የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 08.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ ኢትዮጵያ

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖችም በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በስድት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ባለ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኃላፊ ለዶቼ ቬለ DW ገልፀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03

«የመከላከል ጥረቱ ቢቀጥልም በቁጥጥር ሥር አልዋለም»

ከሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ የተገኘው የአንበበጣ መንጋ ወረርሽኝ በምሥራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባሉ በርካታ ወረዳዎች መከሰቱን ታውቋል። በመንጋው በተለይ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ የሚረዱ ባህላዊና ዘመናዊ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተገልፃል። ለDW አስተያየት የሰጡ የምዕራብና ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንደናገሩት ከሰሞኑ በየዞኑ ባሉ በርካታ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የተለያየ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል። በተለይ የምዕራብ ሀርጌ ዞን የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኃላፊ አቶ አነስ አልይ በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ላይ ተከስቷል ያሉት የአንበጣ መንጋ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በሚገኝ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተናግረዋል። በምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ስምንት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው አንበጣ በርካታ ሄክታር በሸፈነ የዕፅዋት እና የደረሰ ምርት ላይ ማረፉን የተናገሩት በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ፅ/ቤት ባለሞያ የሆኑት አቶ አሸብር ለማ በበኩላቸው ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። በሁሉቱም ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጉዳትን ለመከላከል ተማሪዎች ጭምር የተሳተፉበት ባህላዊና ዘመናዊ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በሀገሪቱ በአብዛኞቹ አካባቢዎች የተከሰተውን ይህን የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ አስቀድሞ መከላከል አይቻልም ነበር ወይ በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ሞያዊ ምላሽም ሰጥተዋል። የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ድሬደዋን ጨምሮ በሶማሌ ክልል እና አሁን ደግሞ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የተከሰተ ሲሆን እየተደረገ ካለው የመከላከል ሥራ ባለፈ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አለመዋሉ ታውቋል። የድሬደዋው ዘጋቢያችን መሳይ ተክሉ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic