የአንጎላ ተቃዋሚዎች እና የመንግሥቱ ጥጥር ርምጃ | አፍሪቃ | DW | 27.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአንጎላ ተቃዋሚዎች እና የመንግሥቱ ጥጥር ርምጃ

በአንጎላ በፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ አንፃር ተቃውሞ ያሰሙ 13 ወጣቶች ካለፈው ሳምንት ወዲህ እስር ቤት ይገኛሉ። ይህ ሀያ ዓመት እንኳን ባልሞላቸው ወጣት የመብት ተሟጋቾች ላይ የተወሰደው ርምጃ ብርቱ ተቃውሞ ቀስቅሶዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:30

የአንጎላ ተቃዋሚዎች እና የመንግሥቱ ጥጥር ርምጃ

ርምጃው የአንጎላ መንግሥት ምን ያህል በአንፃሩ ትችት በሚሰነዝሩ እና ተቃውሞ በሚያካሂዱ ወገኖች ላይ በየቀኑ እስራትን የመሰለ ኃይለኛ ርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን በግልጽ የሚያሳይ ሆኖዋል። የአንጎላ ዓብዮታዊ ንቅናቄ ጭምር የሚጠቃለልባቸው የመብት ተሟጋች ቡድኖች የአንጎላ ፖሊስ በመዲናይቱ ሉዋንዳ ያሰራቸው ሰላማዊ ወጣቶች ቁጥር ወደ ሀያ እንደሚጠጋ በማመልከት ርምጃውን በጥብቅ ነቅፈዋል።

የመታሰር እጣ የገጠማቸው ወጣቶች ቤተሰቦች እና ወዳጆች በሉዋንዳ በሚገኘው የአንጎላ ፖሊስ ዋና ጽሕፈት ቤት ደጃፍ በየቀኑ በርምጃው አንፃር ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል። በእስር የሚገኙት ልጆቻቸውን ማየት መጎብኘት ካልቻሉት መካከል በአንጎላ ታዋቂው የተቃውሞ ቡድን አባል የሆነው ፣ ካሁን ቀደም ፀረ ፕሬዚደንቱ ቲ - ሸርቶች በማተሙ በ2013 ዓም ሁለት ወራት ታስሮ የነበረው የማኑዌል ኒቶ አልቬስ እናት ወይዘሮ ዳሊያ ቺቮንዴ የእስራቱ ተግባር ተገቢ ያልሆነ ነው ሲሉ ተችተዋል።

« ፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ በሀገሪቱ የሽብር መንግሥት በማቋቋም በሕዝቡ ዘንድ ፍርሀት ለማስፋፋት ይፈልጋሉ። አሁን ወህኒ የሚገኙት ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ የወጡ የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ሲቭሎች ናቸው። ያልገባኝ ጉዳይ፣ እንዴት አንጎላን የመሰለ ኃያል መንግሥት እነዚህን ሕፃናት ሊፈራ ይችላል። ለምንስ እነዚህን ወጣቶች አስተያየታቸውን በነጻ እንዳይገልጹ ለማፈን ይሞክራል? »

የድምፃዊው ምባንዛ ሀምዛ እናት ሌዎኖር ዦአኦም ይህንን የቺቮንዴ አባባል ይጋሩታል።

« አንድ ጋዜጠኛ አምባገነኖችን እንዴት ማስወገድ ይቻላል በሚል ባቀረበው የመጽሐፍ ይዘት ላይ የሚከራከሩ አንዳንድ ወጣቶች ለመንግሥታቸው ስጋት ይፈጠራሉ ብለው ፕሬዚደንቱ ማሰባቸው ፍፁም የማይገባ ነገር ነው። ፖሊስ እቤቴ በመምጣት ያልፈተሸው ነገር አልነበረም፤ ኮምፒውተር እና የእጅ ስልኮችን ወስዶዋል። የቤቱ ጣራ ላይ ሳይቀር በመውጣት ነበር ፍተሻቸውን ያካሄዱት። በቤታችን አንድም የጦር መሳሪያ የለም፣ ልጄ ሀምዛም ማንንም የማይጓዳ ነው። መንግሥት በቁጥጥር ያዋላቸው ሕፃናትን ነው። ጦር ኃይሉ ውስጥ አልነበሩም። »

ተማሪዎች፣ አርቲስቶች እና ጋዜጠኞች የሚጠቃለሉበት እና የአንጎላ ዓብዮታዊ ንቅናቄ አባላት ካለፉት 38 ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን በአምባገነናዊ ስርዓት በመምራት ላይ ናቸው የሚሉዋቸውን ፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽን አገዛዝ በሰላማዊ ተቃውሞ የማብቃት ዓላማ ይዘው ነው የተነሱት። እስረኞቹ ወጣቶች የት እንዳሉም ሆነ በሕይወት ስለመኖር አለመኖራቸው የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ነው ዘመዶቻቸው እና ጠበቆቻቸው የሚናገሩት። የአንጎላ ሀገር አስተዳደር ሚንስትር አንጀሎ ታቫሬስ ግን ይህን አባባል መሠረተ ቢስ ሲል አጣጥለውታል።

« አንዳንድ የሀገሪቱን ፀጥታ እና ስርዓት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ለማካሄድ ሲያሤሩ እጅ ከፍንጅ የተገኙ አንዳንድ ወጣቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታሰራቸውን አረጋግጣለሁ። ማስረጃ ማሰባሰቡን ጀምረናል። ፍተሻም አካሂደናል። የታሳሪዎቹ የፍርድ ሂደት ሕጉ በሚያዘው መሠረት ይከናወናል፣ ጉዳያቸው በዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በመታየት ላይ ያለ የፍትሕ ጥያቄ በመሆኑ ገና በይፋ አልወጣም። »

የአንጎላ መንግሥት በወቅቱ እየወሰደ ያለው ርምጃ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ ሂውመን ራይትስ ዎች ባልደረባ ያን ሌቪንም ገልጸዋል።

« የአንጎላ መንግሥት ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ በወጣቱ እና በጋዜጠኞች ላይ ያስፋፋው የእስራት ተግባር ፖሊስን እና የሀገሪቱን የፍትሕ አውታር አስተያየቱን በነፃ መግለጽ የሚፈልገውን ሕዝብ ሰብዓዊ መብትን ለመርገጫ እየተጠቀመበት መሆኑን ያሳየ ምልክት ነው። እንደ አንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት ይህ ርምጃው በጣም አሳስቦናል። »

አንቶንዮ ካሽካሽ/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic