የአንድ ዓመቱ ዜና መዋዕል | ኢትዮጵያ | DW | 02.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአንድ ዓመቱ ዜና መዋዕል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ ዛሬ ልክ አንድ ዓመታቸው። በአንድ ዓመት ቆይታቸው ብዙ መጽሐፍ የሚወጣው ታሪክ አኑረዋል። ውጥረቱ በተስፋ፣ ተስፋው በሥጋት ተተክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም "ነፍሴን ልሰዋልህ" ከሚላቸው ጀምሮ "ዓይንህን ላፈር" እስከሚሉ ወዳጅ እና ጠላት አፍርተዋል።


በፍቃዱ ኃይሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ ዛሬ ልክ አንድ ዓመታቸው። በአንድ ዓመት ቆይታቸው ብዙ መጽሐፍ የሚወጣው ታሪክ አኑረዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተገለባብጧል፤ የፖለቲካ ተዋናዮች የላይኞቹ ወደታች፣ የታችኞቹ ወደላይ ተንጠዋል። ውጥረቱ በተስፋ፣ ተስፋው በሥጋት ተተክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም "ነፍሴን ልሰዋልህ" ከሚላቸው ጀምሮ "ዓይንህን ላፈር" እስከሚሉ ወዳጅ እና ጠላት አፍርተዋል። በዚህ አጭር መጣጥፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አንድ ዓመት ሥራዎች በወፍ በረር እየቃኘን አንድምታውን እንጠይቃለን።

የኢሕአዴግ የንስሐ ሩጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ተቀባይነት ያስገኘላቸው እና ተስፋ እንዲጣልባቸው ያደረገው የኦሕዴድ እና ብአዴን ትብብር፣ እንዲሁም ከሕወሓት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት ነበር። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢሕአዴግ ውስጥ ምርጫ በጉጉት ተጠበቀ፣ የእርሳቸው መመረጥም በተቃዋሚዎች ዘንድ ሳይቀር ዕውቅና አገኘ። ከዚያ በፊት ተጀምሮ የነበረው የፖለቲካ እስረኞቹ ፍቺ "አይፈቱም" የተባሉትን እነ አንዳርጋቸው ፅጌን ሳይቀር አስከተለ። “ሽብርተኛ” ድርጅቶች “ምኅረት” አገኙ። ስደተኞች ተመለሱ። ለሦስት ዓመታት የዘለቀው ተቃውሞ በፌሽታ ሰልፎች ተተካ። ኢትዮጵያ ላፍታም ቢሆን ቂሟን ረሳች።

“አይነኬ” ይባሉ የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትር እና የደኅንነት ሹሞች ተሻሩ። አፋኝ አዋጆች መሳቢያ ውስጥ ተከተቱ። የታገዱ ድረ ገጾች ተከፈቱ። የተመለከታቸው በወንጀል ይከሰስ የነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፥ ኢሳት እና ኦኤምኤን አገር ውስጥ ቅርንጫፍ ከፈቱ።

ደም መፋሰስ እና የአገር መፍረስ ይከሰታል ብለው ሲጨነቁ የነበሩ ሁሉ "እፎይ" አሉ፤ ኢትዮጵያ የነጻነት እና የተስፋ አገር መሰለች። ይኼ ሁሉ የሆነው ግን ለመተንተን እንኳን እስኪቸግር በብርሃን ፍጥነት ነበር።

ለውጡን የማፅናት ሙከራ

ዓለም የፖለቲካውን መለዋወጥ እንደ ድራማ እየተከታተለ ነው። ብዙዎች ለውጡ ሕጋዊ እና ተቋማዊ መደረግ አለበት እያሉ መወትወታቸውን ቀጠሉ። የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ማሻሻያ ምክር ቤት ተቋቋመ፣ አፋኝ ይባሉ የነበሩት አዋጆች በይፋ ክለሳቸው ተጀመረ። የሲቪል ማኅበራቱ አዋጅ ተሻሽሎ ፀደቀ። የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ፣ የምርጫ እና የሚዲያ ሕግጋቱም ክለሳ ግብረ ኃይል ተመድቦለት ይካሔድ ጀመር።

"ሰበር ዜና አያልቅባቸው" የተሰኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ከ30 በላይ የነበሩትን ሚኒስትሮች ወደ ኻያ ሰበስበው ግማሾቹን ሴቶች በማድረግ ለዓለም የዜና አውታሮች ዳግም የዜና ግብዓት ፈጠሩ። ሴቷ ፕሬዚደንት ሳሕለ ወርቅ በትዕምርታዊ ትእይንት ተሾሙ። ቀድሞ በሲቪል ማኅበራት አዋጅ የታፈኑት መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፥ የቀድሞዋ የፖለቲካ እስረኛ እና ስደተኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ እንደመቱ ተቆጠረላቸው። በአንድ በኩል የስርዓተ ፆታ ማስተካከያ ሲያደርጉ፣ በሌላ በኩል ቀድሞ የተገፉትን መልሰው በመሰብሰብ እርቅ አወረዱ።

 

የኢትዮ-ኤርትራ ጉሮ ወሸባ

በጠቅላይ ሚነስትሩ ጥረት ከተገኙ ትላልቅ ድሎች አንዱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የኖረው የጠብ ግድግዳ መፍረሱ ነው። የኹለቱም አገር መሪዎች እየተመላለሱ መጠያየቅ ጀመሩ። የተነፋፈቁ እና ተራርቀው የከረሙ ቤተሰቦች ዳግም ዓይን ላይን ተያዩ። ታፍኖ የከረመ የኹለቱ ሕዝቦች ፍቅር ገነፈለ። ሰዎች ያገኙት ቁጥር ላይ ከዚህ እዚያ፣ ከዚያ እዚህ እስከ መደዋወል በፍቅር እና በደስታ አቅላቸውን ሳቱ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በውስጣዊ ብሔርትነኝ ተከፋፍላ የምትታመሰውን ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ቀንድ ጋር አዋህዳለሁ፤ ድንበር አልባ አገራት አደርጋለሁ የሚል ሕልማቸውንም ይህን አጋጣሚ ተንተርሰው ይፋ አደረጉ።

የኢኮኖሚውን ሰበቃ መጋፈጥ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡት ሥራ አጥ ወጣቶች ሲያምፁባት በከረመችው ኢትዮጵያ ነው። የዕዳ ውዝፍ ጣሪያው ጫፍ ላይ ቆሟል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኢትዮጵያ የመድኃኒት መግዣ አቅም እስከሚያጥራት ድረስ ቀውስ ፈጥሮ ነበር። የአገር ውስጥ ኢኮኖሚው በቀውሱ ተዳክሟል። ይህን ለመታደግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ሳዑዲ አረቢያ ጎራ በማለት የዶላር ረብጣዎችን በማግኘት ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሔ ፈጥረዋል። ይሁን እንጂ ይኼ እርምጃቸው ለውጡን በንቃት የሚከታተሉትን ምዕራባውያን አስደንግጧል። ለወትሮው በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ክፍፍል ወገን ያልመረጠችው ኢትዮጵያ፥ ‘የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት አንዱን ወግና ይሆን?’ የሚል ጥያቄ አጭሮባቸዋል።

ከዚያም በላይ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩትን ድርጅቶች ለግል ይዞታ እናዛውራልን አሉ። ይሁን እንጂ ዛሬም የሥራ አጥነቱን በአጭር ጊዜ መቅረፍ የሚያስችል መላ አልመቱም። ወጣቶች ከአደባባይ ወደ አዳራሽ የሚገቡበት ዘዴ አልተቀየሰም። ኢኮኖሚው በመንገድ መዘጋት እና ሌሎችም ደቦ ፍርዶች ሳቢያ እንደተቀዛቀዘ ነው። የዜጎች መፈናቀል የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን ወጪ አሻቅቦታል። እነዚህ ተደማምረው የለውጡ ሩጫ ላይ መሰናክል ሆነው ቆመዋል።

