የአካዳሚ ማዕረግና የሸፍጥ ንግድ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 16.05.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአካዳሚ ማዕረግና የሸፍጥ ንግድ

በተለያዩ አገሮች እንደሚያጋጥመው ሁሉ፤ በዚህ በጀርመን ሀገርም የአካደሚ ማዕረግ የሸፍጥ ነጋዴዎች አሉ። ያልደከሙበትን ማዕረግ ለማግኘት የሚፈልጉም የዚያኑ ያህል! በሌላ በኩል ኅሊና በማይፈቅደው ሁኔታ የመመረቂያ ጽሑፍን ፤ ከሌሎች ሥራዎች

 የመሥረቅ ሁኔታ መኖሩም በየጊዜው ይወሳል። ጀርመን ፣ ከፍተኛ ትምህርትን ፤ በፌደራል ክፍለ-ሀገር ደረጃ ሳይሆን፤ በፌደራሉ መንግሥት ሥር ብታውል  ዓለም አቀፋዊ ደረጃዋን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ይበጃታል እየተባለም ነው።

 በጀርመን ሀገር ፣ ዩኒቨርስቲዎች ፤ በአካዳሚው ዓለም፣  እንዲህ እንዳሁኑ እጅግ በዛ ያሉ ለዶክተርነት ማዕረግ በተለያዩ ዘርፎች ምርምር የሚያካሂዱ ተማሪዎች ተበራክተው አያውቁም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪዎችና ፕሮፌሰሮች፣ ስለዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ ፤ የሚሰጡት ምላሽ በደፈናው፣ በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ የተሠማሩት ተማሪዎች፣  እጅግ በዛ ያሉ ናቸው የሚል ነው።  በጀርመን ሀገር በያመቱ 25,000 ያህል ተማሪዎች ናቸው፣  በዶክተርነት ማዕረግ የሚመረቁት። ቁጥሩ ፣ ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር የጀርመን እጅግ ብዙ ነው። አንድ ከፍተኛ የቀለም ተማሪ (የካዳሚ ሰው)ለምረቃ የሚያቀርበው ጽሑፍ፤ በህይወቱ የሚገጥመው ከፍተኛው ሳይንሳዊ ፈተና ነው። የመጨረሻው ዓላማ ፤ ሰፊ ምርምር በማድረግ ለሳይንስ ተገቢውን ቦታ በመስጠት  ኑሮንም ሆነ ህይወትን ከዚሁ ዘርፍ ጋር ማያያዝ ነው።

የዶክተርነት ማዕረግ፣ እንደ ጥንቱ ብርቅ አይደለም። ባሁኑ ዘመን እንደ ኢንዱስትሪ ምርት በሽ-በሽ ሆኗል።  ዋጋውም ሆነ ክብሩ እየቀነሰ ለመምጣቱ፤ ፈተና ወስደው በሚያልፉት መጠን መገምገም ይቻላል ይላሉ፤ ከፍተኛ የትምህርት  ተቋማትን  የትምህርት ጥራት የሚመረምሩ ጠበብት። በፈተና የሚወድቁት ከአንድ  ከመቶ በታች ናቸው። ታዲያ ፈተናን አልፎ ፣ እንደ የደረጃው በአስመሥጋኝ ውጤት ፣ በላቲኑ የክብር አጠራር፣ Cum Laude  (ከክብር ጋር)   Magna Cum Laude (ከታላቅ ክብር ጋር)  Summa Cum Laude (ከከፍተኛ ክብር ጋር)እንዲያም ሲል  Maxima Cum Laude(ከበጣም ትልቅ ክብር ጋር )  በሚሉ ማዕረጎች መመረቅ የተለመደ ጉዳይ ነው። ታዲያ ይህ እንዳለ ሆኖ ፤ የጥራቱ  ቁጥጥር በእርግጥ እስከምን ድረስ ነው? እንዴት ቁጥጥሩ ላላ? ለምንድን ነው ብዙዎች ጀርመናውያን የዶክተርነት ማዕረግ የሚፈልጉት? ከሥም በፊት በአህጽሮት የሚሠፍሩት ሁለት ሆኅያት ምንድን ነው ትርጓሜአቸው?  የሚሉ የአንክሮ ጥያቄዎች ይቀርባሉ። ኑሮውን ፣ ህይወቱን፤  ከሳይንሳዊ ምርምር ጋር አዛምዶ መዝለቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፣ ከ«ባችለር» ና  «ማስተር» ቀጥሎ በዶክተርነት ለመመረቅ የሚያስችለውን ጽሑፍ በብቃት የሚያቀርብ ፤ ወደ ፕሮፌሰርነት መሸጋገር ይችላል።

ይህ መደበኛውና ትክክለኛው አካሄድ ነው። ይሁንና ከዚህ ውጭ ህገ-ወጥና አሳፋሪም በሆነ መልኩ፣ እያጭበረበሩ ያልደከሙበትን አዝመራ ለመሰብሰብ የሚጥሩ ጥቂቶች እንዳልሆኑ እየተደረሰበት ነው።

በሰሜን ጀርመን ፣ በሃምበርግ ከተማ የሚታተመው ታዋቂው  ሳምንታዊ ጋዜጣ DIE ZEIT «የአካደሚ ማዕረግ የሸፍጥ ነጋዴዎች»፣  በሚል ርእስ፣ የትምህርትን  ማዕረግ፣ ቢሮ ከፍተው  በገንዘብ ስለሚለውጡ አጭበርባሪዎች ሰፊ ሐተታ ነው ያቀረበው። 

ሃንስ ቮልክማር የተባሉ ሰው። በ ምዕራብ ጀርመን ዞሊንገን በተባለች ከተማ በአንድ ራሱን በቻለ ሰፊ ቤት የሚኖሩ፤  «ፕሮፌሰር ክላውስ ዲተር ቪሎቭስኪ» የሚባሉ  ሰው፤ ዳሚር ባይታሎቭ ከተባሉ ጓደኛቸው ጋር ሆነው፣ በኤኮኖሚ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሰጧቸው መሆኑን ያስታውሳሉ። ከሞስኮ ዩኚቨርስቲ የተሰጠ በማሰኘት! የአንድ ኩባንያ አማካሪ የነበሩት ሃንስ ቮልክማር ፤ እንኳንስ የዶክተርነት ማዕረግ ሊኖራቸው የመጀመሪያ ዲግሪ የሚያገኙበትን ትምህርት እንኳ በቅጡ አላጠናቀቁም ። በሩሲያ የኮሌጅ መምህር ተብለው ተሰይመውም ነበር። ከ 10 ዓመት በፊት የሆነው ይህ ጉዳይ  ቮልክማርን እስካሁን እንደሚያሣፍራቸው ይናገራሉ። ክላውስ ዲተር ቪሎቭስኪ ዛሬም ዞሊንገን ውስጥ ባማሩ ቅብ ስዕሎች ባጌጠው ቤታቸው፣ ከፍተኛ የሐሰት የትምህርት ሰነዶችን  ከመሸጥ  የታቀቡበት ሁኔታ የለም። በማጭበርበር የሚያሰናዷቸውን  የአካደሚ ማዕረጎችን ሰነዶች ፣ እንደየደረጃቸው፤ ከ 25,000 እስከ 40,000 ዩውሮ ነው የሚሸጧቸው። የእኒህ ሰው ደንበኞችም በመቶ የሚቆጠሩ እንደነበሩ ጉዳዩን የተከታተሉ  ጋዜጦች አጋልጠዋል። አንዳንዶችም የሰውየውን ህገ-ወጥ ተግባር  ለመታዘብ ያህል ብቻ፣ ደንበኞች መስለው የቀረቧቸው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ክላውስ ዲተር ቪሎቭስኪ፤ በምሥራቅ አውሮፓ ከሚገኙ አንዳንድ በህገ ወጥ አሠራር ከተካኑ ሰዎች ጋር በመተባበር ያዛጋጇቸው የአካደሚ ማዕረጎች፣ የሩሲያ ዩኒቨርስቲዎች ጨርሶ የማያውቋቸው መሆኑም ተደርሶበታል።

