የአንጎሎ ምርጫና ኤኮኖሚዋ | ኤኮኖሚ | DW | 29.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአንጎሎ ምርጫና ኤኮኖሚዋ

አፍሪቃ ውስጥ በነዳጅ ዘይት አምራችነት ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ትልቅ አገር በሆነችው በአንጎላ ከነገ በስቲያ አርብ ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል።

default

አፍሪቃ ውስጥ በነዳጅ ዘይት አምራችነት ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ትልቅ አገር በሆነችው በአንጎላ ከነገ በስቲያ አርብ ምክርቤታዊና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በምርጫው የፖርቱጋል ቅን አገዛዝ ካበቃ ወዲህ አገሪቱን ሲገዛ የቆየው የአንጎላ ሕዝብ የነጻነት እንስስቃሴ MPLA-ና ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት ባሻገር የበላዩ ሆነው የኖሩት መሪው ፕሬዚደንት ዶሽ ሣንቶሽ አሸናፊ እንደሚሆኑ የሚጠራጠር የለም።

ዶሽ ሣንቶሽ ከኤኩዋቶሪያል ጊኒው ቴኦዶሮ ኦቢያንግ ቀጥለው አፍሪቃ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሥልጣንን የሙጥን ያሉት ሁለተኛው አምባገነን ገዢ ሲሆኑ መንግሥታቸው ሕብረተሰቡንና መገናኛ ዘዴውን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ነው የቆየው። ይሁንና አሁን ከአገሪቱ ወጣት ትውልድ የተወሰነው ክፍል በሁኔታው ለለወጥ ሲነሣ በዓረቡ ዓለም ጸደይ የተቀሰቀሱ ተማሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የመብት ተሟጋቾች ሳይቀር በአደባባይ በመሰለፍ ዶሽ ሣንቶስ ሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ነው።

መንግሥትም ታዲያ በተቃዋሚዎቹ ላይ ጠንካራ ክንዱን መዘርጋቱ አልቀረም። ተቃውሞው የዓረቡን ጸደይ ፈለግ ተከትሉ ባለፈው ዓመት ነበር የጀመረው። ግን እስካሁን ሰፊ የሕዝብ እንቅስቃሴ በመሆን ብዙሃኑን ከጎኑ ሊያሰልፍ አልቻለም። የሆነው ሆኖ በዓለም ላይ በተፈጥሮ ጸጋ ከታደሉት ሃገራት አንዷ የሆነችው አንጎላ ለወጣቱ ትውልድ የተሥፋ ምንጭ ሆና አትገኝም።

በአንጻሩ ስራ አጥነት፣ የከፋ ድህነት፣ ሙስናና ጭቆና ጎልተው የሚታዩት የሕብረተሰቡ መለያ ነጸብራቁ ናቸው። ስለዚህም የሁኔታው አስከፊነት ወጣቱን ሙዚቀኛ ካርቦኖ ካዚሚሮን የመሳሰሉ የኪነት ሰዎች ሳይቀር አደባባይ እንዲወጡ ማስገደዱ አልቀረም።

«ሁላችንም የተቃወሰ መንግሥታዊ የአስተዳደር ዘይቤ ሰለቦች ነን። ለዚህም ነው በሙዚቃ ሙያዬ ሳልወሰን ከሌሎች ወጣቶች ጋር በአደባባይ በመሰለፍ መንግሥትን ለመቃወም የወሰንኩት። እርግጥ መንግሥት ነጻነታችንን ያፍናል። እናም ከመካከላችን የተወሰኑት አንድ ነገር እንዳይሆኑ በጣሙን ነው የምንሰጋው። በመሠረቱ ሰላማዊ ስንሆን ከመንግሥት ሃይል ጋር ግጭት የማድረግ ፍላጎት የለንም። የምንሻው በአጭሩ ፍትህን ነው። ይህ ደግሞ ለሕዝቡ ይገባዋል እንጂ አይበዛበትም»

ነገር ግን በሕዝቡ መደፋፈር መደናገጥ የያዙት የአንጎላ ፖሊስ፣ የጦር ሃይልና የጸጥታ ባልደረቦች የተቃውሞውን መሪዎች አንዴ በገንዘብና በአውቶሞቢል ሽልማት ለመግዛት ሌላ ጊዜም መሸንገሉ ሲያቅት በዛቻና በጉልበት ዕርምጃ ለማስፈራራት ሲጥሩ መታየታቸው አልቀረም። እንግዲህ ትናንት ሰባ ዓመት የሞላቸው አንጋፋ ገዢ በዚህ በገፋ ዕድሜም በቅርቡ ከሥልጣን ገሸሽ ለማለት ሃሣብ ያላቸው አይመስልም። እንዲያውም የምርጫውን ቅስቀሳ ለተመለከተ ፕሬዚደንቱ ዘላለማዊ ሆነው የሚሰማቸው ነው የሚመስለው።

