የአካል ጉዳት መለኪያ ሶፍትዌር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 24.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአካል ጉዳት መለኪያ ሶፍትዌር

በኢትዮጵያ የመኪና አደጋ የሰው ሕይወትን በመቅጠፍ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። አደጋው አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይም ይገኛል። በመኪና አደጋ የሚከሰተው የአካል ጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ልኬቱን የሚያሳውቅ ሶፍትዌር በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ተሰርቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:39

ጉዳቱን አስልቶ፤ ግልጽነት ባለው መልክ እና በፍጥነት ለማወቅ ያስችላል

ኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶባቸዋል ከሚባሉ ሃገራት መካከል አንዷ ናት። በሀገሪቱ በአካል ጉዳት መንስኤነት ከተመዘገቡት ውስጥ የመኪና አደጋ በመጀመሪያው ረድፍ ይቀመጣል። በማሽኖች ምክንያት የሚደርስ የአካል ጉዳትም ሌላው ተጠቃሽ ነው። የአደጋው ተጎዲዎች ወደ አቅራቢያው ወደሚገኝ ህክምና ማዕከል እስከሚደርሱ ድረስ በመጀመሪያ ርዳታ ወቅት ለሚያጋጥም ደም መፍሰስ፣ የአጥንት ስብራት፣ የውስጥ አካላት መድማት ህክምና ይደረግላቸዋል። የአካል ጉዳቱን ተከትሎ የሚነሱ የካሳ ክፍያና ቅሬታውን ለመፍታት፤ የህክምና ባለሞያዎች የጉዳቱን መጠን የሚገልጽ የህክምና ማስረጃ በሚመለከታቸው የኢንሹራንስና ፖሊስ አካል ይጠየቃሉ። በዚህም ትክክለኛውን መረጃ ለመስጠት የህክምና ባለሞያዎች አዳጋች ሲሆንባቸው ይስተዋላል። ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ ቅድሚያ ትኩረታቸው የሰውን ሕይወት ማትረፍና ርዳታ በማድረጉ ላይ ስለሚሆን ነው።

አካል ጉዳተኝነት መጠን መለኪያ መተግበሪያ ሶፍትዌር (Disability Rating Software) ይሄን ችግር ለማቃለል ተሰርቷል። የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ የሶፍትዌር ፕሮጀክቱ ተመራማሪ ናቸው። ዶ/ር ብሩክ አዲሱ ሶፍትዌር በአደጋ የሚፈጠር የአካል ጉዳት መጠንን ትክክለኛ ጉዳቱን አስልቶ፤ ግልጽነት ባለው መልክ እና በፍጥነት ለማወቅ እንደሚያስችል ይገልጻሉ።  «የአካል ጉዳቱን ገምታችሁ ላኩልን የሚል ደብዳቤ ከኢንሹራንስ ካምፓኒዎች፣ ከፖሊስ፣ ከፍርድ ቤት ጥያቄዎች ይመጣሉ። በ2016 እኤአ ወደ ስራ ገባን። ብዙ ታካሚ በአንድ ጊዜ ልናስተናግድ በምንችልበት መልክ ጥያቄያችን መልስ ይመልሳል።» ዶ/ር ብሩክ አያይዘውም የአካል ጉዳት መለኪያ ፕሮጀክት ለሶፍትዌሩ አጋዥ መጽሀፍ በተያያዥነት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያትት መጽሀፍ ለህትመት እንደሚበቃም ጠቁመዋል። «መጽሐፉን መጻፍ ነው አንዱ ፕሮጀክት፤ አስተያየት ተሰጥቶበታል። በመጨረሻ ለህትመት ይወጣል።»

ሶፍትዌሩ የአካል ክፍልን ጉዳትን መዝግቦ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ አስልቶ እንደሚያስቀምጥ ዶ/ር ብሩክ ይጠቅሳሉ። «የመገጣጠሚያ፣ የአጥንት፣ የጅማት፣ የአንጎል ክፍል እነዚህ ቁጥር አላቸው። አንዱ የአካል ሲጎድል በየቀኑ እንቅስቃሴ ላይ የሚደርስ አለ። ለዛም የሶፍትዌሩ ሁሉም ቁጥር አለው።» በሶፍትዌር ፕሮጀክቱ ላይ ከተሳተፉት ባለሞያዎች የሶፍትዌር ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳግም መልኬ ናቸው። አዳዲስ ሶፍት ዌሮችን በመጠቀም እንደተሰራ እና የሶፍትዌሩ ይዘት ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። «እኔና ጓደኛዬ ተሳትፈንበታል። አዳሲስ ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀምን ነው የሰራነው። በሶፍትዌርነቱ ጥሩ ይዘት ያለው ነው። ሶፍትዌሩን ከፍተው የትኛው አካሉ እንደተጎዳ ከመረጡ ሶፍትዌሩ ሰርቶ ያወጣላቸዋል ማለት ነው።» የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሹመቴ ግዛው የአካል ጉዳት መለኪያ ሶፍትዌሩ ስራው ተጠናቆ በሀገሪቷ ሁሉም ሆስፒታሎች ከወራት በኋላ ይተገበራል ብለዋል። «ከጤናው ዘርፍ የደገፍናቸው የምርምር ፕሮጀክቶች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባሉ ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ ዋና ተመራማሪነት የሚመራ የአካል ጉዳትን መጠን ማወቂያ ሶፍትዌር ነው።» ይሄው የአካል ጉዳት ልኬት ሶፍትዌር ሊያስተማምን የሚችል የአሰራር ስርዓትም ሊሆን እንደሚችል ነው ዶ/ር ሹመቴ የገለጹት። ዐሥር ዓመታትን የፈጀው የአደጋ መጠን መለኪያ ሶፍትዌር ለችግሩ ቁልፍ መፍትሄ ይሆናል ተብሎም ይታሰባል። 

ነጃት ኢብራሂም

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic