የአዉሮጳ ሕብረትና የደቡብ አሜሪካ መሪዎች ጉባኤ | ዓለም | DW | 16.05.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአዉሮጳ ሕብረትና የደቡብ አሜሪካ መሪዎች ጉባኤ

የጉባኤተኞቹ ፈርጀ-ብዙ ልዩነት፤ ብዙ በሚያማዝዘዉ ዉዝግብ እንደደመቀ፣ ነዉ-ፋርክ የተባለዉን የኮሎምቢያ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የቬኑዝዌላና የቦልቪያ መሪዎች ይረዳሉ የሚለዉ ዘገባ ተሰራጨ።ሌላ ጠብ።

ጋርሺያና ሜርክል

ጋርሺያና ሜርክል

የአዉሮጳ ሕብረት አባላትና የደቡብ አሜሪካ ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ሊማ-ፔሩ ዉስጥ ከጥቂት ሰአታት በፊት ተጀምሯል።ጉባኤዉ የሁለቱን አሐጉራት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነዉ።ይሁንና የደቡብ አሜሪካ ሐገራት መሪዎች እርስበራሰቸዉ የገጠሙት ዉዝግብና የቬኑዙዌላዉ ፕሬዝዳትና የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት እንኪያ ሠላንቲያ የጉባኤዉን ሒደት ያዉከዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።


በአብዛኛዉ በኢንዱስትሪ የበለፀገዉን አዉሮጳን በጥሬ ሐብት ከተንበሻበሸዉ ደቡብ አሜሪካ ጋር ለማስተሳሰር ይሕን መሰሉ ጉባኤ ሲደረግ የዛሬዉ አምስተኛዉ ነዉ።የየአመቱ ጉባኤ ልዩነት፤ አለመግባባት፣ እልፍ ብሎም ዉዝግብ አጥቶት አያዉቅም።የዘንድሮዉን ያክል የከረረ-የቃላት እሰጥ አገባ፣ የመረረ ንትርክ አልነበረም።

የጉባኤዉ አዘጋጆች ሃያ ሰባቱን የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች፣ ከሰላሳ-ሰወስቱ የደቡብ አሜሪካ አቻዎቻቸዉ ጋር የሚነጋገሩበት ርዕሥ-ሥፍራ ሲያረቁ፣ ሲመርጡ ተቃዋሚዎቻቸዉን፣ በተለይ የቀኝ-ዘመምና ወግ አጥባቂ መሪዎችን ለማብጠልጠል የሚናገሩት የማያጡ-ለመምረጥ የማይጨነቁት የቬቤኑዙዌላዉ ፕሬዝዳት ሁጎ ሻቬዝ በጀርመናዊቷ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ላይ የቃላት ወዦቧቸዉ ይዘረግፉት ገቡ።

ሻቤዥ፣ ወግ አጥባቂዉን የጀርመን የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ CDUን የሚወክሉትን ሜሪክልን ናዚ እያሉ ቢዘልፏቸዉም ወይዘሮ ሜርክል ከጉባኤዉ በፊት በብራዚል፤ በሜክሲኮና ኮሎምቢያ ያደረጉት ጉብኝት አልተሰናከለም።ዛሬ-ሁለቱ መሪዎች ሊማ ዉስት ባንድ አዳራሽ ይቀመጣሉ።

ጉባኤዉን በበላይነት ካዘጋጁት አንዷ፣ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ቤኒታ ፌሬሮ-ቫልድነር እንደሚሉት የሻቬዥ-ሜርክል ልዩነት ያሁኑን አይደለም የወደፊቱን ጉባኤም አሚያዉክ አይደለም።

«በየትኛዉም መንገድ ቢሆን ከዛሬዉ ጉባኤ የሚቀጥለዉ የኮፐን-ሐገኑ ጉባኤ እንዲሳካ በጋራ እየሠራን ነዉ።የጋራ አለማችን ከግብ እንዲደርሱ እንመኛለን።ይሁንና ባሁኑ ወቅት ከአላማችን ግብ ለመድረስ ምን ያሕል ርቀት እንደሚቀረን ወይም ሥንቱ እጅ እንደተሳካልን ገና አይታወቅም።»


ጉባኤዉ በሻቬዥ-ሜርክል ንትርክ መታጎል አለመታጎሎ አነጋግሮ ሳያበቃ እንደ ሻቬዥ ሁሉ የግራዉን የፖለቲካ መርሕ ያቀነቅናሉ የሚባሉት የቦልቪያዉ ፕሬዝዳት ኢቮ ሞራሌስ የአዉሮጳና የደቡብ አሜሪካ ሐገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ይመስርቱ የሚለዉን ሐሳብ ተቃወሙት።የሞራሌስን ሐሳብ ሻቬዝም፣ ሌሎች ጥቂት የአካባቢዉ ሐገራት መሪዎችም ይጋሩታል።አብዛኞቹ ግን ሥምምነቱ ይኑር ባይ ናቸዉ።የጉባኤዉ አስተናጋጅ የሊማዉ ፕሬዝዳት አለን ጋሪሺያ የማያግባቡትን ትተዉ በሚያግባቡት ላይ መናገሩን ነበር የመረጡት።

«ሁሉም ሰዉ ከቴክኖሎጂ እድገት ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን፤ የዲሞክራሲያዊዉ ሥርዓትና የእኩልነት መርሕ ተካፋይ እንዲሆን መፍቀድ ትልቁ ፈታኝ ዉሳኔ ነዉ።ይሕ ማለት ታዲያ ለወደፊቱ የምጣኔ ሐብት እድገት የጠፈጥሮ ሐብት መራቆት የለበትም ማለትም ጭምር ነዉ።»

የጉባኤተኞቹ ፈርጀ-ብዙ ልዩነት፤ ብዙ በሚያማዝዘዉ ዉዝግብ እንደደመቀ፣ ነዉ-ፋርክ የተባለዉን የኮሎምቢያ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የቬኑዝዌላና የቦልቪያ መሪዎች ይረዳሉ የሚለዉ ዘገባ ተሰራጨ።ሌላ ጠብ። ሻቬዝና ሞራሌስ የኮሎምቢያ አቻቸዉን አልቫሮ ኡርቢን ይወርዱባቸዉ ገቡ።በዚሁ መሐል ሁሉም ከጉባኤዉ ታደመ።