ኢሕአዴግን እያፈረሱ ማዳን

ለውጡ የቀድሞውን ኢሕአዴግ ገድሎ አዲሱን ወልዷል። አዲሱ ግን ገና በቁሙ ዳዴ ማለት እንኳን አልጀመረም። ይህም በለውጥ ሩጫ ላይ ላለው አመራር ከባዱ ፈተና ነው። በሕወሓት የበላይነት ይታማ የነበረው ኢሕአዴግ ገና ካኹኑ በኦዴፓ (የቀድሞው ኦሕዴድ) የበላይነት ይታማ ጀምሯል። ሆኖም ኦሕዴድና ብአዴን ከቀድሞ ታሪካቸው ለመፋታት ሥም እና አርማዎቻቸውን እስከ መቀየር ደርሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ገና እንዋሐዳለን” እያሉ ነው። ይሁን እንጂ በሒደቱ ሕወሓትን አጉድለዋል። ሕወሓት ምንም እንኳን ከግንባሩ አባልነት ባይወጣም የአብሮነት መንፈሱን ካጣ ግን ሰንብቷል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነትንም በደረጃ ብናስቀምጠው በትግራይ በጣም ዝቅተኛውን ደረጃ እንደሚያገኝ አያጠራጥርም።

ኢሕአዴግ ውስጣዊ አንድነት ማጣቱ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ከፌዴራል እስከ ክልሎች እና ዞኖች ድረስ የሚፈልገውን ማስፈፀም እንዳይችል አድርጎታል። መንግሥት ውስጥ ያሉ ብዙ መንግሥታት መፈጠርም መንሥኤ ሆኗል። የለውጡ ጎዳና ላይ ከተተበተቡ መሰናክሎች አንዱ ይኸው ነው።

የሽግግር ጊዜ ፍትሕ
 

ለውጡ ካጋለጣቸው “ምስጢሮች” ውስጥ የመንግሥትን ሥልጣን ተገን ተደርገው የተሠሩ ወንጀሎች ስፋት እና አሰቃቂነት ይገኙበታል። የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና የሙስናው ደረጃ መንግሥት ባለበት አገር የሆነ አይመስልም። አዲሱ አመራር በነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩትን ማሰሩም የዓመቱ አንዱ ክስተት ነበር። ይሁን እንጂ እስሩ ሁሉንም ተሳታፊዎች ያላካተተ በመኾኑ እንዲሁም አንድ ወገን ላይ ያተኮረ ነው በሚል፥ “የፖለቲካ እስር” ነው ተብሎ ተተችቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ በተዘጋጀ ሰልፍ ላይ የተጣለውን ቦንብ በማቀነባበር የተጠረጠሩት የቀድሞው የደኅንነት ሹም በፖሊስ እየተፈለጉ ነው። የትግራይ ክልል ግን የደኅንነት አማካሪ አድርጎ ሾሟቸዋል። ይህም መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር አቅቶታል የሚል ጥያቄ አጭሯል።

የታፈኑ ጥያቄዎች መፈንዳት

ሕዝባዊ አመፆች የፓርቲ ውስጥ ቅራኔ ፈጥረው የለውጥ ጮራ መፈንጠቃቸው ሁሉንም ወገኖች “ጊዜው አሁን ነው” እንዲሉ አድርጓቸዋል። ለዚህ ክስተት እንደ ደቡብ ክልል ማሳያ የሚሆን የለም። ከሁሉም አስቀድሞ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት “ክልል መሆን ይገባኛል” የሚል ውሳኔ አሳልፎ የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄው በክልሉ በኩል ለምርጫ ቦርድ ቀርቧል። ይህንን አርአያ በመከተል ሌሎችም ዞኖች የክልልነት ጥያቄ እያነሱ ሲሆን፥ ይህም የደቡብ ክልልን ታሪክ ያደርገዋል ተብሎ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ክልሎች ይዛመታል በሚል ሁለገብ ቀውስ እንዳይፈጥር ተሠግቷል።

የደቦ ፍርድ እና ስርዓት አልበኝነት

በአንድ ዓመቱ የለውጥ ዓመት እንደ ደቦ ፍርድ አስቀያሚ አሻራ የጣለ ነገር የለም። በሐዋሳ፣ ጂግጅጋ፣ ጣና በለስ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሻሸመኔ፣ ቡራዩ እና ሌሎችም አካባቢዎች ዜጎች ሌሎች ዜጎች ላይ አሳዛኝ ጥቃቶችን አድርሰዋል። ከዚህም አልፎ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ማፈናቅሎች በኢትዮጵያ ታሪክ ጣሪያ ላይ ደርሷል። አልፎ ተርፎም በወለጋ ከስደት የተመለሰው ኦነግ ሠራዊት ነኝ ያለ ቡድን የመንግሥት መዋቅሮችን ለመቆጣጠር መሞከሩ፣ ዝርፊያ እና ጥቃቶችን ማድረሱ እንዲሁም ትምህርት እና የመንግሥት ሥራ ማስተጓጎሉ የኃይል የበላይነት ከመንግሥት እጅ ወጥቷል የሚል ድንጋጤ ከመፍጠሩም ባሻገር የደኅንነት እና የፀጥታ አካሉ ላይ እምነት የማጣት ችግር አስከትሏል።  ቀድሞ መንግሥትን ይፈሩ የነበሩ ሰዎች፥ ዛሬ ዛሬ በደቦ የተደራጁ ሰዎችን መሥጋት ጀምረዋል።

የፍኖተ ካርታ ያለህ?!
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራር ከቀረቡበት ትችቶች መካከል “የለውጡ መንገድ፣ መድረሻው እና የጌዜ ገደቡ አይታወቅም፤ ፍኖተ ካርታ የለውም” የሚለው ዋነኛው ነው። ለዚህም ይመስላል የአመራሮቹ አጀንዳ በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች እና በዘውግ ብሔርተኞች አጀንዳ የተጠመዘዘ የሚመስለው። የብሔርተኝነቱ ጡዘት ክልሎቹን ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት እንዲመሥሉ ከማድረጉም በላይ፥ ለፌዴራል መንግሥቱ የማይታዘዙ አድርጓቸዋል። ከዚህም በላይ በአመራሮቹ እና በተለይም መጀመሪያ ከትግራይ እና ቀጥሎ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኩርፊያ እና ጥርጣሬ እንዲገጥመው አድርጓል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ በሩጫ ተጀምሮ፣ በሶምሶማ ቀጥሏል። የምሥራች ባዘሉ ሰበር ዜናዎች ተጀምሮ፣ ልብ በሚሰብሩ ገጠመኞች ታጅቧል። በተስፋ ነግሦ፣ በሥጋት ተፈትኗል። የቀድሞው የመንግሥት አመፀኝነት መንገሥታዊ ያልኾኑ አካላት ተተክቷል። መንግሥት ሲራዘም የቆየውን የሕዝብ ቆጠራ በብሔርተኞች ውትወታ ዳግም ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሞታል። የቀጣዩን ዓመት አገር ዐቀፍ ምርጫም እንዲሁ እንዲያራዝመው ከሌሎች ወገኖች ግፊት አለበት። የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ባለመካሔዱ የተፈጠረው የቅቡልነት ችግር ሳይቀረፍ፥ አገር ዐቀፉ ምርጫ የሚራዘም ከሆነ ምን ይከሰት ይሆን? የማይራዘም ከሆነስ፥ አሁን ያለው ስርዓተ አልበኝነት እንዴት ቆሞ ምርጫው እንዴት ሊካሔድ ነው? ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ለቅስቀሳ አደባባይ ሲወጡ ግጭቶች እንደማይቀሰቀሱ ምን ዋስትና አለ? በዚህም ኾነ በዚያ አቅጣጫ አሁን የገነነው ሥጋት ብቻ ነው።
በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ«DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።