የአቶ በቀለ ገርባ ጤንነት ″አሳሳቢ ነው″- ልጃቸው | ኢትዮጵያ | DW | 24.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአቶ በቀለ ገርባ ጤንነት "አሳሳቢ ነው"- ልጃቸው

በኦሮሞ ተቃውሞ ሳቢያ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ በቀለ ገርባ መታመማቸውን እና ሕክምና ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። አቶ በቀለን ቅዳሜ ታህሳስ 14 ቀን 2010 የጎበኟቸው ልጃቸው የጤና ሁኔታቸው "አሳሳቢ ነው" ብለዋል።

ወይዘሪት ቦንቱ እንደሚሉት አባታቸው ከዚህ ቀደም "አልፎ አልፎ" ያማቸው የነበረው የደም ግፊት አሁን በርትቶባቸዋል። "የራስ ምታት እና የአንገት ሕመም እንዳለበት ነግሮኛል" ብለዋል። "ትናንትና ሔጄ ስጠይቀው በጣም እንዳመመው ነው የነገረኝ። ቆሞ ራሱ ሊያዋራኝ አልቻለም። ቶሎ ነው የተመለስኩት" ያሉት ቦንቱ "ግፊቱ በጣም ከፍ ብሏል" ሲሉ አክለዋል።

"ሐኪም ቤት ውሰዱኝ ብሎ በተደጋጋሚ ሲጠይቃቸው ደግሞ ምንም መልስ አልሰጡትም። በመጨረሻም እንደ ስብሰባ ነገር አድርገው በፊት በቀን አንድ ጊዜ የሚወስደውን መድሐኒት አሁን ሁለት ጊዜ ያድርገው እና ይከታተል ብለው ወሰኑ። መድሐኒቱ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ ነው እንጂ ሁለት ጊዜ ከተወሰደ ሌላ ጉዳት ያመጣል ብሎ ደግሞ ሌላ ሰው ነገረው። እና መድሐኒቱን ሁለት ጊዜ መውሰዱን ተወው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። 

ሕክምና የተከለከሉበት ምክንያት እንዳልተነገራቸው የገለጡት ቦንቱ ጉዳዩን ነገ ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠበቃቸው በኩል ለፍርድ ቤት እንደሚያመለክቱም ተናግረዋል። "በተደጋጋሚ ሐኪም ቤት ውሰዱኝ ብሎ ጠይቋል። ሊወስዱት አልቻሉም። ስለዚህ በጠበቃችን በኩል ነገ ለፍርድ ቤት ልናመለክት ነው" ብለዋል።  

"ራሴን ያመኛል፣ አንገቴን ይይዘኛል አለኝ። ትናንትና ብዙም መጫወት ሁሉ አልቻለም። ሌላ ጊዜ እንደምናወራው አላወራንም። ቶሎ ነው የተመለሰው" ያሉት ቦንቱ የአባታቸው የጤና ሁኔታ "አሳሳቢ" እንደሆነባቸው ተናግረዋል። 

በድጋሚ ከታሰሩ ሁለት አመት ገደማ የሆናቸው አቶ በቀለ በ30ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያሳለፈውን ውሳኔ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም። ጉዳያቸው ከነገ በስቲያ ታኅሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ይታያል። 

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ 
 

ተዛማጅ ዘገባዎች