የአከፓ-ሀገሮች ጉባኤና ማሳሰቢያው | ኤኮኖሚ | DW | 08.07.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአከፓ-ሀገሮች ጉባኤና ማሳሰቢያው

ከአውሮጳው ኅብረት ጋር በንግድና በልማት ትብብር የተጣመሩት ፸፱ኙ የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(በአሕጽሮት አከፓ)ሀገሮች ከሁለት ሣምንታት በፊት በሞዛምቢክ ርእሰከተማ ማፑቶ በመሪዎች ደረጃ ያካሄዱት ጉባኤ፣ በዓለም ንግድ ድርጅት ሥር መንቀሳቀስ የተሳነው ድርድር መልሶ እንዲነቃቃ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዘበ ነበር።

የዓለም ንግድ እንዲስተካከል ስለሚደረግበት ሁኔታ በቃታር ርእሰከተማ ዶሃ ተጀምሮ የነበረው ድርድር ዙር ባለፈው መስከረም የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባኤ በካንኩን/ሜክሲኮ በተካሄደበት ወቅት እንደከሸፈ የሚታወስ ነው። በዚሁ በዓለም ንግድ ድርጅት ሥር የሚካሄደው ድርድር፣ በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ ድጎማ የሚሰጠትን አጨቃጫቂ ጉዳይ ዋና ርእስ ማድረግ እንዳለበት “አከፓ” ሀገሮች በጥብቅ ነው የሚያስገነዝቡት።
የሚደረጁት ሀገሮች ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምረው የሚያጠብቁት ክርክር፥ ሀብታሞቹ ሀገሮች ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡት የፊናንሱ ድጋፍ የሸቀጦችን ዋጋ እያፋለሰ፣ የሦሥተኛው ዓለም ገበሬዎች የገበያ ውድድር አቅም እንዲያጡ ነው የሚያደርጋቸው ይላል።

በሌላው በኩል ደግሞ፣ አውሮጳ ውስጥ የስኳሩ ገበያ ለነፃው ንግድ ክፍት እንዲሆን የሚደረግበት ጥያቄ አንዳንድ አከፓ-ሀገሮችን የሚያሠጋ መሆኑም ነበር በማፑቶው ጉባኤ ላይ የተንፀባረቀው። ርግጥ፣ ለአውሮጳ ስኳር-አምራቾች የሚሰጠው የፊናንስ ድጎማ እንዲቀነስ የሚደረግበት ርምጃ ለአከፓ- ሀገራት ገበሬዎች ጠቀሜታን ያመጣል፤ ግን የአውሮጳው ገበያ በአውስትራሊያና በብራዚል ላሉት ውጤታማ ስኳር-አምራቾች ክፍት እንዲሆን ከተደረገ፣ በዚህ አኳኋን የውድድር አቅም የሚያጡት አከፓ-ሀገሮች የሚያገኙት ጠቀሜታ ከአጭር ጊዜ በኋላ ትርጓሜ እንደሚያጣ ነው የሚያስገነዝቡት። ስለዚህ፣ የአውሮጳው ኅብረት የልማት ጉዳዮች ተጠሪ ፓውል ኒልሶን እንደሚሉት፣ አውሮጳ ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ የሚመደበው የፊናንስ ድጎማ እንዲቀነስ የሚደረግበት ሁኔታ አንዱን ወገን ሲጠቅም፣ ሌላውን የሚጎዳ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ፣ አስቀድሞ እንደተጠቀሰው፣ የስኳሩ ንግድ ነፃነት ነው አንድ ምሳሌ የሚሆነው።

አከፓ-ሀገሮች እንደሚሉት፣ የንግድ ነፃነት ለሸንኮራገዳ አምራቾቻቸው የሚከፈለውን ዋጋ በጉልህ የሚቀንስባቸው እንደሚሆን ይሠጋሉ--በተለይም ለውጭ ንግድ ገቢያቸው ስኳርን ዋና ምንጭ የሚያደርጉት ሀገሮች ናቸው የንግዱ ነፃነት ጉዳት እንደሚያመጣባቸው የሚያስቡት። ከዚህም የተነሳ፣ የአውሮጳው ኅብረት የዋጋ ቅናሽ በሚፈጠርበት ጊዜ አባላቱ ሀገራት ለሚደርስባቸው የገቢ ጉድለት ማካካሻውን ዋስትና እንዲሰጥ አከፓ-ሀገሮች አጥብቀው ነው የሚጠይቁት። የሸቀጦች ዋጋ በሚወርድበት ጊዜ የአውሮጳ ገበሬዎች ማካካሻውን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችለው የግብርና መምሪያ ግምጃቤት ለእነርሱም የሚጠቅም እንደሚሆን ነው አከፓ-ሀገሮች ተሥፋ የሚያደርጉት። በማፑቶው ጉባኤ ፍፃሜ ላይ የተሰጠው መግለጫ፥ በዋጋ እና በገቢ ደረጃ ረገድ የሚደረግ አንዳች ልዩነት በአከፓ ሀገሮችና በአውሮጳው ኅብረት መካከል ያለውን የትብብር ትርጓሜና መንፈስ የሚቃረን ነው የሚሆነው ይላል። ንግድ ነፃ እንዲሆን የሚደረግበት ርምጃ በመጀመሪያ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማካካስ ይቻል ዘንድ፣ ለአባላቱ ሀገሮች የስኳር አቅርቦቱ ተመን በሚቀጥሉት ፲፭ ዓመታት ውስጥ በያመቱ ከፍ እንዲልላቸውም ነው አከፓ-ሀገሮች የሚጠይቁት።

በአከፓ-ሀገሮች አመለካከት መሠረት፣ ንግድ(ማለት የስኳር ንግድ) ነፃ እንዲሆን የሚደረግበት ርምጃ ቀስበቀስ፣ እርከን በእርከን የሚከናወን መሆን አለበት፤ ርምጃው ድንገተኛ ከሆነ የስኳር እንዱስትሪዎቻቸውን ክፉኛ የሚያመሰቃቅል እንደሚሆን ነው የሚሠጉት። አከፓ-ሀገሮች ለማናቸውም የዋጋ ቅናሽ ዝግጁ የሚሆኑበት በቂ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ያስገነዝባሉ። እንዱስትሪዎቻቸውን እንደገና በሚያደላድሉበት ጊዜ የስኳሩ አቅርቦታቸው ተመን እንዲጨመር አስፈላጊ ሆኖ ያዩታል። በርዥም ጊዜ ውስጥ ግን፣ ይኸው ልዩ የንግድ መድልዎ የሚያበቃ መሆን አለበት--አለበለዚያ ግን ከዓለም ንግድ ድርጅት ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ ይሆናል። አንዳንዶቹ ሀገሮች የንግዱን መድልዎ እጎአ እስከ ፪ሺ፯ እንዲያበቁት ነው የሚጠየቅባቸው።

የአውሮጳው ኅብረት አሁን በ፲ አዲስ አባላት የተስፋፋበትም ሁኔታ ነው ለአከፓ-ሀገሮች ጭንቀት ተጨማሪ ምክንያት የሚሆነው። በእነርሱ አመለካከት መሠረት፣ ካሁን ቀደም ከአውሮጳው ኅብረት ሲያገኙት የነበረው ርዳታ ወደ አዲሶቹና ደህየት ወዳሉት የኅብረቱ አባላት የሚቀለበስ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ፣ አዲሶቹ የአውሮጳው ኅብረት አባላት ለገበያ የሚያቀርቧቸው ዕቃዎች ጠንካራ ውድድር ሊደቅኑባቸው እንደሚችሉም ነው አከፓ-ሀገሮች የሚሰጉት። የሆነ ሆኖ፣ እነዚያው የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(አከፓ)ሀገሮች አውሮጳ ውስጥ በገበያ ውድድር ለመጠናከር ከፈለጉ፣ ኤክስፖርታቸውን ብዙወጥ ማድረግና ጥራቱንም ማሻሻል እንዳለባቸው በማፑቶው ዓቢይ ጉባኤ ላይ በግልጽ ነው የተነገራቸው።


አሁን የቀረበ አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የአውሮጳው ኅብረት የልማት ርዳታ መርሕ የተባ መ ድ ወደተለመው የአሠርቱ ምእት ግብ የሚያቃርብ ሆኖ አይታይም። ስድስት አውሮጳውያን የልማት ድርጅቶችን የሚያጣምረው “አላየንስ ፪ሺ፲፭” የተሰኘው የልማት ድርጅቶቹ ቡድን እንደሚለው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮጳው ኅብረት ዙሪያ ስለ አሠርቱ ምእት የልማት ግቦች አትኩሮቱ እየጎላ ቢገኝም፣ በመርሕና በትግበራ፣ በሃልዮትና በእውነታ፣ በመፈክርና በውጤቱ መካከል ትልቅ ክፍተት ነው የሚታየው። የአውሮጳው ኅብረት ለአሠርቱ ምእት የልማት ግቦች ያለውን አስተዋጽኦ የሚያተኩርበት ጥናት፣ ኅብረቱ የአሠርቱ ምእትን የልማት ግቦች ክትትል በተግባር ማሳየት ነው የሚሳነው ይላል። ስለዚህ፣ የአውሮጳው ኅብረት የልማት መርሕ ግቦቹን ለማስጨበጥ የሚችልበት ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት ዘገባው ያስገነዝባል።