በኤኮኖሚው ሁኔታ ላይ እናተኩርና እርግጥ አንጎላ ከሰላሣ ዓመታት በላይ በዘለቀው በዶሽ ሣንቶሽ አገዛዝ ዘመን ጠቃሚ ዕድገት አድርጋለች። ዛሬ በተለይም በቻይና የታነጹት የባቡር ሃዲዶች፣ አውራ ጎዳናዎች፣ድልድዮችና በርካታ ሕንጻዎች ጥቂትም ቢሆን የእርስበርሱ ጦርነት ዘመን አሻራ ደብዘዝ እያለ እንዲሄድ ለማድረግ ያበቁ ናቸው። ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ ታዲያ MPLA-ና ፕሬዚደንቱ ሕዝቡን የረጅም ጊዜ ሰላምና ዕድገት እንዳጎናጸፉት እየነገሩት ነው።

ሆኖም በግንቢያና በመዋቅራዊ ልማት ላይ የፈሰሰው ታላቅ መዋይለ-ነዋይ አብዛኛውን የጦርነት ጠባሳ በሽፍንም የፖለቲካ ተቺዎችና ተራ ዜጎች በአገሪቱ በሰፈነው ሰፊ ድህነትና የእኩልነት እጦት ምሬታቸውን እየገለጹ ነው። የፊታችን ምርጫ ምንም ያምጣ ምን አብዛኛው ተራ ሕዝብ ብሶቱን መግለጹንና ለተሻለ ኑሮ ለውጥ መሻቱን መቀጠሉ የሚጠበቅ ነው የሚሆነው። አንጎላ በጥቅሉ ሲታይ ባለፈው አሠርተ-ዓመት ጠቃሚ የኤኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን የጀርመኑ የንግድ ጋዜጣ የሃንደልስብላት ወኪል ቮልፍጋንግ ድሬክስለር እንደሚሉት በመሃሉ አቆልቁሎ የነበረው ዕድገት በዚህ ዓመት መልሶ ከፍ እንደሚልም የሚጠበቅ ነው።

«የወቅቱ የአንጎላ የኤኮኖሚ ይዞታ ብዙም የከፋ አይደለም ለማለት ይቻላል። ከሶሥትና አራት ዓመታት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር እርግጥ ጥቂት ደከም ማለቱ አልቀረም። አንጎላ በጎርጎሮሳውያኑ ዓመታት 2004 እና 2008 መካከል በአፍሪቃ ከፍተኛውን የኤኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡ ተሳክቶላት ነበር። ይህም በአማካይ 17 ከመቶ ዕድገት መሆኑ ነው። በ 2007 እንዲያውም 22 ከመቶ ደርሶ ነበር። ሆኖም ከ 2008 ወዲህ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በመውደቁ የተነሣ ዕድገቱ እያቆለቆለ ሲመጣ ወደ ሶሥት በመቶ እስከመውረድ ደርሷል። በሌላ በኩል በዚህ ዓመት ከ 10 እስከ 12 በመቶ ዕድገት እንደሚገኝ ነው የሚጠበቀው። ይህም የሚያሳየው የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ምን ያህል በጥሬ ዕቃ ዋጋ ላይ ጥገኛ እንደሆነ ነው። አንድ ነገር ልጨምር፤ መንግሥት እርግጥ አገሪቱ ዘመናዊ ዕርምጃ እንድታሳይ አድርጓል። ዋና ከተማይቱ ሉዋንዳ ውስጥ ዘመናዊ የቢሮ ሕንጻዎች፣ ሆቴሎች፣ አፓርትመንቶችና መንገዶች በሰፊው ተሰርተዋል። ጥሩ ዕርምጃ አለ። ግን ችግሩ ገንዘቡ በከፍተኛው መደብ ዕጅ የተወሰነ መሆኑ ነው»

እርግጥም የዕድገቱ ተጠቃሚዎች የአገሪቱ ገዢዎችና ጥቂት አበሮቻቸው ሲሆኑ ለብዙሃኑ የተረፈ ብዙም ነገር የለም። ይህ እንግዲህ በአፍሪቃ የተለመደው የዕድገት ዘይቤ መሆኑ ነው። ጥቂቶች ይካብታሉ፤ ብዙሃኑ ግን የበይ ተመልካች ከመሆን ባሻገር የሚቀራቸው ነገር የለም። የጥቂቶች ዕድገት፤ የብዙዎች ድቀት ቢባል ማጋነን አይሆንም።

«ችግሩ እዚህ ላይ ነው። በአፍሪቃ አዘውትሮ እንደተለመደው ሃብቱ መንግሥትና ከርሱ ጋር የተሳሰረው ከፍተኛ የሕብረተሰብ ቡድን እንዳሻው የሚመዘብረው መሆኑ ነው። አንጎላ ውስጥ ሙስና እጅግ ከፍተኛ ነው። ከነዳጅ ዘይት የሚገኘው በሚሊያርድ የሚቆጠር ገቢ ማንም ተጠያቂ ሳይኖርበት ነው የሚሰወረው። የሕዝቡ አማካይ የሕይወት ዘመን በ 50 ዓመት የተወሰነ ሲሆን አገሪቱ በዓለም ላይ ሕጻናት በአጭር ዕድሜ ከሚቀጩባቸው ሃገራት አንዷ ናት። ሩቡ የአገሪቱ ሕዝብ ደግሞ መሃይም ነው። ለግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ታስባ የታነጸችውን ዋና ከተማ ሉዋንዳን ዛሬ ብንመለከት ከጠቅላላው ሃያ ሚሊዮን የአንጎላ ሕዝብ አምሥት ሚሊዮኑ የሚኖረው በዚያ ነው። ከዚሁ 90 በመቶው ደግሞ በከፋ ድህነት ሕይወቱን ይገፋል። ኑሮውም አንጎላ ሚስማር ሳይቀር ሁሉንም ነገር ከውጭ የምታስገባ በመሆኗ እጅግ ውድ ነው። ከጥቂቶቹ ባለጸጎች በስተቀር የሚችለው የለም። ሉዋንዳ ከቶኪዮ ቀጥላ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ኑሮ የተወደደባት ከተማ መሆኗ ማስገረሙ አይቀርም»

በአገሪቱ በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድርን ያህል እየሆነ መሄዱ የተሰወረ አይደለም። ዋና ከተማይቱ በአንድ በኩል በደመቁ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች፣ አሸብራቂ ውድ መደብሮችና ምግብቤቶች ስትጥለቀለቅ በሌላ በኩል ዳር ዳሩን የተኮለኮለው የቆርቆሮ ደሳሳ ጎጆ ብዛት ደግሞ ብዙ ይናገራል። ገዢው ፓርቲ በበኩሉ ድህነትን በሰፊው በመቀነስ ማሕበራዊ መሻሻል እንዲኖር አድርጌያለሁ ባይ ነው።

የድህነቱ አስከፊነት ግን ለዓይን የተሰወረ አይደለም። አንጎላ እንግዲህ ይህን ሁኔታ ለማሻሻል መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋታል። ግን ይህ ከሰሞኑ ምርጫ ሊጠበቅ ይችላል ወይ? እንደ ኬፕታውኑ የጀርመን ጋዜጣ ወኪል እንደ ቮልፍጋንግ ድሬክስለር ከሆነ ብዙ ተሥፋ መጣል የሚያዳግት ነገር ነው።

«ብዙ ለመጠበቅ አይቻልም በመሠረቱ። በአንጎላ ሲቪል ሕብረተሰብ ውስጥ ነጻነትን የሚጠይቀው ድምጽ ይበልጥ እየተበራከተ እንደሚሄድ ተሥፋ ማድረግ ነው የሚቻለው። ለምሳሌ መንግሥትን ተቃውመው አደባባይ የወጡ የሃይል ዕርምጃ እንዳይወሰድባቸው። በአሥር ከመቶ ድጋፍ የተወሰነው ተቃዋሚ ወገን የቀድሞው ዩኒታ የዓመጽ ቡድን እንደሚጠናከር ተሥፋ ማድረግ ይቻላል። ባለፈው የ 2008 ዓመተ-ምሕረት ምርጫ መንግሥት በ82 ከመቶ ድምጽ ነበር ያሸነፈው። ገዢው ፓርቲ በአሁኑም ምርጫ አሸናፊ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ግን ምናልባት ዩኒታ ድጋፉን ከ 10 ወደ 15 በመቶ ከፍ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። እርግጥ ይህ በመንግሥት ላይ የለውጥ ግፊት ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ ተቃዋሚ ወገን ለመሆን አያበቃም። ሆኖም መንግሥት ጥቂት ግፈት የሚያደርግበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ አገሪቱን ምናልባት ወደ ጠነከረ ዴሞክራሲ የሚመራ ትልቅ ዕርምጃ በሆነ»

ግን የአፍሪቃ የምርጫ ልምዶች ለተሥፋ መንስዔ የሚሆኑ አይደሉም። ስለዚህም የአንጎላ ሕዝብ ድህነትና መበዝበዝ ምናልባትም ባለበት ይቀጥላል። የአገሪቱ ኤኮኖሚ በእጥፍ አደገ እየተባለ እንደተለመደው ቢለፈፍ ወደፊትም የገዢዎች መመጻደቂያ ከመሆን አልፎ ለብዙሃኑ አንዳች ትርጉም አይኖረውም። መፍትሄው በአንጎላም ቢሆን ምዝበራን አቁሞ በአገሪቱ የተፈጥሮ ጸጋ የሚገኘውን ገቢ ለማሕበራዊ ዕድገት በስራ ላይ ማዋል ነው። ይህ ካልሆነ ሰንጠረዥ የዋሸውን አደባባይ እየገለጸው ይቀጥላል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 29.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15y9y
 • ቀን 29.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15y9y