የአንባዥ ሱስ-እፀዋት ፍጆታና አንፃሩ ትግል | ኤኮኖሚ | DW | 01.07.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአንባዥ ሱስ-እፀዋት ፍጆታና አንፃሩ ትግል

የተባ መ ድርጅት ዘንድሮ በአብሾ/ማለት በአንባዥ ሱስ-እፀዋት ፍጆታ አንፃር ለሚያካሂደው ትግል “ሕክምና ይረዳል” የተሰኘውን ርእስ ነው የሰጠው። መርዘኛ የሱስ እፀዋትን እና ከዚህ ጋር የተያያዘውን ወንጀል ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ሊጠናከር ይበቃ ዘንድ፣ ሰኔ ፲፱፣ ፲፱፻፺፮---ያለፈው ቅዳሜ መሆኑ ነው---አነቃቂ ቀን እንዲሆን ያወጀው የተባ መ የመርዘኛ እፀዋትና ወንጀል መታገያ ተቋም፣ በመርዘኛው ሱስ የነበዙት አብሾኛዎች በሕክምናው ዘዴ እየተጠቀሙ ከዚ

��ው ጠንቀኛ ሱስ እንዲላቀቁ ለማግባባት ይጥራል። ትግሉ በተለይም ሄሮይንን እና ኮካኢንን የመሳሰሉት፣ ጠንካሮቹ የአንባዥ ሱስ እፀዋት በመላው ዓለም ውስጥ የወንጀለኛ ድርጅቶች መነገጃ የሚሆኑበት ሰንሰለት የሚበጠስበትንም ሁኔታ ነው የሚመለከተው።

እስካሁን ድረስ እንደታየው፣ የሚደረጁት ሀገሮች የመርዘኛ ሱስ እፀዋት አምራቾች፣ እንዱስትሪ-ሀገሮች ደግሞ ተቀባዮችና ፍጆተኞች የሚሆኑበትን ሚና ይዘው ነበር የቆዩት። ግን ሁኔታው አሁን ተለዋውጧል። ዛሬ ላኦስን፣ ኮሎምቢያን፣ በተለይ ደግሞ አፍጋኒስታንን በመሳሰሉት፣ ኦፒዩም፣ ኮካኢንና ሌሎችም መርዘኛ የሱስ እፀዋት በሚመረቱባቸው ሀገሮች ውስጥ ሕዝቡ ራሱ የአደገኛው ሱስ ሰለባ የሚሆንበት ዝንባሌ እየጎላ ነው የተገኘው።

እስያዊቱ ሀገር ኣፍጋኒስታን ዛሬ በሄሮይን አምራችነት ረገድ በዓለም አንደኛውን ቦታ ነው የያዘችው። በመላው ዓለም ውስጥ ለሕገወጡ ገበያ ከሚቀርበው ጠቅላላ ኦፒዩም ፸፭ በመቶው አፍጋኒስታን ውስጥ ነው የሚመረተው፣ ከ፴፪ቱ የአፍጋኒስታን ክፍላተሀገር ፳፰ቱ ሞን የተሰኘውን የሱስ እጽ ያመርታሉ። ጦርነት ሲፈራረቅባት የቆየችውና አሁን ብሔራዊውን መልሶ ግንባታ ለማራመድ የምትጥረው አፍጋኒስታን ይኸው የመርዘኛ ሱስ እፀዋት ምርትና ፍጆታ ከባድ እክል ነው የሆነባት። የዚያችው ሀገር መሪ ሃሚድ ካርሳይ ችግሩን እንዲህ ነው የሚያዩት፥ “........ማንም ሰው፣ በተለይ ደግሞ ማንም መንግሥት የመርዘኛ አብሾ ሸቃጭ ተብሎ እንዲሰደብ አይፈልግም፤ እኛ በአትክልት አምራችነት ወይም በሌሎች የግብርና ውጤቶች ዝናን ብናተርፍ ነው ደስ የሚለን፤ አሁን ታዲያ የመርርዘኛ ሱስ እፀዋትን ምርት ለማጥፋትና ለሕዝባችን አዲስ የኑሮ መሠረት ለመፍጠር እንበቃ ዘንድ፣ የዓለም ኅብረተሰብእ ርዳታ እንዲጠናከር አሳስባለሁ።”

በመርዘኛ ሱስ እፀዋቱ ፍጆታ የሚነብዙት አፍጋናውያን አሃዝ በየጊዜው ነው የሚጨምረው። ለአብሾ እፀዋቱ ኮንትሮባንድ ንግድ መሸጋገሪያ በሆኑት በሁለቱ ሀገሮች ፓኪስታንና ኢራን ውስጥም ነው የሱሰኞቹ አሃዝ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሲገዝፍ የቆየው። እንዲያውም፣ ዛሬ በእነዚያው ሀገሮች ውስጥ ያለው የሱሰኞች አሃዝ በአውሮጳና በዩኤስ-አሜሪካ ካለው ድምር የሱሰኞች ይዘት የላቀ መሆኑም ነው የሚመለከተው። ኢራን ውስጥ ዛሬ ሁለት ሚሊዮን የኃይለኛ አብሾ ሱሰኞች እንዳሉ በይፋ ቢነገርም፣ ታዛቢዎች አሃዙን ቢያንስ ከ፴ በመቶ አብልጠው ነው የሚያዩት።

በብሔራዊ ኤኮኖሚ አኳያ ሲታይ፣ የሱስ እፀዋቱ ፍጆታ ለአምራቾቹም ሆነ ለአሸጋጋሪዎቹ ሀገራት ከባድ ጉዳት ነው። ድህነት፣ ተሥፋአልባነት እና የሱሰኞቹ የልማት ተሳትፎ ጉድለት በሚሊያርድ ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ነው የሚያጓድደው። ከዚህም የተነሳ፣ አሁን ዓለምአቀፍ የርዳታ ድርጅቶችም እንደሚገነዘቡት፣ የመርዘኛ ሱስ እፀዋትን ፍጆታ ለመታገል፣ የልማት ፖለቲካ ጽንሰሐሳቦች እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሆኑት።

ለምሳሌ የጀርመን የኤኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴር መሥሪያቤና የጀርመኑ የቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት አፍጋኒስታን ውስጥ አዲስ መርሐግብር ነው የዘረጉት። በዚሁ ፕሮዤ አማካይነት ሕዝቡ በመርዘኛ ሱስ እፀዋት ፈንታ ሌላ አማራጭ ግብርና እንዲከተል ይደረጋል። በጀርመን ቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት/በአሕጽሮት GTZ ዘንድ “ልማትን መሠረት ያደረገ የሱስ እፀዋት ቁጥጥር” ለተሰኘው መርሐግብር የፕሮዤ መሪ የሆኑት ክሪስቶፍ ቤርክ እንደሚሉት፥ ባለፈው ዓመት በአፍጋኒስታን ርእሰከተማ ካቡል የተጀመረው ትንሽ ፕሮዤ አደጋው በተለይ ለሚያሠጋቸው ሴቶች እንዲበጅ የታሰበ ነው። የመርዘኛው ሱስ(ለምሳሌ የኦፒዩም ወይም የሄሮይን) ጥገኞች የሆኑት ወገኖች ከዚሁ አደገኛ ሱስ እንዲላቀቁና ከመርዙ እንዲነፁ፣ ወደ መታከሚያና ማገገሚያ ማዕከላት እንዲወሰዱ በማድረግ ይረዳል የካቡሉ ፕሮዤ። ግን የተረጅዎቹ ሰዎች አሃዝ በጣም የተገደበ ነው፣ ሆኖም በፕሮዤው መጀመሪያ ዓመት የተከናወነው ሥራ በጣም የተሳካ ሆኖ ነው የተገኘው።

በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ የመርዘኛ እጽ ሱሰኞችን በሕክምናው እንክብካቤ አማካይነት ከዚሁ አደገኛ ሱስ ለማላቀቅና እንደገና ምርታማ ኃይል ወደሚሆኑበት ጤናማ ኑሮ ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት ረገድ በአውሮጳና በዩኤስ-አሜሪካ የተገኘው ተሞክሮ ነው መሠረት የሚሆነው። ተሞክሮ እንደሚያሳየው፥ የመርዘኛ እጽ ሱሰኞችን ከዚያው የጠንቅ ቁራኛ ለማላቀቅ የሚወሰደው የሕክምናው ርምጃ ሊሠምር የሚችለው፣ ሱሰኞቹ ከዚያው ጠንቅ እየተላቀቁ በሚነፁበት ጊዜ አዲስ መጻኢ እንደሚኖራቸው ግልጽ ሲደረግ፣ በማኅበራዊው ኑሮ ውስጥ እንደገና የሚዋሃዱበት መንገድ ሲቃና ብቻ ነው። አለበለዚያ ግን ሱሰኞቹ አደገኛውን መንገድ እየተው የሕክምናውን መስመር እንዲከተሉ ማግባባት የሚቻል አይሆንም። የመርዘኛ እጽ ሱሰኛነት ዛሬ በተለይ የድህነት ጥያቄ ሆኖ ነው የሚታየው።

