የአንድነት ፓርቲ ከመድረክ አባልነት መታገዱ | ኢትዮጵያ | DW | 24.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአንድነት ፓርቲ ከመድረክ አባልነት መታገዱ

አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መድረክ በመባል ከሚታወቀው የፓርቲዎች ስብስብ መታገዱ ተሰማ። አንድነት የታገደው፤ የመድረኩ አመራር አካላት እንደሚሉት፤ የግንባሩን ደንብና መመሪያ አክብሮ ለመንቀሳቀስ ባለመቻሉ ነው።

እገዳ እንደተጣለበት ያረጋገጠው የአንድነት ፓርቲ በበኩሉ መድረኩ የሥራ ድክመት ይታይበታል
ሲል ይተቻል። በተያያዘ ዜና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ትላንት መድረክን መቀላቀሉ ታውቋል።

ኣንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ አባልነት የታገደው፤ የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እንደሚሉት፤ የግንባሩን ሕገ ደንብና ድርጅታዊ ስነሥርዓት ጠብቆ ሊራመድ ባለመቻሉ ኣሊያም ባለመፈለግ ነው። ከዚህ አልፈው ዝርዝር ጉዳዮችን ለመግለጽ ግን የፈለጉ ኣይመስልም፤ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤

የአንድነት ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢኒጂነር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው የተጠቀሱት መግለጫዎች ቢኖሩም የአንዳንድ አመራሮች የግል አስተያየት እንጂ የፓርቲው አቋም አይደለም ብለዋል። እናም የሊብራል ዲሞክራሲን ለምንከተል ኃይሎች ይህ መብት እንጂ ጥፋት አይደለም ሲሉም ተከራክረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑ፤ የአንድነት ኃይሎች ወደ አንድ ጫፍ እና የብሔር ድርጅቶች ደግሞ ወደ ሌላ ጫፍ የመሰባሰብ አዝማሚያ ይታያልና ከምን የተነሳ ይመስልዎታል? የሚል ጥያቄም አቅርቤላቸው ነበር፤ ለኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው። እሳቸው አይደለም ቢሉም የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ግን እኔም ኣንዳንድ እማነባቸው ነገሮች አሉ ይላሉ።

አንድነት ከአባልነት ቢታገድም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ በአዲስ አባልነት ትላንት መድረክን መቀላቀሉን ዶ/ር መረራ ኣረጋግጠዋል። የሲዳማ አርነት ንቅናቄን ጨምሮ የመድረክ ስብስቦች በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ የደቡብ ማህበረ ዲሞክራሲ አንድነት እና አረና ትግራይ ናቸው።

ጃፈር ዓሊ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic