የአንጎላ ምርጫ ዘመቻ | አፍሪቃ | DW | 05.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአንጎላ ምርጫ ዘመቻ

አንጎላ ከ17 ቀናት  በኋላ አዲስ ምክር ቤት እና አዲስ ፕሬዚደንት ትመርጣለች። ምርጫው ከብዙ ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱን እየመሩ ያሉት በወቅቱ በጠና የታመሙትን የፕሬዚደንት ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽን ዘመን ያበቃል፣ ያም ቢሆን ግን ብዙም የሚቀየር ነገር አይኖርም ተብሎ ይጠበቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:30

ተቃዋሚዎች ምርጫው ፍትኃዊና ሰላማዊ እንዲሆን ጠይቀዋል

ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ ከኢኳቶርያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ቀጥለው በአፍሪቃ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉ መሪ ናቸው። የአንጎላን የስልጣን ኮርቻ ከተቆናጠጡ 38 ዓመት ሆኗቸዋል። በጎርጎሮሳዊው 1979 ዓ.ም ስልጣን ላይ ሲመጡ አንጎላ ከፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ ተላቃ ነፃነቷን ካገኘች ገና አራት ዓመቷ ነበር። በሀገሪቱ በዚያን ጊዜ በገዢው የአንጎላ ነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ፣ በምህጻሩ፣ በ«ኤምፒኤልኤ» እና በሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ማለትም፣ በአንጎላ ሙሉ ነፃነት ብሔራዊ ህብረት፣ በምህጻሩ በ«ዩኒታ» እና የአንጎላ ነፃነት ብሔራዊ ግንባር፣ በምህጻሩ በ«ኤፍኤንኤልኤ» መካከል የርስበርሱ ጦርነት ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ነበር።  

በአንጎላ የርስበርሱ ጦርነት ከ16 ዓመታት በኋላ ምርጫው በ1992 ዓም ተካሂዷል። የያኔው ምርጫ በሀገሪቱ ከዚያን ጊዜ በኋላ እንደተካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ፕሬዚደንት ዶሽ ሳንቶሽን እና ፓርቲያቸው አሸናፊዎች ሆነዋል። የተቃዋሚ ወገኖች ምርጫቹን እኩል እድል ያላገኙባቸው እና የመንግሥት የማጭበርበር ተግባር የታየባቸው ነው በሚል በጥብቅ ይነቅፋሉ። ይሁንና፣ ምርጫውን የታዘቡ ዓለም አቀፍ ቡድኖች የምርጫውን ውጤት ሲቀበሉ ነው የታዩት። 

በዘንድሮው የአንጎላ ምርጫ በመዲናይቱ ሉዋንዳ ለሚገኙት የምክር ቤት መንበሮች ስድስት ፓርቲዎች በተፎካካሪነት ቀርበዋል። በምርጫው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት በተዘዋዋሪ መንገድ ይመረጣሉ። በምርጫው ውጤት የአብላጫውን ድምፅ በሚያገኘው ፓርቲ የእጩዎች ስም ዝርዝር ላይ ስሙ በአንደኛነት የሚቀርበው እጩ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ይሆናል።   በዘንድሮው ምርጫ አንድ በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ቢኖር፣ ፕሬዚደንት ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ የሀገሪቱ መሪ እንደማይሆኑ ነው።  በምርጫው እንደማይወዳደሩ ቀደም ሲል ካስታወቁ በኋላ፣ ፓርቲው በመጨረሻ ባካሄደው ጉባዔው ዦዋዎ ሉሬንቾን ቀዳሚው እጩ አድርጎ ሰይሟል።   ከምርጫው በኋላ ሉሬንቾ ቀጣዩ የአንጎላ ፕሬዚደንት መሆናቸው እንደማይቀር ማንም አልተጠራጠረም። 
የተቃዋሚው ወገን በአሁኑ ምርጫም እንደ ገዢው ፓርቲ እኩል እድል እንደማይኖረው ለዶይቸ ቬለ የገለጸው ጋዜጠኛው ኾዜ አዳልቤርቶ ፣ በፓርቲዎቹ መካከል የሚታየው ክፍፍልም ሌላ እንቅፋት መሆኑን ተናግሯል።

«የተቃዋሚ ወገን በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በቂ የማሸነፍ እድል የለውም። እርግጥ፣ በወቅቱ በሚታየው ከፍተኛ የህዝብ ብሶት የተነሳ የተቃዋሚ ወገን ከገዢው ፓርቲ የተወሰነ ድምፅ መንጠቁ አይቀርም።  ይሁን እንጂ፣  የተቃዋሚ ፓርቲዎች የተከፋፈሉ  እና ጠንካራ መሪም የሌላቸው ናቸው። ምን ለመስራት እንደሚፈልጉም መልዕክታቸውን ለህዝብ በሚገባ መልኩ ማስተላለፍ አልቻሉም።»
የአንጎላ የተቃዋሚው ወገን በዚሁ ምርጫ ላይ እድሉ በጣም የተገደበ መሆኑን ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው የተቃዋሚው ፓርቲ፣ «ኤፒኤን» ቃል አቀባይ ቴካ ንቱ ገልጸዋል።
« እስካሁን እንደሚታየው በሀገሪቱ ያሉት ፓርቲዎች እኩል የመፎካከር እድል አላቸው ሊባል አይችልም። እርግጥ፣ ሁሉም ፓርቲዎች በመንግሥት ራድዮ እና ቴሌቪዥን ማስታወቂያዎቻቸውን  ማስተላለፍ ይችላሉ። ይህ ግን ብቸኛው ምሳሌ ነው፣ ከዚህ በተረፈ ግን ፓርቲዎች በጠቅላላ በአንድ ዓይን ታይተው እኩል እድል ይሰጣቸዋል ብሎ ማሰቡ ስህተት ነው። »

ምክንያቱም፣ ይላሉ  የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ንቱ፣ ሁሌም ሲደረግ እንደቆየው ገዢው ፓርቲ ከሌሎቹ በተለየ ለራሱ ሰፊ እድል ሰጥቶዋል። ቴካ ንቱ ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ በጀርመን የኤሰን ከተማ  ሲሆን የሚኖሩት፣ ለምርጫው ዘመቻ  እረፍት ወስደው ወደ አንጎላ ሄደዋል።  ንቱ እንደሚሉት ፣ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ዘመቻ ላይ ከገዢው ፓርቲ ጋር መፎካከር የሚያስችላቸው ፣ ለምሳሌ፣ ለማስታወቂያ፣ ለእጩዎቻቸውም ሆነ ለረዳቶቻቸው መጓጓዣ፣ ወይም ድምፃቸውን ሊሰጧቸው ይችሉ ይሆናል ለሚባሉ መራጮች ስጦታ መስጫ እንኳን የሚሆን  ለገንዘብ የላቸውም።  ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አይገባም ብለዋል ንቱ።

«ባለፉት ምርጫዎች የተቃዋሚው ወገን በጠቅላላ ከ220 የምክር ቤት መንበሮች መካከል 50 ዎቹን እንኳን አለማግኘቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። ይህ የምክር ቤቱ የመስራት አቅምን ይገድባል። በአሁኑ ጊዜ ያለን ምክር ቤታዊ አምባገነናዊ ስርዓት ነው። እና ይህ ማብቃት አለበት።»

ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚገምቱት፣ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ብዙም የማይታዩት የአንጎላ ፕሬዚደንት ዶሽ ሳንቶሽ በጠና ሳይታመሙ አልቀሩም። የፖርቱጋል    ሳምንታዊ መጽሄት «ኤስፕሬሶ» ታማኝ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው እየተበላሸ የሄደው የፕሬዚደንቱ ጤንነት የአንጎላ አመራር አባላትን እጅግ አሳስቧል። በካንሰር በሽታ በመሰቃየት ላይ ሳይሆኑ አልቀሩም የሚባሉት ፕሬዚደንቱ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለህክምና ወደ ስጳኝ የባርሰሎና ከተማ  መመላለሳቸውን ቀጥለዋል፣ ዶሽ ሳንቶሽ እና ፓርቲያቸው ለድህረ ሳንቶሽ ጊዜ  መዘጋጀታቸውን ጋዜጠኛው ኾዜ አዳልቤርቶ ተተኪያቸውን ቀጥለዋል። 
«  ርዕሰ ብሔሩ ፕሬዚደንቱ አንድ ነገር ቢሆኑ፣ ይህ ለ «ኤምፒኤልኤ» ድንገተኛ አይሆንበትም፣ የዶሽ ሳንቶሽን ተተኪ በማዘጋጀት ዦአዎ ሉሬንሶን መርጧል። በመሆኑም፣ ፕሬዚደንቱ ድንገት በምርጫ ዘመቻ ወቅት እንኳን ቢሞቱ ፓርቲው ችግር አያጋጥመውም።»

Angola Wahlkampf Joao Lourenco MPLA

ዦአኦ ሉሬንሶ

ሌሎች ታዛቢዎች ይህን አስተሳሰብ አይጋሩም። ከፍተኛ የመንግሥት ቦታዎችን ለመያዝ የስልጣን ሽኩቻ ሊነሳ ይችላል ባይ ናቸው። ምክንያቱም ኾዜ ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግሥት ስልጣን ቦታዎችን ለርሳቸው ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ሰጥተዋል። ለምሳሌ ልጃቸው ኢዛቤል ዶሽ ሳንቶሽ የሀገሪቱን የነዳጅ ዘይት ተቋም-ሶናንጎልን፣ ወንድ ልጃቸው የመንግሥቱን የነዳጅ ዘይት መስሪያ ቤትን በኃላፊነት ይመራሉ። የፖሊስ፣ የጦር ኃይሉ እና የስለላ ድርጅቱም በዶሽ ሳንቶሽ ታማኞች ነው የተያዘው።  እነዚህ ባለስልጣናት ዶሽ ሳንቶሽ ስልጣናቸውን በሚለቁበትም ጊዜy ይህንኑ ስልጣናቸውን እንደያዙ መቆየት ይችላሉ። የአንጎላ ምክር ቤት በመጨረሻው ጉባዔው ወቅት ተሰናባቹ ፕሬዚደንት የሾሟቸው ባለስልጣናት እንዳይነኩ የሚያዝ አንድ ህግ በከፍተኛ ድምፅ አፅድቋል። ህጉን በምክር ቤት የሚወከሉት ሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች «ዩኒታ» እና «ካዛ-ሲኤ» ቢቃወሙትም፣ ከ220 የምክር ቤት መንበሮች 40 ብቻ በመያዛቸው ሕጉ አልፏል። የሕጉ ማለፍ በጣም አነጋጋሪ እንደነበር ዜጠኛ ኾዜ አዳልቤርቶ አስታውሷል።

Angola Jose Eduardo dos Santos

ኤድዋርዶ ዶሽ ሳንቶሽ

«ፕሬዚደንቱ ትተውልን የሚሄዱት ሕግ ብዙ ክርክር አስነስቶ ነበር። በኔ አስተያየት፣ ይህ ጥያቄ ክፍት ሆኖ መቆየት ነበረበት።  ምክንያቱም ሕጌ የቀጣዩን የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ስልጣን በጣም ይገድባል። ዦአዎ ሉሬንሶ ጀነራል ናቸው። እና ለጦር ኃይሉ፣ ለፖሊሱ እና ለስለላው ተቋም የሚፈልጓቸውን ሰዎች መሾም  ይፈልጋሉ ብዬ ነው የማስበው። » 
ከሁለት ሳምንት በፊት በተጀመረው የምርጫ ዘመቻ ገዢው ፓርቲ፣ «ኤምፒኤልኤ» ተስፋ ለቆረጠው ድሀው የሀገሪቱ ወጣት 500,000 የስራ ቦታዎች ለመፍጠር ፣ ተቃዋሚው ፓርቲ «ዩኒታ » ደግሞ ንዑሱን ስራ የመጀመሪያ ደሞዝ 500 ዶላር ለማድረግ፣ «ካዛ- ሲኤ» የተባለው ሌላው ተቃዋሚ ፓርቲ ደግሞ የመንግሥት እና ያካባቢ ምክር ቤታዊ ምርጫ ሕጎች ተሀድሶ ላማድረግ ቃል ገብተዋል። ሁሉም ተፎካካሪ እጩዎች እና ፓርቲዎች የምርጫው ዘመቻ  ትክክለኛ እና በተለይ ሰላማዊ እንዲሆን ከመጠየቅ ባይቦዝኑም፣ በተቃዋሚ ወገን ደጋፊዎች እና በፀጥታ ኃይላት መካከል ግጭት መታየቱ እና አንድ የ«ኤምፒኤልኤ»ን ባንዴራ ያቃጠለ ግለሰብም በዚሁ ሰበብ መገደሉ ተሰምቷል።

አንቶንዮ ካሽካሽ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ
 

Audios and videos on the topic