ከአብሾው መርዝ ሱሰኛነት ጎን፣ የኤድስና የኤድስ ተሃዋሲ መስፋፋትም ነው የጎልማሶችን የኑሮ ዕድል የሚሰብረው። እንዲያውም፣ ዛሬ በያለበት የአምራቹን ኅብረተሰብ ከፊል ለአደጋ የሚዳርገው ኤድስና የኤድስ ተሃዋሲ ችግር የብልሹው ምዕራብ ፈንታ ነው ስትል የነበረችውም ወግአጥባቂ ኢራን እንኳ ዛሬ አመለካከቷን የቀየረች ሆና ነው የምትታየው። ዛሬ በዚያችው ወግአጥባቂ ሀገር ርእሰከተማ ቴህራን የመርዘኛ እጽ ሱሰኞች ከየመንገዶች ዳርቻ እየተለቀሙ ከዚያው አሥጊ ሁኔታቸው የሚላቀቁበት ርዳታና ሕክምና እንደሚደረግላቸው ማግባቢያ ዘመቻ ይካሄዳል። የኢራኑ ጽንሰሐሳብ ጀርመንም ውስጥ ለአደገኛ ሱስ ጥገኞች ከደረጀው ልዩ የሕክምና ዘዴ ጋር የሚመሳሰል ሆኖ ነው የሚታየው።

ለአደገኛ ሱስ ጥገኞች ማዳኛና መንከባከቢያ ጀርመን ውስጥ የተዘረጋው መርሐግብር የተመራዦቹ ሟቾች አሃዝ በተለይ ከ፲፭ ዓመታት ወዲህ እጅግ ዝቅተኛ እንዲሆን ለማድረግ ማስቻሉን ለዚሁ የጤንነት አገልግሎት የተመደበው መሥሪያቤት አሁን ለማረጋገጥ ችሏል። ጀርመን ውስጥ የአብሾ ወይም የመርዘኛ እጽ ሱሰኞችን ከዚያው መርዝ ለማላቀቅ ከሚሠረባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ ሜታዶን የተሰኘውን ጉዳትአልባውን አማራጭ ሥራይ የሚመለከት ነው። ከዚሁ ጎንለጎን ሥነልቡናዊው እንክብካቤ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ነው ያለው። ከዚህም በላይ፣ በአደገኛው ሱስ የተመረዙት ወገኖች ቀስበቀስ ወደ ኅብረተሰቡ ጤናማ አኗናር እንዲመለሱ ለማድረግ መጀመሪያው እርከን ይሆን ዘንድ፣ እነዚሁ ሱሰኞች በልዩ ክፍሎች ውስጥ ሆነው በከፍተኛ ቁጥጥርና በንፁሕ መርፌ ሥራዩን አካላቸው ውስጥ እንዲዶሉት ይፈቀዳል፣ ግን ዓላማው የኋላ ኋላ ጥገኞቹን ከዚሁ አደገኛ ሱስ ሙሉ በሙሉ ማላቀቀ ነው።

አፍጋኒስታንን ከአደገኛው የሱስ እፀዋት ምርትና ፍጆታ ለማላቀቀ፥ በአውሮጳውም ኅብረት በመደገፍ የሚጥረው የጀርመኑ ቴክኒካዊ ትብብር ድርጅት/ጂቲዜድ እንደሚለው፣ ያው ጠንቀኛ ተክል ጦርነት ላመሰቃቀላት ሀገር ሰላማዊ ዕድገት ከባድ እክል ነው የሆነው። ከሀገሪቱ ጠቅላላ ብሔራዊ ውጤት ግማሽ ያህሉ የሚመነጨው ከመርዘኛ ሱስ እፀዋቱ ሽያጭ ነው ይባላል። ድርጅቱ እንደሚያስገንዝበው፣ ክልከላና ቅጣት ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም፥ በዚህ ፈንታ ገበሬዎቹ ወደ ጤናማው የእርሻ ሙያ እንዲቀለበሱ ማግባባትና በዚሁ አግጣጫ በሚዘረጋላቸው የእርዳታ መርሐግብር እንዲተማመኑ ማድረግ ነው የሚያዋጣው።

ተዛማጅ ዘገባዎች