1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የአቶ ታዬ ደንደዓ የችሎት ውሎ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 2016

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ ጠበቆቻቸው ላይ ከመንግስት የሰላ ማስፈራሪያ በመድረሱ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ገለጹ ።

https://p.dw.com/p/4hUAL
Äthiopien Taye Dendeha
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ የቀረበው ክስ ጭብጥ

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ ጠበቆቻቸው ላይ ከመንግስት የሰላ ማስፈራሪያ በመድረሱ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ገለጹ ። አቶ ታዬ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ላይ ቀርበው እንዳስረዱት «አቃቤ ሕግ እና ሰዎቻቸው» ባሏቸው አንድም ጠበቃ እንዳይቆምላቸው በጠበቆቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሷል ። የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም የሰጠው የንብረት ማስመለስ ትዕዛዝም አለመከበሩን አንስተው ቅሬታቸውን አሰምተዋል ።

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በልደታ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በፊት ግንቦት 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት በሕጋዊነት ያልተመዘገበ የተባለው የጦር መሣሪያ ክስ ላይ የቀረቡትን የአቃቤ ሕግ ምስክር በመስማቱ፤ ከሳሽ አቃቤ ሕግ የቀረበውን የሰው ምስክር ከሰነዶች ማስረጃዎች ጋር በማበር የጥፋተኝነት ብይን ይሰጥልኝ ባለው መሰረት ጥፋተኝነት ላይ ውሳኔ ለመስጠትም ነበር ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ።

ይሁንና ዛሬ በተያዘው ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮውን የያዘው ችሎቱ ባሉት ተደራራቢ መዝገቦች ምክንያት መዝገቡን ለዛሬ ባለማድረሱ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚስፈልገው በማስረዳት በቀረቡት የሰው እና ሰነድ ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።

የአቶ ታዬ ደንደዓ የሰብዓዊ መብት ቅሬታዎች

ችሎቱ የዛሬው ዋና ጉዳይ የሆነውን ብይን የመስጠት ጉዳዩን ቀን ማራዘሙን ተከትሎ በዚያ ላይ ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው በማስረዳት፤ ነገር ግን ለችሎቱ አስተያየት የሰጡት ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ ሁለት መሰረታዊ ያሉት ጥያቄዎችን ለተሰየሙ ዳኞች አቅርበዋል፡፡

ተከሳሹ ለችሎቱ ያቀረቡት አንደኛው የመብት ጥያቄ ከዚህ በፊት ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ያቀረቡት ጥያቄ እና ያንን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ እስካሁን ተፈጻሚ አለመሆኑን ነው፡፡ በእለቱም ባቀረቡት ጥያቄ በምርመራ ወቅት በኤግዚቢትነት የተያዙ ብዙ ንብረቶች ብመለሱም ሁለት የእጅ ስልኮቻቸው፣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና መደመር ሲመረመር የሚል ረቂቅ ጽሁፍ ንብረቶቻቸው በመሆናቸው እንዲመለሱላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ብጠይቁም እስካሁን ፍርድ ቤቱ ሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ አለመከበሩንና ንብረቶቻቸው እንዳልተመለሱላቸው በምሬት ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም በዚህ ጉዳይ ላይ የአቶ ታዬ ደንደዓን ባለቤት አስተያየት እና ከፌዴራል ፖሊስ ተወክሎ ደብዳቤ ያቀረቡትን ሰው አስተያየት ካደመጠ በኋላ ንብረቶቹ በኤግዚቢትነት መያዝ እንደማይቸሎ በመግለጽ ሌላ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡

የአቶ ታዬ ደንደኣ "የጥብቅና መብት መከልከል”

አቶ ታዬ ደንደዓ በዛሬው ችሎት ያቀረቡት ሌላኛው የመብት ጥያቄ "አቃቤ ህግ እና ሰዎቻቸው” ባሏቸው ጠበቆቻቸው ላይ የሰላና ከባድ ያሉት ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደሚደርስ አስታውቀው ይህ እንዲቆም መጠየቃቸው ነው፡፡ አቶ ታዬ ለችሎቱ ባቀረቡት ቅሬታ መሰል ዛቻዎች ጠበቆቻቸው ላይ የሚደርሰው ከደህንነት መስሪያ ቤትም ጭምር መሆኑን አብራርተው አስረድተዋል፡፡

የቀደሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ "ከነበሩኝ አምስት ጠበቆች በሁለቱ ላይ ከባድ ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑን በደንብ ባውቅም በቀሪዎቹ ሶስቱ ላይ የሚደርስ ዛቻ ኑር አይኖር ለጊዜው የማውቀው ነገር የለኝም” በማለስ ተናግረዋልም፡፡

አቶ ታዬ ዛሬ ለችሎቱ ስቀርቡ ከዚህ በፊት በነበሩ ሁሉም ችሎቶች ላይ አብሮአቸው ስቀርቡ ከነበሩ ጠበቆቻቸው አንድም ሰው ባለመቅረባቸው ለችሎቱ አስተያየት የሰጡም በራሳቸው ብቻ ነው፡፡ አቶ ታዬ ዛሬ አንድም ጠበቃ ከሳቸው ጋር ላለመቅረቡም ያቀረቡት ምክንያት "ጠበቆቻቸው ላይ በተሰቦቻቸውን የመጉዳት ጭምር ማስፈራሪያ ስለምደርስ” ምናልባትም ህንኑን ሰግተው ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ይህን መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ነው ጥያቄ ያቀረቡት፡፡

አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደር
አቶ ታዬ ደንዳኣ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Haileselasi/DW

አቃቤ ህግ በዚህ ቅሬታ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡ ችሎቱ በፊናው ጠበቃ መወከል በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 20 ላይ እንደተቀመጠው ጠበቃ መወከል መብት መሆኑን በማስረዳት፤ መሰል ድርጊት ተፈጽመው ከሆነ ለፍትህ ስርዓቱም እጅግ ጎጂ መሆኑን አስገልዝቧል፡፡ ተከሳሽ የክስ ብያኔን ተከላከሉ እንኳ ብባል ጠበቃ የግድ አስፈላጊ መሆኑንም በማስረዳት ችሎቱ በጉዳዩ ላይ እንደሚመክር ነው ያሳወቀው፡፡

በአቶ ታዬ ደንደዓ ላይ የቀረበው ክስ ጭብጥ

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ"ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚል ሦስት ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል መባሉም ይታወቃል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