዚህም በአባል ሃገራት መካከል የበለጠ መተባበር ያስፈልጋል። ይህም ለስደት ምክንያት የሆነዉን መንስኤ ለመዋጋት መወሰን ማለት ነዉ። ኮሚሽኑ ያቀረበዉ ሃሳብ በትክክለኛዉ አቅጣጫ የሄደ ነዉ ለዚህም ነዉ ጀርመን በክርክሩ ላይ እጅግ ገንቢ በሆነ መልኩ የተሳተፈችዉ።»

የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ተገን ጠያቂዎቹን ወደሁሉም አባል ሃገራት ማከፋፈል በሚለዉ ቢስማሙም ዝርዝር አፈፃጸሙን የየሃገራቱ የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች እስከመጪዉ ሐምሌ ወር ማለቂያ ደረስ አጥንተዉ ያሳዉቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic