የአዉሮጳ ኅብረትና የስደተኞች ጉዳይ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአዉሮጳ ኅብረትና የስደተኞች ጉዳይ

የአዉሮጳ ኅብረት ጣሊያንና ግሪክ የገቡ ስደተኞችን ወደተለያዩ አባል ሃገራት የማስፈር እቅድ ነድፏል። ወደአዉሮጳ ለመግባት የሚያልሙ ስደተኞች የሚሸጋገሩባቸዉ ግሪክና ጣሊያን ችግሩ ከአቅማቸዉ በላይ መሆኑን መናገር ከጀመሩ ሰንብተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:55 ደቂቃ

የአዉሮጳ ኅብረትና የስደተኞች ጉዳይ

የአዉሮጳ ኅብረት በስደተኞች የተጥለቀለቁትን ሁለቱን ሃገራት ባስቸኳይ መተባበሩ ጊዜ ሊሰጠዉ እንደማይገባ ያሳስባል። የኅብረቱ ሀሳብ ግን የሁሉንም አባል ሃገራት ስምምነት ያገኘ አይመስልም።

ወደአዉሮጳ የገባ ተሰዳጆች ጠያቂ በኅብረቱ ዉል መሠረት መጀመሪያ እግሩ በረገጠበት ሀገር ነዉ ጥገኝነት መጠየቅ የሚችለዉ። በሜዲትራኒያን ባህር ላይ እስካሁን የቀጠለዉ የስደተኞች ፍሰት አሁን ኅብረቱ የቀድሞ መመሪያዉን እንዲያሻሽል ያስገደደዉ ይመስላል። የአዉሮጳ ኅብረት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነዉ በኅብረቱ ስምምነት ዉስጥ አዲስ አንቀጽ ለመጨመር ሲወስን። አዲሱ አንቀጽም የአስቸኳይ ጊዜን ይመለከታል። ይህም ወደአዉሮጳ የገቡ ስደተኞችን ወደተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገራት ተከፋፍለዉ ጥገኝነት እንዲያገኙ የሚፈቅድ ነዉ። በአሁኑ ጊዜ ጣሊያንና ግሪክ ወደአዉሮጳ ለመግባት ባላባራዉ የስደተኞች ጎርፍ ተጥለቅልቀዋል።

Belgien EU-Kommission beschliesst Quotenplan für Flüchtlinge

የኅብረቱ ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራምፖሎስ

ማልታም ለረዥም ጊዜያት የስደተኞች መዳረሻ በመሆኗ ስትቸገር ቆይታለች። አዲሱ የኅብረቱ አንቀጽ አሁን ትኩረቱ ጣልያንና ግሪክን ያስጨነቁትን ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደተለያዩ የኅብረቱ ሃገራት አከፋፍሎ የሁለቱን ሃገራት ችግር ለማቃለል ያለመ ነዉ። የኅብረቱ ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራምፖሎስ ይዘረዝራሉ፤

«40,000 ጥገኝነት ፈላጊዎችን ወደሌሎች ሃገራት ለማስፈር የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ እቅድ አለን። በሁለት ዓመታት ዉስጥም ሶርያዉያንና ኤርትራዉያን ከጣሊያንና ግሪክ በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት እንዲሰፍሩ ይደረጋል።»

ሆኖም ሃሳቡን እንደማርቀቁ ተግባራዊነቱ ቀላል አይደለም። የኅብረቱ ባለስልጣናት አባል ሃገራቱ ሃሳቡን እንዲቀበሉት ለማግባባት ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ብሪታንያ፤ ዴንማርክ፣ እንዲሁም አየርላንድ በኅብረቱ ዉስጥ ያላቸዉን ልዩ መብት ተጠቅመዉ ከአስቸኳይ ጊዜ እቅዱ ራሳቸዉን ማግለል ይችላሉ። ፈረንሳይ፤ ስፔን፣ ሀንገሪ፣ ፖርቱጋል፣ ቼክ ሪፑብሊክ፣ የባልካን ሃገራት እና ስሎቫኪያ ተገን ጠያቂዎቹን በዉስን ኮታ መቀበል እንደማይፈልጉ ይፋ አድርገዋል። ኮሚሽነር አቭራምፖሎስ ግን ለስደተኞች ጥገኝነት የመስጠቱ ዉሳኔ ከኮታ ጋ ግንኙነት እንደሌለዉ ያስረዳሉ፤

«አንዳንድ በትክክል ያለመረዳት ወይም የአተረጓጎም ስህተቶች አሉ። በሕገወጥ መንገድ የመጡ ስደተኞችን በመላዉ የአዉሮጳ ኅብረት የማስፈር ሃሳብ የለም። የተወሰነ ኮታ ስለመኖሩም ሃሳብ አላቀረብንም። የማንወደዉና በፍፁም ያልተጠቀምነዉ ቃል ነዉ። ይህ ሁሉ አጋርነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነዉ። ያም ቢሆን ግን ለስንት ስደተኞች የጥገኝነት ማረጋገጫ መስጠት እንደሚችል መወሰን የሚችለዉ እያንዳንዱ አባል ሀገር ነዉ።»

ያም ሆኖ ሁሉም የኅብረቱ አባል ሃገራት የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ባቀረበዉ ሃሳብ መሠረት ጥገኝነት ፈላጊዎቹን ለመቀበል አልተዘጋጁም። የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን በተቻለዉ አባላቱን ለማግባባት እየጣረ ነዉ። ጥገኝነት ጠያቂዎቹን ለሚቀበሉ ሃገራትም ከ6000 ዩሮ አንስቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ ገልጿል። ቀደም ሲል ግን የኮሚሽነሩ ሠራተኞች አባል ሃገራት ባላቸዉ ስፋትና የኤኮኖሚ ጥንካሬ መሠረት ጥገኝነት ጠያቂዎቹን በኮታ እንደሚቀበሉ አመልክተዉ ነበር። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ጀርመን በሁለት ዓመት ዉስጥ እስከ 8000 ስደተኞች መቀበል ይኖርባታል። የአረንጓዴ ፓርቲ የአዉሮጳ ምክር ቤት አባል ስካ ካለር ስደተኞቹን ለመቀበል ለረዥም ጊዜ የቆየዉ የኅብረቱ ዉል መስተካከል ይኖርበታል ይላሉ፤

Schweigeminute beim EU-Sondergipfel zur Flüchtlingspolitik

ሊቢያ ዉስጥ ለተገደሉት ስደተኞች የሕሊና ጸሎት

«ጥገኝነት ጠያቂዎቹን ማከፋፈሉ የመጀመሪያዉ ርምጃ ነዉ። ሆኖም ጥገኝነት ጠያቂዎች የት መጠየቅ እንዳለባቸዉ የሚደነግገዉ የደብሊኑን መመሪያ ከመሠረቱ መለወጥ ይኖርበታል። ይህም እግራቸዉ በገባበት የመጀመሪያ የአዉሮጳ ግዛት የሚለዉ ማለት ነዉ። ይህ ደግሞ አሁን አይሰራም። ለረዥም ጊዜ ያየነዉ ጉዳይ ነዉ።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም በተለይም የስደተኞቹ መዳረሻ የሆኑት የመጀመሪያዎቹ የአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸዉም አልተወጡም። ለምሳሌ ሜዲትራኒያን ባህርን እያቋረጡ ወደጣሊያን ደሴቶች የሚመጡትን ተገቢዉን ምዝገባ ሳታካሂድ ወደሰሜን ታሳልፋቸዋለች በሚል ጀርመን ጣሊያንን ትወቅሳለች። የአዉሮጳ ኅብረት በ2ዓመት ዉስጥ ወደየአባል ሃገራቱ በማከፋፈል ጥገኝነት እንዲያገኙ ለማድረግ ካለመዉ ጣሊያንና ግሪክ ዉስጥ ከሚገኙት 40,000 ተሰዳጆች በተጨማሪ 20,000 ሶርያዉያንንም ከአዉሮጳ ዉጭ ከየሚገኙባቸዉ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚያመጣ ተገልጿል። ዉሳኔዉም እነኚህ ስደተኞች አዉሮጳ ለመግባት ሲሉ በሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች እጅ ወድቀዉ በአደገኛ መንገድ ሜድትራኒያን ባህርን ከማቋረጥ ለማዳን ነዉ። ኅብረቱ ከሀገር ሀገር ሰዉን በ ሕገወጥ መንገድ አሸጋጋሪዎቹን ለመቆጣጠር የባህር ላይ ጥበቃና ቅኝቱን ማጠናከሩን አስታዉቋል።

በርን ሪገርት/ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic