የአንበጣ ወረራ በአፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 09.09.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአንበጣ ወረራ በአፍሪቃ

ሰሞኑን በመገናኛ-ብዙሃንም በሰፊው እንደተዘገበው፣ ባሁኑ ጊዜ ምዕራባዊውን የአፍሪቃ ከፊል የወረረው የአንበጣው መንጋ የያዘው ግዝፈት ከ፲፭ ዓመታት ወዲህ ታይቶ አይታወቅም ነው የሚባለው። የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ እንደሚለው፣ በሳሕል አካባቢ ባሉት በድሆቹ ሀገሮች ውስጥ ሰብልን ግጦ የሚጨርሰውን ይህንኑ ግዙፍ የአንበጣ መንጋ ለመታገል ብዙ ሚሊዮን ዶላር ነው አስፈላጊ የሚሆነው። ማዕከላዊ መሥሪያቤቱን በሮማ ያደረገው ፋኦ የአንበጣን ወረራ

የአንበጣ ወረራ በሞሪታንያ

የአንበጣ ወረራ በሞሪታንያ

�ደት አስቀድመው የሚገመግሙት ጠበብቱ የሚያቀርቡለትን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ከሣምንታት በፊት ጀምሮ ነው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሲያቀርብ የቆየው።

የአንበጣው ወረራ ከሚያዋክባቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች መካከል በተለይ ሞሪታንያ ናት እጅግ ከባዱ ጉዳት የደረሰባት። በዚያችው ሀገር ውስጥ ከሰብሉ እስከ ፹ በመቶ የሚሆነው ከፊል እንደተደመሰሰ ነው የሚነገረው። ከዚህም የተነሳ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ርዳታ እንዲሻ ግዴታ ነው የሆነው። በዚያው በአፍሪቃው ምዕራብ በግዙፉ የአንበጣ መንጋ የተወረረችው ትንሽቱ ሀገር ጋምቢያ በዚሁ አደጋ ምክንያት ብሔራዊውን የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ እስከማወጅ ነው የደረሰችው። የአንበጣው ወረራ አሁን በዚያው አካባቢ ወደ ማሊ፣ ወደ ኒዤር እና ወደ ናይጀሪያም እየተሸጋገረ ነው የተገኘው። ወረራው የአህጉሩንም ምሥራቅ የሚያሠጋ ሆኖ ነው የሚታየው።

አንድ ግዙፍ የአንበጣ መንጋ እስከ ፹ ሚሊዮን የሚደርሱ አንበጣዎችን እያግተለተለ የሚወርረውን አካባቢ በሙሉ የሚሸፍን እንደመሆኑ መጠን፣ ሰብሉንና መስኩን ሁሉ በቅጽበት ግጦ ነው ባዶ የሚያስቀረው። እንዲያውም አንድ የአንበጣ መንጋ በአንድ ቅንጣት ቀን ብቻ ለአእላፍ ሰዎች ቀለብ የሚበቃውን እህል ነው የሚደመስሰው። መስኮች ጭምር ናቸው በቅጽበት ተግጠው ባዶ የሚቀሩት። በአካባቢው እጅግ ከባዱ የአንበጣ ወረራ በደረሰባት ሞሪታንያ ርእሰከተማ ኑአክሾት፥ ሌላው ቀርቶ በየመንገድ ዳር ያሉት ዛፎችና የእግር ኳስ ሜዳው ሣርም በአንበጣው መንጋ እንደተገጠቡ ነው የሚነገረው።

የአንበጣውን መንጋ እጅግ አደገኛ የሚያደርገው፣ አረንጓዴውን ሁሉ ለመጋጥ ያለው ግዙፍ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የፈጣን እንቅስቃሴ ኃይሉና እጅግ ተፋጥኖ የሚባዛበት ባሕርዩም ነው። አንድ የአንበጣ መንጋ በተለይ ከነፋስ ጋር እየከነፈ፣ በአንድ ቀን ብቻ እስከ ፩፻፴ ኪሎሜትር የሚደርስ ርቀት ነው የሚያቋርጠው። የመራባቱንና በፍጥነት የመባዛቱን ሁኔታ የሚያመቻችለት፥ ሙቁና እርጥቡ አየር ነው። ጠበብቱ እንደሚሉት ከሆነ፣ በሚቀጥሉት ቀናት አዲሱ አንበጣ ከየምድሩ ቀዳዳ እየተፈተለከ እንደሚኮለኮል ነው የሚጠበቀው። አንድ የአንበጣ መንጋ በ፲፪ ሣምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ይዘቱን በአሥር እጅ ሊያገዝፈው እንደሚችል ይታወቃል።

አንበጣው ከተወለደ በኋላ በመጀመሪያ አረንጓዴ ነው የሚሆነው፤ ክንፍአልባም ነው፣ ወዲያ ወዲህ የሚንቀሳቀሰው እንደ ፌንጣ በመዝለል ነው። እንደየአካባቢው ፀባይ መጠን በኋላ ቀለሙ ወደ መጋላነት ይለወጣል፤ ክንፍም ያወጣል፣ ተሰባስቦም መንጋ ይፈጥራል። ባለፈው ዘመን የሥነሕይወት ተመራማሪዎች አረንጓዴዎቹና ቡኒዎቹ አንበጣዎች ሁለት የተለያዩ ዓይነቶች እንደሆኑ ለረዥም ጊዜ ሲያምኑ ነበር፤ ግን ይህ እንዳልሆነ አሁን ግንዛቤው የጎላ መሆኑ ነው።

