የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ፤ትምሕርት ቤቶችን የመክፈት ዝግጅት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 23.10.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ፤ትምሕርት ቤቶችን የመክፈት ዝግጅት

መንግሥት ችግሩን ለመከላከል የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተቸቱ አልቀረም።«ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ»የተባለው ፓርቲ ሃገሪቱ ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆኗ እየታወቀ መንግስት በቂ መድኃኒት የሚረጩ አውሮፕላኖችና መድሀኒት አላዘጋጀም፤ሀላፊነቱን ሳይወጣ የገበሬው ሰብል በበረሀ አንበጣ ተበልቷል ሲል ወቅሷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:16

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ኢትዮጵያ ከ25 ዓመታት ወዲህ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንበጣ መንጋ ሰፊ አካባቢን ወሯል። በአማራ በኦሮምያ በትግራይ በአፋርና በሶማሌ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንበጣ ከግማሽ ሚልዮን ሄክታር የሚልቅ የእርሻ ማሳና የእንስሳት ግጦሽ መሬትን መውረሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል ። አምስት ክልሎች እና አንድ የከተማ አስተዳደርን ያዳረሰው የአንበጣው መንጋ በርካታ የደረሰ ሰብል እያወደመ ነው። በአውሮፕላንና ሄሊኮችተሮች የታገዘ የፀረ-አንበጣ ኬሚካል ርጭት እንዲሁም መኪናና የሰው ኃይል በማሰማራት ወረራውን የመከላከል ጥረቱ መቀጠሉን ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴ ኤታ በተለይ ለዶይቼ ቨለ በዚህ ሳምንት ገልፀዋል። ሆኖም ዶክተር ማንደፍሮ የገንዘብ እጥረት ባይኖርም ፀረ-አንበጣ ኬሚካል ከሚረጩ አውሮፕላኖች ሁለቱ መከስከሳቸው ሶስቱ ደግሞ በመለዋወጫ ዕቃዎች ችግርና በብልሽት ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸው የመከላከል አቅሙን እንደቀነሰው አስረድተዋል::
መንግሥት ችግሩን ለመከላከል የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መተቸቱ አልቀረም። «ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ»የተባለው ፓርቲ  በትዊተር በኢትዮጵያ አምስት ክልሎች የተከሰተው የበረሀ አንበጣ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጾ ሃገሪቱ ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆኗ እየታወቀ መንግስት በቂ መድኃኒት የሚረጩ አውሮፕላኖችና መድሀኒት አላዘጋጀም፤ሀላፊነቱን ሳይወጣ የገበሬው ሰብል በበረሀ አንበጣ ተበልቶ ረሀብ ሲመጣ ይህ ረሀብ ሰው ሰራሽ ረሀብ ነው ብሏል።ባልደራስ መንግሥትን ተጠያቂ ባደረገበት በዚህ መልዕክቱ « የግብርና ባለሙያዎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ገበሬው ይህንን መንጋ ለመከላከል ጥረታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠየቆ ፣ በዚህ ጊዜ ከገበሬው ጎን በመቆም ሚችሉት ሁሉ ድጋፍ

እንዲሰጡ ባልደራስ ከአደራ ጋር ለደጋፊዎች ጥሪ አስተላልፏል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራን አለመሥራት ያስጠይቅ የሚለውን መልዕክታቸውን ያስቀደሙት ያሬድ ኃይለ መስቀልም «አንበጣ ከመጣ ዓመት ሞላው ።ትንሽ ሳይንስ ለተማረ ሰው እንኳን የመጣው አንበጣ በልቶ እንቁላሉን ጥሎ ነው የሞተው።ለምን የአንበጣ መከላከያ ተከታትሎ ከምድር ሳይነሳ አላጠፋውም?ሲሉ ሞግተዋል። «በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በጊዜ የማሰብ ማቀድና ተግባራዊ የማድረግ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ ባለሥልጣናት ምክንያት ይህን መሰሉ ጉዳት ሲደርስ አያሳዝንም?በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል።
በዚህ ሳምንት ሰኞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስና ማብራሪያ ላይ ስለ አንበጣ የሰጡት ማብራሪያ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ብዙ አነጋግሯል።ዐቢይ በፓርላማው ስብሰባ «አንበጣ የመደመር ፍልስፍናን በትክክል አፕላይ ያደረገ «የተገበረ»ሰራዊት ነው።»ማለታቸው  ትችቶችን አስተናግዷል።  ፍጹም በትዊተር ህዝቡ የሚጠይቀው እረ ገበሬውን ከዚህ ጉዳ እናውጣ፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ የመደመር ሃሳብ ገብቶታል አንበጣ በማለት ጽፏል
ቅድስት ጤናዬ በትዊተር «በረሃብ ሲቃ ላይ ባለው ህዝብ ማላገጥ ዋጋ ይስከፍላል።የተራበ ህዝብ እና አንበጣ ምን አገናኘው?ለተራበው ህዝብ መድረስ ነው የሚሻለው? ወይስ አንበጣ መደመርን ያስተምራል ብሎ ማውራት? ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ብሮከር ያሲኖ በተቃራኒው በትዊተር «ያለን ምርጫ እንደ አንበጣው ተደምረን ወረራውን ለመመከት መረባረብ ብቻ ነው።ብሄር ክልል ወንዝ ሳይለይ ብለዋል።
ሒሩት በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት፣ ምድራችን ያየችው መከራ እጅግ ብዙ ነው!አንበጣ፣ኮሮና፣ጎርፍ ፣ዘረኝነት፣ረሃብ፣ጦርነት የፖለቲካ ሽኩቻ፣ ጥላቻ፣መሰደድ ፣ሞት !!ከእነዚህ አንዱ ውስጥ፣ እጃችን ካለ በእውነት ከአንበጣና ከኮሮና አንሻልም! እባካችሁ የህዝባችንን መከራ አናብዛ ሲሉ በመምከር ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
«ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ተወት አድርገን ተባብረን አንበጣዎችን እናጥፋ፣ገበሬዎችን ብቻ ሣይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንታደግ።»ያሉት ደግሞ ደሴ ላኮመልዛ ናቸው። አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ ክልሎች ትምሕርት ሚኒስቴር ባስቀመጣቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መሰረት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምሕርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው። ሌሎች ደግሞ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ይህም በዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያነጋግሩ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ነው። 

ኮንጎ ሰፈር በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት የተለያዩ ጥያቄዎችን አካቷል።። 
ሰሞኑን ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ይጀምራሉ ሲባል እሰማለሁ።ልዩ ጥንቃቄ ማለት ምን ማለት ነው ለትምህርት ቤቶች ሲባል የሚደረግ ልዩ ጥንቃቄ እስከዛሬ ድረስ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በመንግስት እየተሰጠን ካለው የጥንቃቄ መልእክት የተለየ ተጨማሪ ምን ጥንቃቄ ይኖር ይሆን እስከዛሬ ድረስ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በመንግስት እየተሰጠን ያለው የጥንቃቄ መልእክት በማህበረሰቡ የነበረው ተፈፃሚነት እስከምን ነበር ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ በተለምዶ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት የሚዛመተው ተራው ጉንፋን ማህበረሰቡን በሚያዳርስበት ሁናቴ ኮቪድ ስርጭት ቢስፋፋ ምን ታስቧል? ሰሞኑን የተለያዩ አገሮች ትምህርት ቤቶችን ከከፈቱ በኋላ የኮቪድ ወረርሽኝ በመስፋፋቱ ትምህርት ቤቶችን እንደገና መዝጋታቸው በተለያዩ የዜና ምንጮች እየተነገረ ነው እኛስ ከተመሳሳይ አገራት ምን ትምህርት መውሰድ ይገባን ይሆን ሲሉ ጠይቀው ለማንኛውም የሚዲያ ጋጋታ የሌለን እንዳለ ማድረግ በኮቪድ አይሰራም እና ሰብአዊ ጥፋት ከመድረሱ በፊት እውነት እውነቱን መነጋገር ይበጃል ይህ ሳይሆን ለሚከሰት ማንኛውም ጥፋት መንግስት በታሪክ ተጠያቂ ይሆናል።ሲሉ አሳስበዋል።ጊዜ ለኩሉ ኃይሉ ደግሞ ትምሕርት ይጀመር እንጂ አይዘልቅም ባይ ናቸው ።
«ጅምር እንቅስቃሴ አለ ከሁለትና ሶስት ሳምንት በኃላ እንደሚቆም ግን ያስታውቃል።ዩኒቨርስቲዎችን በተመለከተ ግን ከኮሮና በፊትም በግጭት ምክንያት እንዳቆሙ ዘንድሮም በዚሁ ምክንያት ትምህርት ያካሂዳሉ የሚል እምነት የለኝም«ብለዋል
ተስፋዬ ነጋ 
ደግሞ «እኔ እራሴ መምህር ነኝ ፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ብርሃነ ጊወርጊስ አንደኛ ደረጃ ት፡ቤት ።በት፡ቤቱ አልኮል እና ጭምብል የተሟላ ቢሆንም የተማሪ ወንበር አቀማመጥ ግን 1ለ5 ነው ነገር ግን የወረዳው የትምህርት አመራር ትምህርት እንድናስተምር ስላስገደዱን ፣እያስተማርን ነው ሲሉ የርሳቸውን ተሞክሮ ካካፈሉ በኋላ 
«በክልሉም ሆነ ባገር አቀፍ ት/ቤት ለመክፈት የሚደረገው ቅድመ ዝግጅት ከሚዲያ ፍጆታ ያለፈ አይመስልምና ለማንኛውም እኛ መምህራን ድሮም ሻማ ነንና አሁን ደግሞ ለመቀጣጠል ተዘጋጅተናል ብለዋል።ከበደ ወርቁ ደግሞ በአጋጣሚው ቅሬታቸውን ገልጸዋል።« የትምህርት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ሆይ በኢትዮጵያ ሀገራችን በጣም ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች ሞልተዋል ።ነገር ግን በመንግሥት እንደ ዜጎች የሚታዩ አይመስሉም።»

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic