የአንጎላ ነዳጅ ዘይት | አንጎላ- ነዳጅ ዘይት | DW | 05.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አንጎላ- ነዳጅ ዘይት

የአንጎላ ነዳጅ ዘይት

በአንጎላ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ክምችት ይገኛል። አንጎላ የነዳጅ ዘይት ክምችትዋን ለመጀመርያ ግዜ ያገኘችዉ በ1960ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ነዉ። ከጎርጎረሳዉያኑ 1975 እስከ 2002 ዓ,ም ድረስ በአንጎላ የነበረዉ የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ ሀገሪቱ ያላትን የነዳጅ ዘይት ለማዉጣት የተሻለ ዘዴ ተፈጠረላት።

ዛሪ አንጎላ ከናይጀርያ ቀጥላ በአፍሪቃ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገር ናት። ያም ሆኖ ዛሪም 40 በመቶዉ ህዝቧ በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢን በማግኝት ይኖራል። ታድያ ሀገሪቷ ከጥሪ ሐብቷ የምታገኘዉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ወዴት እየገባ ነዉ? የዶቼ ቬለዋ ሪናተ ክሪገር መልስ ለማግኘት አንጎላ ዉስጥ የሳምንታት ቆይታ አድርጋ ነበር። ሪናተ ጉዞዋን የጀመረችዉ የዴሞክራቲክ ኮንጎ አጎራባች ከሆነችዉ በሰሜናዊ አንጎላ ከምትገኘዉ ከሶዮ ከተማ በመነሳት ነዉ። ዘገባዉን አዜብ ታደሰ ሰብሰብ አድርጋ እንዲህ ታቀርበዋለች።

ታክሲ ነጅዉ ሉሲያኖ ንዞምቦ መንገድ ዳር ላይ ባለዉ ቀላ ያለ አሸዋ ላይ በመኪና ቁልፉ ሶስት ቀለበቶችን አገጣጥሞ ሳለና ከላዩ ላይ እንደገና አሰመረበት። የ32 ዓመቱ ታክሲ ነጂ በአንድ እጁ የፀሃይዋን ጨረር ከአይኑ እየከለለ በሁለተኛ እጁ መሪት ላይ የሳለዉን ምልክት በማሳየት ማስረዳቱን ጀመረ። «ይሄ ካቢንዳ ነዉ። ይሄ ሶዮ ነዉ። ይሄ ደግሞ ሉዋንዳ ነዉ። የሉዋንዳዉ እና የካቢንዳዉ የነዳጅ ማመላለሻ ቧንቧ ሶዮ ላይ ይገናኛል። የነዳጅ ማመላለሻዎቹ ቧንቧዎች ከመሪት ወደ ባህሩ አቅጣጫ እንዲያልፉ ሆነዉ የተሰሩ ሲሆን ከባህሩ ወደ ሶዮ ጋዝን ለማመላለሻነት ጥቅም ላይ ዉለዋል። እንደ ሉቺያኖ ከሶዮስ የባህር ዳርቻ ወደ አትላንቲክ ዉቅያኖስ የተዘረጋዉ የጋዝ ማመላለሻ ቧንቧ እስከ 1700 ሜትር ጥልቀት ካላቸዉ ቦታዎች ነዉ ጋዙ የሚመረተዉ። የኤሌትሪክ ስራ አዋቂዉ ሉችያኖ ከጎአ 2010 እስከ 2011 ዓ,ም የጋዝ ማመላለሻዉ ቧንቧ በአካባቢዉ ላይ ሲዘረጋ አንጎላ LNG በተሰኘ የፈሳሽ ጋዝ ኩባንያ ዉስጥ በኤሌትሪክ ሰራተኛነት ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። እንደ ነዳጅ ዘይት አምራች ሀገሮች ድርጅት OPEC ገለጻ ከአፍሪቃ አህጉር አንጎላ ከናይጀርያ ቀጥላ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት አምራች አገር ናት። በተጨማሪ አንጎላ 366 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ሃብት አላት። ከሉችያኖ ጋር ወደ ሶዮ LNG አንጎላ ወደተባለዉ ኩባንያ ተጓዝኩ። የዚህ ድርጅት ግንባታ የጀመረዉ እንደ ጎ በ2008ዓ,ም ነበር። 240 የእግር ኳስ ሜዳን የሚህል ስፋት ያለዉ የኩባንያዉ ቅጽር ግቢ የተወሳሰበ ቧንቧ የተዘረጋበት ሰፊ ክልል ላይ የሚገኝ ነዉ። LNG ኩባንያ ቼቭሮን የተሰኘ በርካታ አለማቀፍ የሃይል ማምረቻ ኩባንያዎችን ያካተተ ግዙፍ ድርጅት ነዉ። እንደ እቅዱ ይህ ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ኩባንያ በጎ 2012 ዓ,ም ስራዉን የሚጀምር እና በዓመት 5,2 ቢሊዮን ቶን ፈሳሽ ነዳጅ ጋዝ ማምረት ነበረበት። በዚህም አንጎላ ነዳጅ ፈሳሽ ጋዝን ለዉጭ ሽያጭ ከሚያቀርቡ የአፍሪቃ አገራት አንዷም ያደርጋት ነበር። በአፍሪቃ አህጉር በአጠቃላይ ስምንት ፈሳሽ ጋዝ አምራች ኩባንያዎች ብቻ መኖራቸዉ ይታወቃል። ግን በሶዮ የአንጎላ ከተማ የሚገኘዉ አምራች ኩባንያ እስካሁን በሙከራ ስራ ላይ ከመሆኑ በስተቀር፤ ምርት ማቅረብ አለማቅረቡ በግልፅ አይነገርም።

በዚህም ምክንያት ኩባንያዉን ለመጎብኘት ማንኛዉም ሰዉ ፈቃድን አያገኝም። በአንድ የመረጃ መግለጫ ካርድ ላይ ተፅፎ የሚታየዊ በካይ ጋዝን ለመቀነስ አንጎላ አዲስ ንጹህ የሃይል ማመንጫ ለማግኘት በመስራት ላይ መሆንዋን የሚያሳይ መረጃ ብቻ ለአንባብያን ተገልጾአል። በርግጥ እዉነታዉ ይህን ዓላማ ለማሳካት ከሚደረገዉ ጥረት እጅግ የራቀ መሆኑ ነዉ። አንጎላ ዉስጥ በብዙ ቦታዎች እንደ ቀድሞዉ ግዜ ሁሉ የነዳጅ ዘይትን ለማዉጣት በሚደረገዉ እርምጃ የሚያፈተልኩ መርዘኛ ጋዞች እንዲሁ እንደችቦ እንዲቀጣጠሉ ይተዋሉ። በሶዮ በአንድ የመንገድ ዳርቻ አንድ ሜትር ርዝመት ያላቸዉ ሁለት ሰፋፊ ረጃጅም ቶቦዎች ነበልባል እሳትን ሲተፉና፤ ነበልባሉ የሚፈነጥቀዉ ብርሃን እስከ ሰማይ ድረስ ሲያበራ ይታያል። የመንገድ መብራት አልፎ አልፎ በሚታይበት በዚህ ቦታ ታድያ ይህ ነበልባል እንደ መንገድ መብራትም ማገልገል መጀመሩን ታክሲ ነጅዉ ሉችያኖ ይናገራል። «ለሊት መንግዱ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ነዉ። በጣም ጥቅጥቅ ያለጨለማ ከመሆኑ የተነሳ የሆነ ሰዉ መንገድ ሲያቋርጥ እንኳ አይታይም,,,ግን ሙሉ ከተማዉ በነዳጅ ዘይት የተሞላ ነዉ። ይህ ነዳጅ ዘይት ከሃብት ይልቅ ድህነትን ነዉ ያመጣብን» ሉችያኖ የተቆፋፈረዉን የከተማዉን መንገድ እያሳበረ ታክሲዉን መንዳቱን ቀጠለ። በ1980ዎቹ አመታት በአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነት በነበረበት ወቅት ሉችያኖ ከ 12 የቤተሰቡ አባላት ጋር ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተሰዶአል። ከዝያም በአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነቱ እንዳበቃ ነዉ ወደ ሶዮ ከተማ ከቤተሰቡ ጋር የተመለሰዉ። በሰሜናዊ አንጎላ ያለዉ የጥሪ ሐብት ምርት እኔን ብቻ ሳይሆን በርካቶችን ተስፋ ሰጥቶ ወደ እዚህ ቦታ እንዲመጡ ጋብዞአል ሲል ሉችያኖ ይናገራል። ሉችያኖ በሶዮ የነዳጅ ማምረቻ ኩባንያዉ ሲገነባ ስራን አገኘ። ግን በጎ 2011ዓ,ም የነዳጅ ዘይቱ ቧንቧ ተዘርግቶ እንዳለቀ ስራ አጥ ሆንዋል። ከዝያም ነዉ ሉችያኖ ታክሲ በመንዳት በቀን እስከ 150 ዶላር እያገኘ እሱንና ቤተሰቡን ማስተዳደሩን የቀጠለዉ። በ LNG ፕሮዤ ዉስጥ በሚሰራበት ወቅት ግን ሉችያኖ በወር ወደ 330 ዶላር ያገኝ ነበር። ሉችያኖ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ እምነት በማጣቱ በአንጎላ በ2012 ዓ,ም በተደረገዉ ምርጫ ላይ አለመሳተፉን ይናገራል። « በአንጎላ LNG ኩባንያ ካለ ለ አንጎላ ጥሩ ነዉ ይላሉ። ግን የዚህ ተጠቃሚዎቹ ሌሎች ናቸዉ። ለዚህ ነዉ እኛ አንጎላዉያን የተሰደድነዉ» የአንጎላን የነዳጅ ዘይት ሐብት ማየት የሚፈልግ ወደ ሉዋንዳ መጉብኘት ይኖርበታል። 5 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የሚገኙባት ሉዋንዳ እጅግ ዉድ ከሚባሉት የዓለም ከተሞች አንዷ ናት። በሉዋንዳ አንድ የመኖርያ ቤት ለመከራየት በወር እስከ 5000 ዶላር ይጠይቃል። ለምግብም ቢሆን የሚከፈለዉ ገንዘብ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰሃን ሾርባ እስከ አስር ዶላር ያወጣል።

በሰሜናዊ ምዕራብ ሉዋንዳ ባህር ዳርቻ የሚገኘዉ አቪኒዳ ማርጊናል ጎዳና በመዲናዋ ታዋቂና የተለያዩ ትላልቅ ድርጅቶች የሚገኙት ነዉ። ትላልቅ ኩባንያዎች ባንኮች እንዲሁም በጎዳናዉ አቋራች መንገድ ላይ SONANGOL የተሰኘዉ የአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ዋና መቀመጫ ይገኛል። እንዲሁ በዚሁ ጎዳና የሀገሪቷ ብሄራዊ ባንክ ይገኛል። አቪኒዳ ማርጊናል መንገድ አስፓልት የለበሰ ሰፊና ንፁህ መስዕብ ያለዉ ሲሆን በጎዳናዉ ላይ የሚታዩት መኪናዎች እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ ብቻ ናቸዉ። ታድያ ይህ አዲሱ የአንጎላ ሐብት መግለጫ ምልክት ሆንዋል። በአሁኑ ግዜ መንግስት መንግድ ስራን በማስፋፋት ሌሎች ከተሞችን ማገናኘት ጀምሮአል ። ቀደም ሲል አንጎላን በሀገር አቋራጭ ጎዞዎች ማቋረጥ የማይታሰብ ነበር። በመዲናዋ ታዋቂ የሆነዉ አቪኒዳ ማርጊናል ጎዳና አጠገብ ያሉ መንገዶች በመቆፋፈራቸዉ መኪኖች እጅግ በዝቅተኛ ፍጥነት ነዉ የሚጓዙት። በዚህም ከፍተኛ የትራፊክ ጭንቅንቅ ይታያል። የመንገድ መብራቶችም ባለመስራታቸዉ ለአንድ ሁለት ኪሎሜትር ርቀት መንገድ ግማሽ ሰዓት መጓዝን ይጠይቃል። በሉዋንዳ መሃል ከተማ VILA ALICE አካባቢ OPEN SOCITY ANGOLA የተሰኘዉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ቢሮ ይገኛል። መንግስት የሚያገኘዉን ነዳጅ ዘይት 98 በመቶ ለዉጭ ገበያ ያቀርባል። ግን ህዝቡ ከዚህ ገቢ የሚያገኘዉ ምንም ጥቅም የለም ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ዋና ሊቀመንበር ኤልያስ ኢዛክ ይከሳሉ « የጥናት መዘርዝሩ እንደሚያሳየዉ በአንጎላ በነዳጅ ዘይት ምርቱ ዘርፍ ተሰማርተዉ የሚገኙት ሰራተኞች 0,5 በመቶ ናቸዉ። እዚህ የሚታየዉ ነገር ሁሉ ተፃራሪ ነዉ። እንደሚታወቀዉ ኤኮኖሚያዊ እድገት አለ፤ እኛም ሃብት እያካበትን እና በእርስ በርሱ ጦርነት ግዜ የፈረሰዉን መንገድ እየገነባን ብቻ ነዉ ያለነዉ፤ በርግጥ ያም ቢሆን አስፈላጊ ነዉ። ግን ይህ የኤሌትሪክ አገልግሎት፤ የመጠጥ ዉሃ እና የንጽህና ጉዳዮች ለሌለዉ ነዋሪ ማህበረሰባዊ ህይወት አኗኗሩን አያሻሽልለትም » በጎ2012 ዓ,ም የተመድ ባወጣዉ ዘገባ መሰረት በአንጎላ 37 በመቶዉ ህዝብ በቀን ከአንድ ዶላር በታች በማግኘት በድህነት መኖሩን መንግስት ዘግቦአል። በ2000 ዓ,ም ይህ አሃዝ 54 በመቶ እንደነበር እና የደሃዉ ቁጥር በአሁኑ ሰዓት በአንድ ሶስተኛ መቀነሱን መንግስት ባወጣዉ ዘገባ በማነፃፀር ያሰምርበታል። ሁኔታዉ የተሻሻለ ቢሆንም ከሀገሪቱ አቅም ጋር ሲነጻጸር፤ የድሃዉ ቁጥር የበልጥ መቀነስ ይችል ነበር። በሌላ በኩል የሀገሪቱ መዲና ከመጠን ባለፈ መልኩ እድገት ይታይበታል። የዓለም ባንክ ባቀረበዉ ዘገባዉ የሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት በጎ,አ 2000 ዓ,ም 660 ዶላር ነበር፤ 2011 ደግሞ 5,150 ዶላር ሆንዋል። በዚህ ዓመታት ዉስጥ የሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት በስምንት እጥፍ ጨምሮአል። ምጣኔ ሐብቱ ማደጉ የሚስተዋለዉ ድሃዉ ህዝብ ምን ያህል ጥቅምን ያላገኘበት፤ ሃብታሙ ግን ይበልጥ ሀብት የሰበሰበት የተሽቆጠቆጠበት በመሆኑ ብቻ ነዉ። የህግ አዋቂዉ አንጎላዊ ኖርበርቶ ጋርሲአ፤ በአንጎላ የሚታየዉ ድህነት ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ ሊቀረፍ አይችልም ሲሉ በ2012 ዓ,ም በሀገሪቱ ምርጫ በተካሄደ ግዜ ለዶቼ ቬለ ተናግረዉ ነበር።

« የሀገሪቱን ሐብት በተስተካከለ መንገድ ማከፋፈል የሚቻለዉ አዳዲስ የስራ ቦታዎችን በመክፈት። ይህ ደግሞ ሀገሪቷ የምታራምደዉን መረሃ-ግብር አይጎትተዉም። የሚያሳዝነዉ በአንጎላ በጣም ያልተስተካከለ የሥርዓተ ትምህርት ሁኔታ ነዉ ያለን። 34 በመቶዉ ህዝቧ ያልተማረ ነዉ፤ ያ ደግሞ የሀገሪቱ ያላትን ሃብት በተመጣጠነ መልክ ለማከፍፈል ከባድ ያደርገዋል። በዚህም መክንያት መንግስት ስልጠና እና ትምህርት ለህዝቡ በማቅረብ የስራ ቦታን እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርበታል።» በሀገሪትዋ የሚታየዉን ድህነት እና ረሃብ በጥብቅ ለመዋጋት መንግስት እስከ መጭዉ 2017 ዓ,ም በአዲስ መረሃ-ግብር እቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ ንድፍ አዉጥቶአል። ከእቅዶቹ መካከል ለነዋሪዉ የኤሌትሪክ ሃይልና፤ የንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦትን ማሻሻል ይገኝበታል። ይህን አቅርቦት በመዲና ሉዋንዳ ካዜንጋ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችም እየጠበቁት ያለ ጉዳይ ነዉ። ካዜንጋ መንደር በሉዋንዳ በርካታ ነዋሪዎችን ያቀፈ ጥቅጥቅ ያለ የመኖርያ ቤቶች የሚነኝበት የድሆች መንደር ነዉ። የአካባቢዉ መንገዶች አስፋልት አልተነጠፈባቸዉም፤ ዝናብ በዘነበ ግዜ የካዜንጋ መንገዶች በፍሳሽ ዉሃ ችቃ እና በማጥ ተዘፍቀዉ ነዉ የሚታዩት። በልዋንዳ ቀበሌዎች ዉስጥ በቅስና የሚያገለግሉት Eruicleurival Vasco ካዜንጋ ኤሌትሪክም በቀን ዉስጥ ከመጣ ለአንድ ሁለት ሰዓታት ብቻ ነዉ ሲሉ ይናገራሉ። «መብራት ለአንድ ወር ያህል አላገኘንም፤ ዛሪ መቶ ነበር ግን ተመልሶ ጠፍቶአል። የአገሪቱ የመብራት ሃይል ሰራተኞች የመብራት ማመንጫ የዉሃ ግድቡ በመድረቁ የመብራት ችግር መከሰቱን ይነግሩናል። እነሱ ስለጉዳዩ ስለሚያዉቁ፤ ያሉንን በግድ ማመን አለብን።» ከሉዋንዳ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ የቪያና ከተማ ነዋሪዎች የመንግስት እርዳታን በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። ነዋሪዎቹ በመጀመርያ ይኖሩ የነበሩት ከባህር ጋር ከተገኛኘዉ ሉዋንዳ ከተማን ከሚያዋስነዉ አካባቢ ላይ ነበር። መንግስት ይህን ቦታ በሉዋንዳ ሰማይጠቀስ ህንፃዎች ከሚገኙበት ከአቪኒዳ ማርጊናል ጎዳና ጋር በማገናኘት አዲስ ግንባታን መስራት ስለፈለገ በ 2009 ዓ,ም ቦታዉ ላይ ይኖሩ የነበሩ ሰዎችን በግድ እንዲፈናቀሉ አድርጎዋል። ከዚህ ግዜ ጀምሮ እነዚህ ቤት አልባ ሰዎች በቪያና አካባቢ በቆርቆሮ ትናንሽ ዛኒጋባ መጠለያን ሰርተዉ መኖር ጀምረዋል። ከቪያና፤ ከተማ ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘዉ በኪላምባ ከተማ ዉስጥ በሺዎች የሚቆጠር ባዶ የመኖርያ ህንጻዎች ይገኛሉ። እዝያ ከሚገኙት ከሶስት ሽህ የመኖርያ ህንጻዎች መካከል እስካሁን 220 መኖርያ ቤቶች ብቻ መሸጣቸዉ ተጠቅሶአል።

በኪላምባ የሚገኘዉ ይህ አዲስ የመኖርያ ህንጻ በ2008 ዓ,ም በአንጎላ ምርጫ በተካሄደ ግዜ ፕሪዝደንት ዶሽ ሳንቶስ የመኖርያ ቤት ለነዋሪዉ እንደሚሰሩ በገቡትን ቃል መሰረት የተገነባ ነዉ። ዶሽ ሳንቶስ በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት የአንጎላ ህዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዛዉ የሚችል አንድ ሚሊዮን መኖርያ ቤት እሰራለሁ ሲሉ ቃል በገቡት መሰረት የተሰራ መሆኑ ተነግሮአል። ግን በኪላምባ አንድ የመኖርያ ህንጻ ዋጋ ከ90,000 እስከ 150,000 ዶላር ይሸጣል። አብዛኛዉ አንጎላ ነዋሪ ደግሞ ይህን ዋጋ ሊቋቋመዉ አልቻለም። «ኪላምባ ለማን ነዉ የተገነባዉ? ቤት መስራት ለሚችሉ ገንዘብ ላላቸዉ ሰዎች ነዉ የተሰራዉ። በአንጎላ በአብዛኛዉ ያለዉ የመኖርያ ቤት ግን እጅግ ድህነት የሚታይበት ጣርያዉ የተበሳሳ መብራት ዉሃ የሌለዉ ነዉ። አብዛኛዉ ህዝብ በዚህ ደረጃ ነዉ የሚኖረዉ። መንግስትም ብዙ ግዜ ይህን የደሃዉን መኖርያ ነዉ እያፈረሰበት ያለዉ። ሃብታሞች ላይ ምንም የሚደርስ ነገር የለም። ደሃዉ ግን ያለምንም መተዳደርያ መንገድ ላይ እየተጣለ ነዉ። በፖለቲካዉ ረገድ ይህ ሃላፊነት የጎደለዉ ስራ ነዉ። ደሃዉ በህገ ወጥ መኖርያ ቤቱን ቢሰራ ተጠያቂዉ የከተማ መስረታ መዋቅር የሌለዉ እራሱ መንግስት ነዉ።» በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም የአንጎላ ኤኮኖሚ በ7 በመቶ አድጓል። ባለፉት አመታት እንደዉም የኤኮኖሚዉ እድገት እስከ 20 በመቶ ማደጉ ነበር የሚነገረዉ። ይህ የእድገት የአደጉት ሀገሮች እንኳ የሚያልሙት የእድገት መግለጫ አሃዝ ነዉ። የኤኮነሚ ምሁሩ ፈርናዶ ሄቶር የአንጎላ የምጣኔ ሃብት እድገት የተገኘዉ ከነዳጅ ዘይት ምርቱ ዘርፍ ነዉ ይላሉ ። የዚህ እድገት ተጠቃሚዉም ፕሪዚደንት ዶሽ ሳንቶስ እና ጥቂቶች ናቸዉ። ዶሽ ሳንቶስ ስልጣንናቸዉን ጨብጠዉ ሀገሪቷን ለ33 ኛ ዓመት በመምራት ላይ ይገኛሉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ነሃሴ ወር በአንጎላ ለመጀመርያ ግዜ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ ተካሂዶ፤ በምክር ቤት በኩል ዶሽ ሳንቶስ ለመመረጥ በቅተዋል። «ከስድስት የማይበልጡ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸዉ ከ 80 እስከ 90 በመቶ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ይዘዉ ይገኛሉ። አገሪቱን የሚመራዉ የ MPLA ፓርቲም በጉልበት ስልጣኑን ይዞና ማህበረሰቡን በሱ ላይ ጥገኛ አድርጎ ይገኛል። በአንጎላ የ MPLA ፓርቲ ከፍተኛ ደረጃ የበላይነት አሳድሮ ይገኛል። በፊናንስ፤ በኢኮኖሚ እና በማህበረሰባዊ ሁኔታዎችም እንዲሁ። ለምሳሌ የአገሪቱን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ዳኛ በእጩነት ያቀረቡት የአገሪቱ ፕሪዝደንት ናቸዉ።» በአንጎላ የዝምድና ጥቅቅም፤ እና ሙስናን በተመለከተ መንግስት በየግዜዉ በዓለማቀፍ ደረጃ ነቀፊታ ይደርስባታል። ለምሳሌ ሶናአንጎል የተሰኘዉ ሀገሪቱ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ከ2007 እስከ 2011 ዓ,ም ያስገኘዉ ወደ 32 ቢሊዮን ዶላር ወዴት ደረሰ? እንደ ዓለም ባንክ ፤ይህ ገንዘብ በይፋ ከቀረበዉ የወጭ ገቢ ሰንጠረዥ ላይ አይታይም። መንግስት በበኩሉ ገንዘቡን በሀገሪቱ ዉስጥ ለተደረጉ የመሰረተ ልማት ፕሮጄዎች መዋሉን ይገልጻል። በርግጥ ለየትኛዉ ዘርፍ ተብሎ ለሚቀርብለት ጥያቄ ግን መልስ የለዉም። በአንጎላ በ2012 ዓ,ም በተደረገዉ ምርጫ UNITA የተሰኘዉ በሀገሪቱ ትልቁ የተቃዋሚ ቡድን 19 በመቶ ድምጽን በማግኘት ሁለተኛዉ ጠንካራ የሀገሪቷ ፓርቲ ሆንዋል። ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያለዉ MPLA ፓርቲ 70 በመቶ የመራጭ ድምጽን በማግኘት ቀዳሚነቱን ስፍራ መያዙ ይታወቃል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች MPLA ን በመንቀፍ መራጭን የማግኘቱ እንቅስቃሴ ቀላል አለመሆኑን ይገልጻሉ። የ UNITA ፓርቲ ሊቀመንበር ኢዛክ ሳማኩቫ እንደሚሉት፤

«እኛ ሃሳባችንን የምንገልጽበት ክፍት መንቀሳቀሻ ቦታን አላገኘንም። የአገሪቱ ህግ በሃሳብ ደረጃ እንደሚያሳየዉ መድብለ ፓርቲ አራማጅ መሆናችን ነዉ። ግን የሀገሪቱ መንግስት የሚያራምደዉ የአንድ ፓርቲ አሰራርን ነዉ። እንደሚታወቀዉ ለተለያዩ ሃሳቦችና ክፍት ቦታ እንዳለ ነዉ። ግን አንጎላ ዉስጥ የአንድ ሰዉዪ ፍላጎት ብቻ ነዉ እየተሟላ ያለዉ» ጉዞአችንን ወደ ጀመርንበት ወደ ሰሜናዊዋ አንጎላ ወደ ሶዮ ከተማ እንመለስ። ታክሲ ነጅዉ ሉችያኖ አዲስ የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ ቧንቧን እያሳየ የሀገሪቱ ጥሪ ሐብት ብዙ ነገሮችን እንድናደርግ እድል ቢፈጥርልንም፤ ስለ አገሪቷ መጻዔ ዕድል ስጋት ይዞኛል ሲል ይናገራል።«ምናልባት አንድ ቀን በአንጎላ ይህ የነዳጅ ዘይት ያለቀ እንደሆነ፤ ምንም ነገር አይኖረንም። አሁን ያለን አንድዪ ሃብታችን የነዳጅ ዘይትና የአልማዝ ጥሪ ሃብታችን ብቻ ነዉ» እንደ ምሁራን ገለጻና ትንበያ አንጎላ ከ 20 -30 ዓመታት በኋላ ያላት የነዳጅ ዘይት ሃብት ተሟጦ ያልቃል።

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

DW.COM