የዓለም መሪዎች በመስከረም ፲፱፻፺፫--ወይም እጎአ በ፪ሺ ዓ.ም.--በተባ መ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተስማሙባቸው የልማት ግቦች፥ እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ--ካሁን ወዲያ ሲታይ በአሥር ዓመታት ውስጥ መሆኑ ነው--ድህነት በግማሽ የሚቀነስበትን፣ የመሠረታዊ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይዘት የሚሻሻልበትን፣ በሽታዎች በቁጥጥር ሥር የሚደረጉበትንና የሚገቱበትን፣ ጠቅላላውም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም የሚዳረስበትን ክንውን የሚመለከቱ ናቸው። በእነዚሁ ግቦች ክትትል ረገድ የተገኘው ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚመጣው ዓመት ፍተሻ እንደሚደረግበት ነው የሚጠበቀው።

የአውሮጳው ኅብረት ሥራ-አስፈጻሚ አካል የሆነው የአውሮጳው ኮሚሲዮን ከአባል-ሀገራቱ ጋር በመተባበር እጅግ ትልቁን የልማት ርዳታ ነው ዝግጁ የሚያደርገው--ማለት ኮሚሲዮኑ እጅግ ትልቁ የልማት ርዳታ ምንጭ ነው። ግ’ን፣ ጥናቱ እንደሚያስረዳው፣ የአውሮጳው ኅብረት ለተባ መ አሠርቱ ምእት የልማት ግቦች እስካሁን ዝግጁ ያደረገው ርዳታ መንማና ሆኖ ነው የሚታየው።

ከጠቅላላው ብሔራዊ ውጤት ነጥብ-፯ በመቶው ለልማት ርዳታ እንዲመደብ ከረዥም ጊዜ በፊት በተገባው ቃል መሠረት፣ የአውሮጳው ኅብረት የርዳታ በጀቱን የሚያሳድግበት የጊዜ ሠሌዳ ይዘረጋ ዘንድ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑት ግብረሠናይ ድርጅቶች አሁን አጥብቀው ነው የሚያሳስቡት። በሌላው በኩል ግን፣ የእነዚሁ ድርጅቶች አስተባባሪ ቡድን “አላየንስ ፪ሺ፲፭” እንደሚለው፣ ለኅብረቱ የልማት ርዳታ አመዳደብ አሁን አንድ እክል ሆኖ የሚታየው፣ የፀጥታ አጠባበቁ ጥያቄ ነው። ይኸውም ችግሩ የልማቱ ጉዳይ ከፀጥታ ጥበቃ ጥያቄዎች ጋር የሚጣበቅበት ሁኔታ ነው። በድህነት አንፃር የሚደረገው ትግል ከፀጥታ ጥበቃ ጥያቄዎች ጋር መወሳሰብ የለበትም፣ ራሱን የቻለ ትኩረት ነው ማግኘት የሚገባው--ድርጅቶቹ እንደሚያስገነዝቡት። በሚደረጁት ሀገሮችም ውስጥ የፖሊስና የጦር ሰራዊቱ ሥልጠና አስፈላጊ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ከልማት ግምጃቤት መወሰድ እንደሌለበት፣ በፀጥታ ጥበቃ እና በአሠርቱ ምእት የልማት ግቦች መካከል ግጭት እንዳይኖር ነው ግብረሠናይ ድርጅቶቹ አጥብቀው የሚያስገነዝቡት።

የአውሮጳው ኮሚሲዮን ደግሞ፣ በፀጥታ ጥያቄና በልማት ርዳታ መካከል ተሳሳሪ ሁኔታ ይታያል፧ ማለት የልማት በጀት ለፀጥታ ዓላማ ይቆነጠራል የሚለውን የግብረሠናይ ድርጅቶቹን ሂስ አይቀበለውም፣ ድርጅቶቹ ለዚሁ አባባላቸው ምክንያት እንደማይታይላቸው ነው ኮሞሲዮኑ የሚያስገነዝበው። ለዚሁ አንድ ማስረጃ ሆኖ የቀረበው፥ የአውሮጳው ኅብረት እጎአ ከ፪ሺ፫ እስከ ፪ሺ፯ የመደበው የልማት ግምጃቤት ነው። በዚሁ የልማት ግምጃቤት አማካይነት፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለሚደረጁት ሀገሮች ትምህርት ማስፋፊያ እና ጤና ጥበቃ በሚሊያርድ ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚሸጋገር ኮሚሲዮኑ ያስገነዝባል።