በአንድ በኩል  ይህን በመሰለ  ጭፍን የማጭበርበር ተግባር፣ በአካዳሚው ዓለም ያልደከሙበትን ለማግኘት፣ ያልዘሩትን የትምህርት  አዝመራ ለመሰብሰብ የሚጥሩ መኖራቸው ሲታወቅ፤ በዚህ በጀርመን ሀገር ፤ ባለፈው ዓመት፤ የመከላከያ  ሚንስትር የነበሩት ካርል ቴዎዶር  ትሱ ጉተንበርግ፣ ለዶክተርነት ያበቀቸውን የመመረቂያ ጽሑፍ፤ ከሌሎች ሥራዎች ቃል- በቃል ገልብጠው መውሰዳቸውና  በዋቢነት አለመጥቀሳቸው፣ የሥልጣን ቦታቸውን ለቀው እስኪነሱ ያስገደዳቸው መሆኑ አይዘነጋም። በቅርቡ ደግሞ፣ የ ትሱ ጎተንበርግን  ያክል አገር እስኪያውቀው ድረስ በሰፊው የሌሎች ሰዎች  ሥራዎች አይጨለፍበት እንጂ፣ የጀርመን የትምህርትና  የምርምር ሚንስትር፤ የ 56 ዓመቷ  ዶ/ር አኔተ ሻባንም፣ እ ጎ አ በ 1980 ዓ ም፤ በዱሰልዶርፍ ዩኒቨርስቲ ፣ ለዚሁ ማዕረጋቸው ያበቃቸውን  Person und Gewissen(«ሰውና ኅሊና»)ያሉትን  ፣ 325 ገጾች  ያሉት የምረቃ ጽሑፍ ሲያዘጋጁ ፣ በ 50 ገጾች ውስጥ ፣ አልፎ -አልፎ  የተወሰኑ ዐረፍተ ነገሮችም ቢሆኑ፣  ከሌሎች ሰዎች ሥራዎች ሳይቆነጠሩ እንዳልቀሩ የሚጠቁም  ክስ ቢጤ፣ ከአንድ ድረ ገጽ ከተሰነዘረባቸው ወዲህ፣«ትክክለኛ ሥራ ስለመሥራቴ ኀሊናዬ ያውቃል» ከማለታቸውም፣ ዩኒቨርስቲው  የምረቃ ጽሑፋቸውን ዳግመኛ እንዲፈትሽ፣  ራሳቸው ጠይቀዋል።  የምረቃ ጽሑፋቸውን በተመለከተ  በድረ ገጽ ላይ የጻፈው ሰው ራሱን በይፋ ስላልገለጠ፤ ብዙም ለመናገር እንደማይሹ ነው የገለጡት።

የተለያዩ ታዋቂ ፖለቲከኞች በዶክተርነት ለመመረቅ ያሰናዷቸውን የጽሑፍ ሥራዎች የሚመረምረው VroniPlag የተሰኘው ድርጅት መሥራች፤ ማርቲን ሃይዲንግስፌልደር ፤ በቅርቡ ፤ አንዳንድ አንቀጾች ላይ በወ/ሮ ሻቫን ሥራዎች ላይ የሥርቆት ምልክት ቢኖርም ፤ እንደርሳቸው ግምገማ፤ አጠቃላይ የምረቃ ሥራቸውን ውድቅ የሚያደርግ እንዳልሆነ ከመጥቀሳቸውም፤ ፍጹም ከአጠያያቂነት የጸዳ ሥራ ግን አይደለም ማለታቸውን Neue Osnabrücker Zeitung የተሰኘው ጋዜጣ አሥፍሮታል።  

*********

ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ በአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከጥር ወር አንስቶ ፣ በአንድ ሚንስትር  የምረቃ ጽሑፍ ሳቢያ የተነሣው ክርክር ፤ የጀርመንን የአካዳሚ መድረክ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡንም ሲያነጋግር የቆየ ጉዳይ መሆኑ የሚታበል አይደለም። ይህ ደግሞ ፣ በመላው የአካዳሚው ዓለም ፤ የምርምር ሥራዎች፤ በትክክልና በንጹኅ ኅሊና የሚቀርቡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ይበልጥ የሚያስገነዝብ  ሳይሆን  እንዳልቀረ ነው የሚታሰበው።

በጀርመን ሀገር፤ ትምህርት ፣ የከፈተኛ ደረጃ ትምህርትም ጭምር ፤ በጀቱም ፤ አስተዳደሩም ፤ የፌደራሉ መንግሥት ሳይሆን የፌደራል ክፍላተ-ሀገር ኀላፊነት ነው። በመሆኑም፣ ጀርመን ፤ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ጥቂት ዩኒቨርስቲዎች ብታደራጅ የተሻለ ነው የሚሉ አልታጡም። ጥቂት የጀርመን ፌደራል ዩኒቨርስቲዎች፤ በዩናይትድ እስቴትስ እንደሚገኙት፣ እንደ ሓርቫርድ፤ የል፤ እስታንፈርድ፣  ወይም እንደ እንግሊዝ ዩኒቨርስቲዎች፤ ኦክስፈርድና ኬምብሪጅ ዝናን የሚያተርፉ ከፍተኛ የትምህርት  ተቋማት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሓሳቡ አንቀሳቃሺዎች ከፍተኛ ምኞት አላቸው። ለምሳሌ ያህል በመዲናይቱ በበርሊን  የሚገኘው የ ሁምቦልት ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት፣ Jan-Hendrik Olbertz ሐሳቡን መደገፍ ብቻ ሳይሆን፤ እንዲከናወንም የሚወተውቱ  መሆናቸው ተጠቅሷል።

Bundesforschungsministerin Annette Schavan

«በጀርመን ሀገር ፣ በፌደራል ክፍላተ ሀገር የሚተዳደሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ አቋማቸው ጠንክሮ መገኘት ይኖርበታል። ፌደራል ክፍላተ-ሀገር፣ ዩኒቨርስቲዎቻቸውንና ኮሌጆቻቸውን፣ እንደሚፈለገው በሚገባ ለማደረጀት አቅሙ አይኖራቸውም። እንደ እውነቱ  ከሆነ፤ የፌደራል ዩኒቨርስቲዎችን እንበል 5 ወይም 7 በመለስኛ ጊዜ ውስጥ ማቋቋምም ሆነ ማደራጀት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።»

የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስትር ዶ/ር ሻቫን፤ በትምህርት  ረገድ የፌደራል ክፍላተ ሀገርን መብት መጋፋት ፍላጎታቸውም ፣ ዓላማቸውም አይደለም።  በመሠረታዊው የህገ-መንግሥት አንቀጽ ለውጥ ካልተደረገ የሚቻል አይደለም ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በቅድሚያ የፌደራል ክፍላተ ሀገር፤ ፈቃደኛነት መታወቅ አለበት ፤ ስምምነትም ያስፈልጋል። የሆነው ሆኖ፤ ይፋ ባይገለጽም፤ በራይንድፋልትዝ ፣ በካርልስሩኸ ከተማ የሚገኘው የሥነ ቴክኒክ ተቋም፣ የፌደራላዊ ዩኒቨርስቲ ደረጃ እንዲይዝ ሳይደረግ አልቀረም። የካርልስሩኸው የሥነ ቴክኒክ ተቋም፣ ከፌደራሉ መንግሥትና ከክፍለ ሀገሩ በአጠቃላይ በዓመት 780 ሚሊዮን ዩውሮ ተመድብሎታል። የተሳካ ውጤትም በማስመዝገብ ላይ ነው።    

የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስትር ዶ/ር አኔተ ሻቫን፣ በዛሬው ዕለት በርሊን ውስጥ በየ 2 ዓመት አንድ ጊዜ ፣ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የሚቀርበውን የጀርመንን የምርምርና  የፈጠራ ሥራዎች ደረጃ የሚቃኘውን ዘገባ ይፋ ያደረጋሉ። ይህም ዘገባ ጀርመን ከሌሎች በኢንዱስትሪ ከገሠገሡ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ደረጃዋ  ምን ላይ እንደሆነም የሚያመላክት ሳይሆን አይቀርም። ከዚህ ጋር በማያያዝም ፣ ሚንስትርዋ፣ በዩኒቨርስቲዎችም  ሆነ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም፤ በሌሎች ተቋማት በከፍተኛ ደረጃ የምርምር ሥራዎች እንዲከናወኑ ሳያሳስቡ እንደማይቀሩ ነው የሚጠበቀው።  በሳይንሱ ዘርፍ፣  የባለሙያዎች እጥረት እንዳያጋጥም ፤ የታዳጊ የሳይንስ ባለሙያዎች ሁኔታም እንዴት እንደሚገኝ ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።  

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic