1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የአቶ ታዬ ደንደአ የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆን

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2016

ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል፡፡ ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት ጠበቃ የኋላሸት ታምሩ ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ በዛሬው ችሎት ጠበቆቻቸው የቃቤ ህግ ክስ ላይ አቅርበውት የነበረው የክስ መቃወሚ ውድቅ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4g6od
የቀድሞዉ የሰላም ሚንስትር ደ ኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ የቀረባበቸዉን ክሥ ተቃዉመዋል
የፌደራሉ ክፍተኛ ፍርድ ቤት ልደተታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ሥርዓት ችሎት የአቶ ታዬ ደንደአን መቃወሚያ ዉድቅ አድርጎታልምስል Seyoum Hailu/DW

የአቶ ታዬ ደንደአ የክስ መቃወሚያ ውድቅ መሆን

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያን ውድቅ አደረገ፡፡ችሎቱአቶ ታዬ ያቀረቡትን ‘‘ክሱ የይሻሻልልኝ’’ ጥያቄን ውድቅ ያደረገው የክስ መቃወሚያቸውንና የዐቃቤ ህግ አስተያየትን መርምሮ በማየት ነው ተብሏል፡፡በዛሬው ችሎት አቶ ታዬ ደንደዓ በቀረበባቸው ክስ ላይም የእምነት ክደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል፡፡ ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት ጠበቃ የኋላሸት ታምሩ ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ በዛሬው ችሎት ጠበቆቻቸው የቃቤ ህግ ክስ ላይ አቅርበውት የነበረው የክስ መቃወሚ ውድቅ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

“አቶ ታዬ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ፣ የጨፌ ኦሮሚያ አባል እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ስለነበሩ የአለመከሰስ መብታቸው እንዲጠበቅ በሚል ክስ ሊመሰረትባቸው እንደማይገባ ተከራክረናል፡፡ ፍርድ ቤቱ ደግሞ ክሱ የተመሰረተው የአለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ ነው በሚል ውድቅ አድርጎብናል” ብለዋል፡፡

የአቶ ታዬ የእምነት ክደት ቃል

ፍርድ ቤቱ መቃወሚውን ውድቅ ካደረገ በኋላ አቶ ታዬ ከጠበቆቻቸው ጋር የሚማከሩበት ጊዜ ተሰጥቷቸው በዛሬው እለት በዋለው ችሎት በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት-ክደት ቃል ሰጥተዋል፡፡ ጠበቃቸው በዚህ ላይም አክለው በሰጡን አስተያየት “የቀረበባቸው የመጀመሪያ ሁለት ክሶች በማህበራዊ ሚዲያቸው ተጠቅሙ አሰራጩ ስለተባለው መረጃዎች በተመለከተ እንዲሁም የጦር መሳሪያን ይዘው መገኘታቸውን በማስመልከት ተግባሩን መፈጸማቸው፤ ነገር ግን አንድም ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው የእምነት ክደት ቃል ሰጥተዋል” ብለዋል፡፡ አቶ ታዬ "የጻፍኩት ጽሁፍ ፕሮፖጋንዳ አይደለም፤ ወንጀል አልፈጸምኩም" በማለት የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ስለመስጠታቸውም ተነግሯል።

ጠበቃ የኋላሸት አክለውም ከሳሽ ዐቃቤ ህግ አቶ ታዬ ክደው የሰጡትን የእምነት ክደት ቃል ተከትሎ ማስረጃዎችና ምስክሮች እንዲሰሙለት ተለዋጭ ቀጠሮ በመጠየቁ፤ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ብለዋል።

የተከሳሽ አቶ ታዬ  ሁለት ቅሬታዎች

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ታዬ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ሁለት ቅሬታዎች ላይ ችሎቱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡ “ከዚህ በፊት በምርመራ ጊዜ በኤግዚቢትነት የተያዙ ብዙ ንብረቶች ብመለሱም ሁለት የእጅ ስልኮቻቸው፣ አንድ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር እና መደመር ሲመረመር የሚል ረቂቅ ገጽሁፍ ንብረታቸው በመሆናቸው እነዲመለሱላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን እንደሚሰጥ መግለጹን” ያነሱት ጠበቃ የኋላሸት፤ አቶ ታዬ ከጤና እክል ጋር ተያይዞም ታስረው የሚቀርቡበት የእጅ ካቴና አላርጅክ እንደፈጠረባቸው ለችሎቱ ገልጸው ያ እንዲቀር ለማረሚያ ቤት አስተዳደር ትእዛዝ እንዲሰጥ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ይህንንም መርምሮ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ቃልመግባቱን አስረድተዋል፡፡

የአቶ ታዬ ደንደዓ ጠበቃ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለመጪዉ ግንቦት 29 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የቀድሞዉ የሰላም ሚንስትር ደ ኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ በሶስት የወንጀል ጭብጦች ተከስሰዉ ጉዳያቸዉ በፍርድ ቤት እየታየ ነዉምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ ሦስት ክሶችን ማቅረቡ ይታወሳል።ይኸውም ክስ፥ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ“ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚል ይገኝበታል፡፡

ሌላው የቀረበባቸው ክስ ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 5:00 ሰዓት ላይ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል የሚል ነው።

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