በዚሁ አደገኛ የእህልና የእፀዋት ፀር አንፃር የሚደረገው ትግል ቀላል አይደለም። ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ በጣም ፍቱን ሆኖ የተገኘው መከላከያ ዘዴ፣ በአንበጣው መንጋ ላይ ፀረተባዩን ንጥረነገር ከአየር መርጨት ነው። ይሁን እንጂ፣ ብዙዎቹ አፍሪቃውያን መንግሥታት በአውሮጵላኖች አማካይነት ፀረ-አንበጣውን ዘመቻ ለማካሄድ አቅም አይኖራቸውም። አንዳድ ገበሬዎች፥ ማሳውን መልሰው በመጎልጎል ምድር ውስጥ የተከማቹትን የአንበጣ እንቁላሎች ለመደምሰስ ይጥራሉ፣ ሌሎቹ ገበሬዎች ደግሞ ከጭንቀታቸው የተነሳ፥ በአካባቢው እሳት በመለኮስ፥ ወይም ድንጋይ በማጋጨትና አስቃጥላዎችን በመነረት የአንበጣውን መንጋ ለማስፈራራትና ምድር ላይ እንዳያርፍ ለማድረግ ይታገላሉ፤ ግን ተሞክሮ እንደሚያሳየው ይኸው የጥንት መከላከያ ዘዴ እምብዛም የሚያዋጣ አይደለም።


የአንበጣው ወረራ ክፉኛ ከሚያሠጋቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሀገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ቤኒን አሁን ያንኑ ከባድ አደጋ ለመከላከል አጣዳፊውን ዝግጅት እንዳደረገች ነው የሚነገረው። ትልቂቱም የቤኒን ጎረቤት ናይጀሪያ የአንበጣው ወረራ አሁን ወደ ሰሜን-ምዕራብ ጠረፏ የተሸጋገረ መሆኑን አስታውቃለች። ይህንኑ መዓት በጥንካሬ ለመታገልና የእህልን ውድመት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ፣ ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንዲዋጣ ዓለምአቀፍ ጠበብት አሁን ማሳሰቢያቸውን በማጉላት ላይ ነው የሚገኙት።

የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ ሰሞኑን ሮማ ላይ የሰጠው መግለጫ፥ አፍሪቃ ውስጥ የአንበጣው ወረራ በተባባሰባቸው አካባቢዎች ከአየርና ከየብስ ፀረተባዩን ንጠረነገር አባቅቶ ለመርጨት ይቻል ዘንድ፣ ለጋሽ መንግሥታት በተጨማሪ አንድ-መቶ ሚሊዮን ዶላር እንዲያዋጡ በጥብቅ ያሳስባል። “ በዚያው የአፍሪቃ ከፊል ለሚሊዮኖች የምግብ ዋስትና ሁኔታ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ቀጣዩን ሰብል በተቻለ መጠን ከንበጣው ወረራ ለማዳን ነው አሁን ዋና ጥረት መደረግ ያለበት” ይላል የዓለሙ ድርጅት ማስገንዘቢያ። በፋኦ ግምገማ መሠረት፣ በ፫፻ ሚሊዮን ዶላር የሚታሰብ የእህል ውድመት ካደረሰው ከ፲፱፻፹ው የአንበጣ ወረራ ይልቅ የዘንድሮው በይበልጥ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚያሠጋው።

ባለፈው ዓመት አፍሪቃ ውስጥ በሣህል አካባቢ፣ ዘንድሮ ደግሞ በሰሜን-ምዕራብ አፍሪቃ እምብዛም ባልተለመደ አኳኋን የጣለው አለቅጥ ከባዱ ዝናም፣ እንደ ፍንዳታ ለሚቆጠረው የአንበጣ ወረራና ለመንጋውም አለቅጥ ፈጣን ተከታታይ ግዝፈት እጅግ ምቹውን ሁኔታ ነው የፈጠረለት። እስከ ሰማንያ ሚሊዮን የሚደርሱ አንበጣዎችን የሚያግተለትለው ግዙፉ ፀረሰብል መንጋ ልክ እንደ ጥቁር ደመና ሰማይን እያለበሰ ወደ ምድር ወርዶ አንድ ኪሎሜትር-ካሬ በሚሆነው ሥፍራ ላይ በሚነጠፍበት ጊዜ ሁሉን ነገር ግጦ ባዶውን ነው የሚያስቀረው። ከዚሁ ከግዙፉ የአንበጣ መንጋ የሚለጥቀው ክንፍአልባው የፌንጣዎች መንጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመብረር ሲበቃ አካባቢው በሙሉ--ዛፉ ቅጠሉ ሣሩ ሳይቀር--ገጣባ ሆኖ ይቀራል።

በቀን ከአንድ-መቶ ኪሎሜትር በላይ ለማቋረጥ የሚችለውን የአንበጣውን መንጋ ሌላው ቀርቶ ባሕር ወይም ግዙፉ በረሃ እንኳ ከክንፈት አያግደውም። በዚህ አኳኋን፣ አሁን ጠበብት በጥብቅ እንደሚያስጠነቅቁት፣ ወደ ደቡባዊው የእስያ አካባቢም ተሸጋግሮ ሰብልን የሚያሟጥጥ እንደሚሆን ክፉኛ ነው የሚያሠጋው። የተባ መ የምግብና የእርሻ ድርጅት/ፋኦ እንደሚለው ከሆነ፣ ገስጋሹ የአንበጣ መንጋ ወደ አፍሪቃው ምሥራቅም ተሸጋግሮ ሱዳን ምድር ላይ ከሰፈረ፣ ከዚያው ተነስቶ ቀይ ባሕርን በማቋረጥ፣ ወደ ዓረብያው ባሕር-ወሽመጥ ለመሸጋገርና ከዚያም ቀጥሎ ወደ ኢራን፣ ወደ ፓኪስታን እና ወደ ሕንድ ሊግበሰበስ እንደሚችል ነው የሚገመተው።