1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ለማ መገርሳ አቋም ፤ የመቀሌዉ ስብሰባ

ሰኞ፣ ኅዳር 29 2012

የማኅበራዊ መገናኛዎች ቅኝት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር የአቶ ለማ መገርሳ አቋምና «ሕገ-መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱን ማዳን» በተሰኘዉ የመቀሌዉ ስብሰባ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተጠናቅረዉበታል።

https://p.dw.com/p/3ULA4
Äthiopien Lemma Megersa, Verteidigungsminister
ምስል Prime Minister Office, Addis Ababa

«የሕዝብ አስተያየት»

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በመደመር ፍልስፍና ወይም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መዋሃድ እንደማይስማሙ መግለፃቸዉ ፤እንዲሁም «ሕገ-መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱን ማዳን» የተሰኘ ሀገር አቀፍ ስብሰባ ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይላት የተባለ መድረክ መመስረቱ ሳምንቱን የአብዛኞቹን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚዘግቡ መገናኛ ዘዴዎችን ትኩረት የሳቡ በርካታ አስተያየቶች የተሰነዘረባቸዉ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ በመደመር ፍልስፍና ወይም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መዋሃድ እንደማይስማሙ፤  ውህደቱን « ከመጀመርያ ጀምሮ የማላምንበት ጉዳይ ነዉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለየ ሃሳብ እንዳለኝም በተለያየ ጊዜ ገልጫለሁ፤ መዋሃዱ ትክክል አይደለም ከሆነም በችኮላ መሆን የለበትም» ማለታቸዉን ተከትሎ፤  ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ፤ የሀሳብ ልዩነት መኖሩ ተፈጥሮአዊ ነው ያሉት የፌስ-ቡክ ተከታታይ ሰዒድ አሕመድ አየለ ናቸዉ።  አቶ ሰዒድ እንደሚሉት  አቶ ለማ ሀሳባቸውንም በግልፅ መናገራቸውና ለዚህ መብቃታችን ተስፋ ነው። ከዚያ ባለፈ "ተሰሚነት የለኝም የሚሰማኝ የለም" ማለታቸው አልገባኝም። አቶ ለማ፤  ከብልፅግና የተሸለ ሀሳብ ከላቸው፤ ለህዝብ ያቅርቡ፤ ህዝብም መዝኖ ያንተ የተሻለ ነው፤ የሚል ይሁንታ ካገኙ፤ ተሰሚነት ተቀባይነት፤ ተፅዕኖ ፈጣሪነትዎ ሁሉ ይቀጥላል። አልያ የተሸለ ከመጣ ደግሞ ያን ማገዝ በራሱ ተሰሚነት ማስቀጠል ይመስለኛል። መልካም ሰርተዋል እና መልካሙን እመኝልዎታለሁ፤ ሲሉ አቶ ሰዒድ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ሞሃመድ ዘይን የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከዳር ያነጋገረው "ቲም ለማ" የለውጡ ዋና አራማጅ በኔ አስተያየት ያለወቅቱ መሰንጠቁ ይመስለኛል። ክቡር መከላከያ ሚንስትሩ የቲም ለማን ራዕይ ከዳር የማድረስ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ያለባቸውም ይመስለኛል ብለዋል።

Äthiopien Abiy Ahmed OPDO
ምስል Abdulbasit Abdulsemed

እንግዳ ወርቅ የተሰኙ የማኅበራዊ መገናኛ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤  ክቡር አቶ ለማ መገርሳ መከላከያ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት፤ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዓሊ አቅራቢነት ነው። ሆኖም ክቡር ለማ ሀሳባቸውን እየተቃወሙ ሳለ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር አብረው እየሰሩ ነው፤ ያ ደስ ይላል፤ ካልተጠራጠርን ማለቴ ነው። ...በሟቹ መለስ ዜናዊ ዘመን መከላከያ ሚንስትር ከነበሩት ውስጥ ጀነራል አባዱላ ገመዳ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አልስማማም ቢሉ ኖሮ ምን ይከሰት ነበር? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

በዲሞክራሲ ባህል የዳበረ ሀገር ቢሆን ኖሮ የተናገሩት ትክክል ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን በእኛ ሀገር ሁኔታ በተለይ በዚህ ጊዜ መገለፁ በህዝብ ላይ ውዠንብር እንዲፈጠር፣ መከፋፈሉ የበለጠ እንዲጨምር የሚያደርግ እና የህዝብን አቅጣጫ የማመላከት እንቅስቃሴ የሚያዳክም ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፤ ሲሉ የገለፁት ደግሞ ሽመልስ ታደሰ ይባላሉ።  በርግጥ ኦቦ ለማ ከፊት ሆነው የአሁኑን ፖለቲካ ከሚሾፍሩት አንዱ እደመሆናቸው ፖለቲካው የሚመራበትን ፍልስፍና አላቀውም ወይም አልተቀበልኩትም ማለት ትንሽ ግር ይላል፤ በማለት አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ሰይፉ ጋሊ አብዱራ ይባላሉ። ሰይፉ በመቀል ነገር ግን ይላሉ፤ ነገር ግን እንደተባለው በሽግግር ወቅት ውስጥ ደግሞ ነገሮች ባልተጠበቀ አኳኻን የፈጠኑ ከሆኑ የመጨረሻ ውጤታቸውን ከመስጋት አንፃር ፖለቲከኞች እራሳቸውን የሚያገሉበት ታክቲክም እንዳለ ደግሞ መታወቅ አለበት። ያም ሆነ ይህ የአቦ ለማ አካሄድ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተወስዶ አሁን ሰለታቀደው ውህደት አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ግልፀኝነት የመፍጠር የማሳወቅ ስራ መሰራት እንዳለበት ጥቆማ የሰጠ ይመስለኛል፤ ብለዋል።

ዛሬ እኮ የሀሣብ ልዩነታቸውን ይዘው ሀገር ለማገልገል ለሥራ ጉዳይ አሜሪካ ናቸው ድሮ ቢሆን ብለህ አሥብ? ሲሉ የሚጠይቁት ደግሞ ዳርሴማ ተመስገን ናቸዉ። በዚህ ለዉጥ ይላሉ ተመስገን በመቀጠል፤ በዚህ ለዉጥ ካልተደመርክ የኢትዮጵያን ጠልፎ መጣል ፓለቲካ አድናቂ ነህ ማለት ነው፤ ባይ ናቸዉ። ንጉሴ ሳሙኤል የተባሉ የፊስ ቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ ለማ ከልቡ ሳይሆን የተሰጠውን ገጸ-ባህሪ ነው የተወነው! ዐቢይ ውህደቱን ሲያፈጥነው ህዝቡ ደግሞ በለማ ጉዳይ እንዲጠመድ ሁን ብለው አብረው የሰሩዋት ሿሿ ነች፤ ሲሉ ሃሳባቸዉን አጠቃለዋል።

ፓስተር ተስፋዬ ሳላቶ የተባሉ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ የሐሳብ ልዩነት የዲሞክራሲ ባህሪ እንጂ መከዳዳት አይደለም። የሐሳብ ልዩነት ሲታፈን ዲሞክራሲ ይሞታል። አቶ ኦቦ ለማ መገርሳ ለብዙኃን ሐሳብ ቢገዙ ግን ለተፈፃሚነቱ ቢተጉ ክህደት አይደለም። ይህ ዓይነቱ መሰል ጉዳይ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው። ችግሩ ብዙ ደጋፊ አለኝ ዝነኛ ነኝ በሚል ቀቢፀ ተስፋ በሐሳብ የሚለዩ ሰዎች ይህንንም ለሌላ ሐሳብ ካዋሉ አካሄዱን ሕዝብ ይፈርዳል።

ሃይሉ ሲንሰበት የተባሉ እንደሚሉት ከሆነ፤ እኔን የሚያሳስበኝ የአቶ ለማ ውህደቱን መደገፍና አለመደገፍ አይደለም፡፡ ይልቅስ ኢሕአዴግ የተባለው ፓርቲ እላያችን ላይ እንዳይፈርስና አገራችንን ሌላዋ ሊቢያ፤ ሶማሊያ እንዳያደርግብን ብቻ ነው፡፡ እነሱ የራሳቸው ጉዳይ ነው፤ ብለዋል።

ለጨወታው ድምቀት መሰለኝ እንደዛ ያሉት ያሉት ደግሞ ሰለሞን ዘየንታ ይባላሉ። ሰለሞን በመቀጠል ለማ ካልሆነ እንኳ በድርጅታቸው እዛው ተወያይተው በድምፅ ብልጫ ውህደቱን ካፀደቁ በኋላ ለሚዲያ እኔ አልደግፍም ማለታቸው ተገቢ አልነበረም። ምክንያቱ የግል አቋማቸውን እዛው በድርጅታቸው አሳይተው ሊሆን ይችላል። መደገፍም አለመደገፍም መብታቸው ስለሆነ ነገር ግን ነገሩን ለማጮህ ይሁን ሌላ በድርጅታቸው ያለቀውን ጉዳይ ለሚዲያ እኔ አደግፍም ብሎ መነጋገር በዚህን ሰዓት ለሀገሪቱ ሰላም ጥሩ አይደለም። ችግርም ካለ በውይይት ለመፍታት ቢሞክሩ መልካም ነው፤ብለዋል። 

አቶ ለማ በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ የጉልበት ማርሽ ቀያሪ ነበሩ። አሁንም ትልቅ ተሰሚነት አላቸው። እሳቸውን ገሸሽ የሚያደርግ የፖለቲካ አካሄድ አገሪቷን ዳግም ወደ ቅርቃር ይመልሳታል፤ ያሉት ደግሞ ሪሳ ኪቶ ይባላሉ።  የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፤ አቋም መግለጽን ተከትሎ ከተሰጡት ሃሳቦች መካከል ከበቡሽ አበበ ያስቀመጡት አስተያየት የአብዛኞችን አሳብ የያዘ ይመስለናል። ሐገሬ ሰላምሽ ብዝት ይበል ይላሉ ከበቡሽ በመቀጠል፤ ለሐገራችን መሪዎች ልቦና ይስጣቸው። ሐገር መምራት ከባድ ነው። ፍቅሩን ያብዛላቸው እግዚአብሔር ሐገራችንን ይጠብቅልን። ሕዝቧንም ይባርክልን ዘረኝነት ይውደም ይውደም ይውደም ብለዋል።

«ሕገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱን ማዳን »

"ሕገ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓቱን ማዳን" በተሰኘ የ50 የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም የፌደራሊዝም ምሁራንና ሌሎች ተጋባዦች ተሳተፉበት የተባለዉ የሁለት ቀናቱ ጉባዔ የኢትዮጵያ ፌደራሊስት ኃይላት ፎሩምን በማቋቋም ረቡዕ ኅዳር 24፤ 2012 ምሽት መጠቃለሉን ተከትሎ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል

Äthiopien Konferenz zu Verfassung & Föderalismus
ምስል DW/M. Haileselassie

ዓለም ኢብራሂም ተመሰረተ እኮ? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ይጀምራሉ .... አይ ህወሀት? ዳግም በጥያቄ በቃ ጭር ሲል አልወድም የሚለው ባህሪዋ እኮ ነው የሚገርመኝ....በሌለ ሽብር የሽብር ህግንና አሸባሪ በአንድ ቀን ፈጥራ ለጥብስ የምታቀርብ ገራሚ ድርጅት ናት እኮ! በመገረም ቃል አጋኖን አስቀምጠዉ። የህወሓት አመራሮችና አባሎች እባካችሁ እውነት ለህዝብ ከቆማችሁ ለራሱ ለትግራይ ህዝብ ነፃነት የዕለት ዳቦ ስጡት። እናነት በዘራፋችሁት ጠግባችሁ አትጨቁኑት፤ ያሉት ደግሞ ትሻዊ ተፈራ ይባላሉ።

እዮብ አሻግሪ በበኩላቸዉ፤ የመቀሌዉን ስብሰባ በአዎንታዊ ጎኑ ያዩት ይመስላል። ደስ ይላል አሉ እዮብ አሻግሪ፤ ደስ ይላል ጭላንጭል ዲሞክራሲ እየታየ ነው በህውሀት ዘመን ይሄ አይታሰብም ነበር እኮ! ብለዋል።  የሌባ ስብስብ አይወክለንም ሲሉ አስተያየት የፃፉት ደሞ፤ ኩመል ዲን ናቸዉ። ጡረተኛ ሰብስባችሁ ኢትዮጲያን ዳግም ለመዝረፍ እምታደርጉት ጥረት መቼም እደማይሳካ እወቁ። አሁን መቀሌ የተሰበሰበው ሁሉ ዘረፋ የቀረባቸዉ ሰዎች ናቸዉ።
ኧረ ከመች ወዲህ ነው ህወኃት ዜጎች ሀሳባቸውን የሚገልፁበት የነፃ መድረክ ከፋታ የሚያውቀው? የተወደድከው የትግራይ ህዝብ ሆይ ለኢትዮጵያ አንድነት መታገል ነው የሚያዋጣህ! ሲሉም ያሳስባሉ። የግርማ ጉዲና አስተየያየት ደግሞ ፈገግ ያሰኛል፤  እነዚህ ሰዎች በስተርጅና ኮሚዲያን ሆነው አረፋት። በስተርጅና ጣራ ላይ አለ ሰራዊት ፍቅሬ ማስታወቂያ ሲሰራ ለካ ይሔ ታይቶት ነው። ማፈሪያዎች! ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ቦጋለ ሃይለየሱስ ናቸዉ። ህግ ቢኖር ኖሮ ትህነግን ማገድ ነበር እሚገባችሁ! ዛሬም ቡችሎችን በፍርፋሪ የሚደልል ፓርቲ መኖሩ ድንቅ ይለኛል! " ወራዳ " እንዳለው ሟቹ ወራዶች ናችሁ! የአብዮት ደምሴ አስተያየት አስታራቂ ሃሳብ የያዘ ይመስላል ፤ የተሻለ ሀሳብ ይዞ የሚመጣ ማንኛውም ሀሳብ የመደመጥና የመመረጥ እድሉ ሰፊ ነው። አሁን ኢትዮጽያውያን ይህን አመዛዝኖ ያሻውን የማንሳትና የመጣል መብት ባለቤት መሆን ጀምረዋል ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም ከራስ በላይ ህዝብና ሀገር ያለ ሁሉ በቅን ልብ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለው ሳይል ካረጀ ካፈጀ ፍረጃና ክስ ተላቆ አዲስ አስተሳሰብና ፓኬጅ ይዞ ለህዝብ ዳኝነት ማቅረብን መለማመድ አለብን።»

Äthiopien Konferenz zu Verfassung & Föderalismus
ምስል DW/M. Haileselassie

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