የአንደኛው ዓለም ጦርነት መታሰቢያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአንደኛው ዓለም ጦርነት መታሰቢያ

በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ያለቀበት አንደኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረበት መቶኛ ዓመት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታስቧል ።በቅርቡ የጦርነቱ መቶኛ ዓመት ከታሰበባቸው ሃገራት አንዷ የጦርነቱ የመጀመሪያዋ ሰለባ ቤልጂግ ናት ።

በጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 28፣ 1914 የኦስትርያው አልጋወራሽ ልዑል ፍራንዝ ፈረዲናንድ የቦስንያን ዋና ከተማ ሳራዬቮን ሲጎበኙ እርሳቸው ና ባለቤታቸው ሶፊ በአንድ የቦስንያ ሰርባዊ ብሄረተኛ ተተኩሶባቸው መገደላቸው በወቅቱ በኦስትርያ ያን ያህል ትኩረት ያገኘ አልመሰለም ነበር ። የተቀረው አውሮፓም የልዑሉ ግድያ ዓመታት የሚቀጥል ጦርነት ውስጥ ያስገባናል ብሎ አላሰበም ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በኦስትርያ ባለሥልጣናት አበረታችነት በሳራዬቮ የክሮአትና የቦስኒያ ሙስሊሞች በሰርቦች ላይ ያስነሱትን አመፁ አጠናክረው ሰርቦችን መግደል ንብረታቸውንም ማውደም ያዙ ። ይህን መሰሉ ጥቃት በሰርቦች ላይ በተደራጀ መልኩ የተካሄደው በሳራዬቮ ብቻ አልነበረም ። በሌሎችም የኦስትሪያና የሃንጋሪ ትላልቅ ከተሞች ተመሳሳይ ጥቃት ተፈፅሟል ። የአልጋ ወራሹ ግድያ በኦስትሪያ ሃንጋሪ ጀርመን ሩስያ ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ መካከል አንድ ወር የፈጀ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ አስከተለ ። በግድያው የሰርብያ ባለሥልጣናት እጅ አለበት የሚል አቋም የያዘችው ኦስትሪያ ሰበብ አስባብ ፈልጋ በሰርቢያ ላይ ጦርነት ስታውጅ ሩስያ ከሰርብያ ጎን ቆመች ። በኦስትሪያ ሃንጋሪና በጀርመን ላይም ጦርዋን አንቀሳቀሰች ። የኦስትሮ ሃንጋሪ ቃል ኪዳን ተጓዳኝ ጀርመን በበኩሏ በቤልጂግና ፈረንሳይ የሩስያን

እንቅስቃሴ እንዲያግዱ ጠይቃ ሳይሳካላት ከቀረ በኋላ እጎአ ነሐሴ አንድ በሩስያ ላይ ጦርነት አወጀች ።በማግስቱ ነሐሴ 2 ሉክስምበርግን አጠቃች ።ነሐሴ 3 ፈረንሳይ ላይ ጦርነት አወጀች ። ነሐሴ 4 የጀርመን ወታደሮች በቤልጂግ በኩል የፈረንሳይን ድንበር ለማለፍ ሲሞክሩ ቤልጂግ በማገዷ ጀርመን ጦርነት አወጀችባት ። ከዚያም ብሪታኒያ በጀርመን ላይ ጦርነት አወጀት። ነሀሴ 4 1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ገለልተኛ በነበረችው በቤልጂግ ተጀመረ ። ልየዥ የተባለችው የቤልጂግ ከተማ የመጀመሪያዋ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ነበረች ።

«ከጀርመን ወረራ በፊት እዚህ በድንበሩ አካባቢ ጦርነት የተካሄደበት ቦታ አልነበረም ። ሰዎችም ስራ ወዳገኙበት ነበር የሚሄዱት ። የጦርነቱ መጀመር ይህን ሁሉ ሙሉ በሙሉ አቋረጠው ። በመጀመሪያው ሳምንት የጀርመን ወታደሮች በአኽንና በልየዥ ከተሞች መካከል 950 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ።በመቶዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን ሆነ ብለው አቃጥለዋል ። ይህ እስካሁን ድረስ የጀርመንና የቤልጂግን ግንኙነት በተለይም ደቡባዊ ቤልጂግ በሚገኙት በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ በዋሎኖች ላይ ተፅእኖ እንዳሳደረ ነው ። ከቤልጂግ በኩል ሁለቱንም ጦርነቶች ያዩ ወገኖች የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የከፋ እንደነበር ይናገራሉ ። »

በቤልጂግ የጀርመን ማህበረሰብ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር ሄርበርት ሩላንድ ነበሩ ጦርነቱ ሲጀመር በወቅቱ ገለልተኛ በነበረችው በቤልጂግ የደረሰውን ጥፋት የተናገሩት ። ያኔ ከጀርመን ጦር ጋር ሲነፃፀር የቤልጅግ ኃይል አነስተኛ የነበረ ቢሆንም በአስገራሚ ሁኔታ ለተወሰኑ ቀናት ወራሪውን የጀርመን ጦር መቋቋም መቻሉ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ ጀግንነት ይታወሳል ።የጀርመን ጦር ሌዥ ከመግባቱ በፊት ቢግ ቤርታ የተባለ ከባድ ጥቃት የሚያደርስ መድፍ ነበር የተጠቀመው ።በነሐሴ መጨረሻ ላይም የጀርመን ጦር የመጨረሻዋን የቤልጂግ ከተማ አንትዌርፕን ያዘ ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ግን ቤልጂግ ሙሉ በሙሉ አልተያዘችም ነበር። ወራሪ ኃይል በቆየበት 4 ዓመታት በተለይ በፍላንደርስ ጦርነቱ አልቆመም ነበር ።በዚሁ የቤልጅግ ግዛት የቤልጂግ ጦር የብሪታኒያና የሌሎችም የተባበሩት ኃይሎች ሠራዊት ጀርመኖችን ሲወጉ ነበር ። የታሪክ ምሁሩ ሄርበርት ሩላንድ ይህ ለቤልጂግ ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው ይላሉ ።

«

Herbert Ruland

ሄርበርት ሩላንድ

እጅግ በጣም ጠቃሚ ነበር ። አንድ ነገር ማሰብ ይገባል ። ያኔ በቤልጂግ የተያዘው አካባቢ ስፋት 800 ካሬ ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር ። የምዕራብ ፍላንደርስ የመጨረሻውይዞታ ነበር ። ፈረንሳዮች የቤልጂጉ ንጉስ አልበርት ሰሜን ፈረንሳይ ወደ ሚገኘው የውጊያ ግንባር ወደ ሶም በመሄድ እዚያ እንዲዋጉ በተደጋጋሚ ይጠይቋቸው ነበር ። ሆኖም ንጉሱ ይህን በመቃወም እዚያው ነበር የቆዩት ። ምክንያቱም ያን ቦታ ለቀው ከወጡ ምናልባትም ወደ ሃገራቸው መመለስ እንደማይችሉ ያውቁት ነበርና ። በምዕራብ ፍላንደርሱ በይስር ወንዝ ዳርቻ የተካሄደው ውጊያ ምናልባትም ቤልጂግ እንደ ሃገር የመቀጠሏ ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል ። የሚያስገርም ታሪክ ነው ። »

የያኔው የቤልጂግ ንጉስ አልበርትና ሃገራቸው ላይ ጦር ያዘመቱት የጀርመኑ ንጉስ ዘመዳሞች ነበሩ ። ንጉስ አልበርት በተለይ በምዕራባዊ ፍላንደር ፣ የቀረውን የቤልጂግ ጦር በራሳቸው መሪነት በማዝመት በወሰዱት ቆራጥ እርምጃ እስከዛሬ ድረስ በቤልጂጋውያን በክብር ይወደሳሉ ።በጀርመንና በተባበሩት ኃይሎች መካከል ለ 4 ዓመታት ያህል በተካሄደ ጦርነት ብዙ ሰዎች አልቀዋል ። 4 ዓመታት የዘለቀው ጦርነት 37 ሺህ የቤልጂግ ወታደሮችን ፈጅቷል ። ይህ ግን ሌሎች ሃገራት በጦርነቱ ከሞቱባቸው ወታደሮች ቁጥር ጋር ሲነፃጸር አነስተኛ ነው ይላሉ ሄርበርት ሩላንድ ።

« ከቤልጂጋውያን በኩል በጦርነቱ ያለቀው ሰው ቁጥር በንፅጽር ሲታይ የተወሰነ ነበር ። የዚህም ምክንያቱ ቤልጂጎች በምሽጎች ውስጥ ይዋጉ ስለነበረ ነው ። ጥቃቱን በመከላከሉ ረገድም የሌሎቹን ያህል ብዙ አልተካፈሉም ። ዋነኛው ውጊያ እ.ጎ.አ በ 1917 ፓሰንዳሌ ውስጥ የተካሄደው ውጊያ ነው ። በዚህ ውጊያ ብሪታኒያ ከፍተኛውን የሟቾች ና የቁስለኞች ቁጥር አስመዝግባለች ። 8 ኪሎሜትር ወደፊት ለመግፋት ለ4 ወራት በተካሄደ ውጊያ የሟቾቹና የቁስለኞቹ ቁጥር 400 ሺህ ደርሶ ነበር ። ለማመን አስቸጋሪ ውጊያዎች ነበሩ ። ያም ሆኖ ከቤልጂጋውያን በኩል የሞቱት በንፅፅር ሲታይ አነስተኛ ነበሩ ።»

Gedenkfeier Erster Weltkrieg Lüttich Gauck Rede 4.8.2014

ዮአሂም ጋውክ

አንደኛው የዓለም ጦርነት ከዚህ ቀደም በጀርመኖችና በቤልጂጎች መካከል የነበረው ትስስር አቋርጦ ነበር ። ከዚያ በፊት ሁለቱ ህዝቦች በጋብቻ በቋንቋ ና በሌሎችም ባህሎች የተሳሰሩ ነበሩ ። ጀርመን ቤልጂግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ለሁለተኛ ጊዜ ወራ ብዙ የሰው ህይወት ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል ።ይሁንና ከሁለቱም ጦርነቶች በኋላ በቤልጂጎችና በጀርመኖች መካከል ፍፁም እርቀ ሰላም ወርዷል ። አንደኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረበት መቶኛ ዓመት የብሪታኒያ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት የቤልጂግ ንጉስ የፈረንሳይና የጀርመን ፕሬዝዳንቶች ጨምሮ ከ83ሃገራት የመጡ የመንግሥታት መሪዎችና ተወካዮች በተገኙበት ልየዥ ቤልጂግ ውስጥ በታሰበበት ባለፈው ሳምንት የጦርነቱ አስተምህሮት ትኩረት ከተደረገባቸው አብይ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው ነበር ። በመታሰቢያው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ ባሰሙት ንግግር የአውሮፓ ህብረት እንደው በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረ ማህበር ሳይሆን ከታሪክ ትምህርት በመውሰድ የተመሰረተ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ደግሞ የአውሮፓ የሰላም ፕሮጀክት ሲሉ የሰየሙት የአውሮፓ ህብረት ስረ መሠረቱ ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ያስከተሏቸው ዘግናኝ ውጤቶች መሆናቸውን ህብረቱም ለሌላው የዓለም ክፍል አርአያ መሆኑን አውስተው ነበር ። ጋውክ በንግግራቸው ቤልጂጋውያን ፣ የጀርመን ወታደሮች በሁለት ጦርነቶች ከፈፀሙባቸው ወረራና ከደረሰባቸው ግፍ በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ለእርቀ ሰላም እጃቸውን በመዘርጋታቸው አመስግነዋቸዋል። ከዚያን ጊዜው ከመጠን ያለፈ ብሔረተኝነትና አሰቃቂ ጭፍጨፋ ትምህርት የወሰዱት አውሮፓውያን በመካከላቸው ሰላም አውርደው የጋራ አውሮፓን በጋራ በመገንባት ሂደት ላይ ይገኛሉ ። ሆኖም አሁንም በአውሮፓ ምድር የሰው ህይወት የሚቀጠፍባቸው መፍትሄያቸውም ቅርብ የማይመስል ግጭቶች ሙሉ በሙሉ አለመወገዳቸው በአንደኛው የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ላይ ጥላ ማጥላቱ አልቀረም ። ጋውክ በንግግራቸው በስፍራው የተሰባሰቡት መሪዎች አሁንም በዓለማችን ሰላምን የሚያደፈርሱ እርምጃዎችን ለመግታት ፈጥነው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አሳስበው ነበር ።

«የአሁኑ መታሰቢያ ሁላችንም ለዓለማችን ሰላም የጋራ ሃላፊነት እንዳለብን ሊያስታውሰን ይገባል። ሰብዓዊ መብቶች ግጭቶች ሲያሰጉ ወይም ተግባራዊ ሲሆኑ ዝም ብለን ልንመለከት አይገባም። ለነፃነት ለመብት መከበር ለመቻቻል እንዲሁም ለፍትህና ለሰብዓዊነት በንቃት መታገል ይገባናል።»

የፈረንሳዩ ፕሬዳንት ፍራንሷ ኦሎንድም የሰላም ተምሳሌት ያሉት የአውሮፓ ህብረት በአውሮፓም ሆነ በሌላው የዓለም ክፍል ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ የሰዎች ሰብዓዊ ክብር ሲዋረድ ዝም ብሎ ሊያይ እንደማይገባ በአፅንኦት ነበር ያሳሰቡት ።

« ከአውሮፓ ብዙም ሳንርቅ ሰዎች ለመብታቸው መከበርና ና ለሃገራቸው አንድነት ሲዋጉ እንዴት ገለልተኛ ልንሆን እንችላለን ? በዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን ተመቶ ሲጣል እንዴት ገለልተኛ መሆን ይቻለናል ?በኢራቅና በሶሪያ ሰላማዊ ሰዎች ለጭፍጨፋ ሲጋለጡ አናሳዎች ሲገደሉ እንዴት ገለልተኛ እንሆናለን ? እንደ ሊባኖስን ያለች ወዳጅ ሃገር አንድነቷ አደጋ ላይ ሲወድቅ እንዴት ገለልተኛ ሆነን መቆየት እንችላለን ?ገለልተኛ ሆነን ልንቆይ አንችልም ። እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለብን ። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር እነዚህን ሃላፊነቶች መውሰድ ያለባት አውሮፓ ናት ።»

አንደኛው የዓለም ጦርነት በአጠቃላይ ከ15 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ፈጅቷል ።ከ20 ሚሊዮን በላይ ደግሞ አቁስሏል።ጦርነቱ የተጀመረበት መቶኛ ዓመት በሚታሰብበት በዚህ ወቅት ላይ ግን ያኔ ጠላት የነበሩት ሃገራት በአንድነት ለጋራ የአውሮፓ እድገት እየተጉ ፣ በአንድ የጋራ ገንዘብ እየተገበያዩ ዜጎቻቸውም በነፃነት ከአንዱ ወደ ሌላው ሃገር ተዘዋውረው እየሰሩ ነው ።ይህ በአሁኑ ጊዜ ሰላም በደፈረሰበት በሌላውም የዓለም ክፍል ጥሩ ተምሳሌት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ በልየዡ የአንደኛው የዓለም ጦርነት 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ አፅንኦት ተሰጥቶት የተወሳ ጉዳይ ነበር ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic