የአዉሮጳና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ | አፍሪቃ | DW | 02.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአዉሮጳና የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ

ጉባኤዉ ገና ሳይጀመር በፊት የአዉሮጳ ሕብረት የአፍሪቃ ሕብረት አባል ያልሆኑትን የአፍሪቃ መሪዎች ጋብዞ አባል ከሆኑት አንዳንዶቹን አለመጋበዙን የተቃወሙ የአፍሪቃ መሪዎች በጉባኤዉ አልተሳተፉም

የአዉሮጳ ሕብረትና የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች አራተኛ የጋራ ጉባኤያቸዉን ዛሬ ብራስልስ-ቤሌጅግ ዉስጥ ጀምረዋል።የሰባ ሐገራት ርዕሳነ-ብሔራት፤ መራሕያነ መንግሥታትና ተወካዮች የተካፈሉበት ጉባኤ የሁለቱን አሐጉራት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነዉ። ጉባኤ በአፍሪቃና በአውሮፓ ኅብረት ፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብታዊ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ትስስሮች ና በአፍሪቃ ግጭቶችን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ለሁለት ቀናት ይመክራል። በጉባኤው ላይ ከተገኙት የአውሮፓ መሪዎች ውስጥ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ እና የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮሬንሲ፤ ከ53 ቱ የአፍሪቃ መሪዎችም የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ጉድላክ ጆናታንና የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ይገኙበታል። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጉባኤው ለአፍሪቃ ችግሮች አፍሪቃዊ መፍትሄ ላይ እንደሚወያይ ተናግረዋል። የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኽርማን ቫን ሮምፖይ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር አውሮፓ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸውን ችግሮች

ለመፍታት፤ ለስደት መፍትሄ ለመፈለግና የሁለቱንም ክፍለ ዓለማት የፀጥታ ጥበቃ ለማሻሻል የአፍሪቃን ድጋፍ እንደምትሻ አስታውቀዋል። አውሮፓ ዋነኛዋ የአፍሪቃ የንግድ እና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አጋር ሆኖ መቀጠል እንደምትፈልግም ተናግረዋል። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የኒዠር ፕሬዝዳንት ማህማዱ ኢሱፉ ደግሞ የሁለቱ ክፍለ አለማት የልማት ትብብር መቀጠል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

«ከዚህ ስብሰባ የምንጠብቀው አውሮፓ ከአፍሪቃ መንግስታት ጎን መቆምዋን እንድትቀጥል ነው። አውሮፓ የመጀመሪያዋ አጋራችን ነች። እና በሁለታችን መካከል ያለው አጋርነት መቀጠሉ ወሳኝ ነው። በሊዝበኑ ጉባኤያችን አንድ የጋራ ስልት አውጥተን ነበር። ያ ስልት ደግሞ ፍሬ አስገኝቷል። እናም ይሄ እንዲቀጥል እንፈልጋለን። በተለይ የልማት ጥያቄ ትኩረት እንዲያገኝ እንፈልጋለን።»

በጉባኤው ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚካሄደው ግድያ እንዲቆምና ለሰላማዊ ሰዎችም ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት በጉባኤው ዋዜማ እንዳስታወቀው በአፍሪቃ ግጭቶችን ለመከላከል 800 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 1.1 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት አቅዷል። ጉባኤው ከንግድ ና ከፀጥታ ጉዳዮች በተጨማሪ በአየር ንብረት ለውጥ በድህነት በስደት እና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይም ይነጋገራል። ነገም የሚቀጥለዉ ጉባኤ ሁነኛ ሥምምነትና መግባባት ይደረስበታል ተብሎ ግን አይጠበቅም።እንዲያዉም ጉባኤዉ ገና ሳይጀመር በፊት የአዉሮጳ ሕብረት የአፍሪቃ ሕብረት አባል ያልሆኑትን የአፍሪቃ መሪዎች ጋብዞ አባል ከሆኑት አንዳንዶቹን አለመጋበዙን የተቃወሙ የአፍሪቃ መሪዎች በጉባኤዉ አልተሳተፉም።የጉባኤዉን አጀማመርና ዓላማን በተመለከተ የብራስልስ ወኪላችንን ገበያዉ ንጉሴን በስልክ አነጋግሬዉ ነበር።

ገበያዉ ንጉሴን

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic