የአተም ቅጥልጣይ ማሽኖች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 19.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአተም ቅጥልጣይ ማሽኖች

ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ ለኖቤል ሽልማት የበቁት 3 ተመራማሪዎች የአተም ቅጥልጣይ ማሽኖች (molecular machines) ንድፍ እና ውኅደት ላይ ባከናወኑት ጥልቅ ምርምር እንዲሁም ግኝት ነው። ለመኾኑ የአተም ቅጥልጣዮች እንደምን ማሽን ሊኾኑ ይችላሉ? የሽልማቱ መሠረታዊ ጥያቄ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:39
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:39 ደቂቃ

የኖቤል ሽልማት በኬምስትሪ ዘርፍ

ስዊድን የሚገኘው ሮያል የሣይንስ አካዳሚያ  ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት የሰጠው ለሦስት ተመራማሪዎች በጋራ ነው። ለሽልማት የበቁት ተመራማሪዎች ትውልደ-ብሪታኒያዊ አሜሪካዊው ሰር ጄምስ ፍሬዘር ስቶዳርት፤ በሽትራስቡርግ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ሊቁ ፈረንሳዊው ዦን ፒየር ሶቫሽ እንዲሁም የኔዘርላንዱ ፕሮፌሰር ቤርንሃርድ ኤል ፌሪንኃብ ናቸው። 

ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ ለሽልማት የበቃው ሥራ ያጠነጠነው የአተም ቅጥልጣዮችን ለማሽንነት ለማዋል የተደረገው የዓመታት ምርምር ነው። ከአንድ በላይ የኾኑ የአተም ቅጥልጣዮችን በመጠቀም ረቂቅ፥ደቂቅ ማሽኖችን ማበጀት እንደሚቻል የተጀመረው ምርምር ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ሰፊ እመርታን አስመዝግቧል። 

ሦስቱ የኬሚስትሪ ሊቃውንት ፍሬዘር ሽቶዳርት፣ ዦን ፒየር ሶቫሽ እንዲሁም ቤን ፌሪንኃብ በተለይ የደረሱበት ግኝት እጅግ አስደማሚ ተብሏል። እነዚህ ተመራማሪዎች የአተም ቅጥልጣዮችን በመጠቀም ከጸጉራችን አንድ ሺህ ግዜ ያኽል የቀጠኑ ረቂቅ ማሽኖችን ማበጀት ችለዋል። የአተም ቅጥልጣዮችን በማቀናጀትም ከትንንሽ ሞተሮች እስከ ነቁጥ ጡንቻዎች በአጠቃላይ ማንኛውንም ተንቀሳቃሽ ነገር መሥራት ችለዋል። ይኽን ብቃታቸውንም ሚሊዮኖች በመላው ዓለም የቴሌቪዥን መስኮት በታደሙበት ስርጭት የልብ እና የደም ቧንቧዎች ባለሙያው እና የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ጎይራን ኬ ሐንሰን ይፋ አድርገዋል።

«የስዊድን ሮያል የሣይንስ አካዳሚያ የ2016ቱን የኖቤል ሽልማት ለዦን ፒየር ሶቫሽ፣ ለሰር ጄምስ ፍሬዘር ስቶዳርት እና  ቤርንሃርድ ኤል ፌሪንኃ በጋራ ለመስጠት ወስኗል። ለሽልማቱ የበቁትም የአተም ቅጥልጣይ ማሽነሪ ንድፍ እና ውኅደት ላይ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ነው።»

በ20ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ላይ የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአንድ በላይ የኾኑ የአተም ቅጥልጣዮችን በመጠቀም ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የአተም ውኅዳንን መፍጠሩ ላይ አተኮሩ። ማሽኖችን ምን ያኽል ደቃቃ አድርጎ ማበጀት ይቻላል? እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1965 ዓም በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ የኾኑት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፒ ፌይማን ተደጋጋሚ ጥያቄ ነበር። ሪቻርድ እጅግ ደቃቃ ማለትም ናኖ ሥነ-ቴክኒክ ላይ በመራቀቅ ከታወቁ ተመራማሪዎች ፈር ቀዳጁ እንደሆኑ ይጠቀሳል። ሪቻርድ ማሽኖችን እጅግ ነቁጥ አድርጎ መሥራት ይቻላል የሚል ጽኑዕ እምነት ነበራቸው። የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በምርምሩ ከገፉት ተመራማሪዎች መካከል ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ ከተሸለሙት ሦስት ተመራማሪዎች አንዱ የኾኑት ፕሮፌሰር ቤርንሃርድ ኤል ፌሪንኃብ ይገኙበታል። ለሽልማት መብቃታቸውን ሲሰሙ የተሰማቸውን እንዲህ ይገልጣሉ።

«ምን ማለት እንደነበረብኝ አላውቅም ነበር። ብቻ በቃ ለአፍታ ጸጥ አልኩ። ከዛ በኋላ ለኖቤል ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ደንግጬ ነበር አልኩ። በልዩ ስሜት ተውጬ ነበር። ምክንያቱም ለእኔ ድንገተኛ እና አስደናቂ ነበር። ሳይንቲስት ነኽና ለትልቁ ሽልማት ለመብቃት ትመኛለህ። ግን ያ መች እንደሚኾን አታውቀውም። ድንቅ ነው፤ በእውነቱ ማመን አልቻልኩም።»

ፕሮፌሰር ቤርንሃርድ ኤል ፌሪንኃ ኔዘርላንድ በሚገነው ግሮኒኘን ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማእከላቸው ኾነው ከዶይቸቬለ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ለዚህ ሽልማት የበቁት በእልህ አስጨራሽ ጠንካራ ምርምር መኾኑን ተናግረዋል።  «በርካታ ሀሳቦች ቢኖሩህም ብዙዎቹ አይሳኩም» ያሉት ፕሮፌሰር ከ30 ዓመታት ምርምር በኋላ ለታላቁ የዓለማችን የሎሬትነት ሽልማት እንደበቁ ገልጠዋል። የስኬታቸው ምንጭም የበርካታ ወጣት እና ብርቱ ተመራማሪዎች ሥራ፣ የዶክትሬት መመረቂያ ምርምር እና ጥናት እንደሆነ ገልጠዋል። 

«እንደዚህ አይነት የናኖ ሳይንስ ጥናት ስታከናውን በሙያው ከተራቀቁ የተለያዩ ቡድኖች ጋር መሥራት አለብህ። ሁሉንም ነገር ብቻህን መሥራት አትችልም። ግን አንድ በአጽንኦት መናገር ያለብኝ ነገር አለ። በምርምሩ ዓለም ከበርካታ ብቃት ያላቸው ወጣቶች እና ከሳይንሱ ማኅበረሰብ ድንቅ ተመራማሪዎች ጋር አብሮ መሥራት ለእኔ ታላቅ  ክብር ነው።»

በክብር ላይ ክብር ተደምሮ ተመራማሪው ለዓለማችን ታላቁ የኖቤል ሽልማት በቅተዋል። የኖቤል ሽልማት ስያሜውን ያገኘው በስዊድናዊው ሳይንቲስት አልፍሬድ ኖቤል ስም ነው። ስቶኮልም ስዊድን ተወልዶ፣ ሩስያ አድጎ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደተማረ የሚነገርለት አልፍሬድ ኖቤል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ጠቅላላ ሐብቱ ለሳይንሳዊ ምርምር እና ሽልማት እንዲውል በመናዘዝ ነበር። አልፍሬድ ኖቤል የተናዘዘው ሐብት 31 ሚሊዮን የስዊድን ፍራንክ ነው። 

ዘንድሮ በኬሚስትሪ ዘርፍ ከተሸላሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሣይንቲስት ፕሮፌሰር ቤርንሃርድ ኤል ፌሪንኃብ ለተጨማሪ ረቂቅ ምርምር ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያሉ መኾናቸውን ተናግረዋል።

«ምንጊዜም የወደፊቱን ነው የምንመለከተው። እጅግ ጉጉ የኾኑ አባላት የሚገኙበት  ግዙፍ የምርምር ቡድን አለኝ። በርካታ ምርምሮችን እያከናወንን ነው። በአተም ቅጥልጣዮች የሚሠሩ ደቃቃ ሞተሮች እና ማሽኖች ላይ ጥናት እያደረግን ነው። ከዛ ደግሞ ለየት ያለ ረቂቅ መድሃኒት ለመፈልሰምም እየጣርን ነው። ረቂቅ አዲስ እንክብሎችን ለመሥራት እየጣርን ነው። ለአብነት ያኽል ነቀርሳን ለማከም የሚውሉ መድሃኒቶቹ አለያም ጸረ በሽታ አማጭ መድሃኒቶች አንቲቢዮቲኮች ይገኙበታል።»

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1901 ዓም  አንስቶ እስካሁን ድረስ በኬሚስትሪው ዘርፍ ለኖቤል ሽልማት የበቁት 108 ተመራማሪዎች ናቸው። ከነዚህ መካከል በተለያየ ጊዜያት 63 ሳይንቲስቶች በተናጠል የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚ ኾነዋል። 23 ሳይንቲስቶች ደግሞ ለሁለት በመጣመር ተሸልመዋል። 22ቱ ሳይንቲስቶች በኖቤል የኬሚስትሪ ዘርፍ የዓለም ሎሬት ተብለው የተሸለሙት እያንዳንዳቸው በጋራ ለሦስት በመጣመር ነው። በኬሚስትሪው ዘርፍ የእድሜ ባለጸጋ ኾነው የተሸለሙት ጆን ቢ ኤን ይባላሉ። ተመራማሪው ጆን የዛሬ ዐሥራ አራት ዓመት ሲሸለሙ 85 ዓመታቸው ነበር። በኖቤል የኬሚስትሪ ዘርፍ ወጣት ተሸላሚ ሴት ተመራማሪ ናት።  የኖቤል ተሸላሚዋ ፍሬድሪሽ ጆይሎት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1935 ዓ.ም ስትሸለም 35 ዓመቷ ነበር።

የዘንድሮ የኖቤል ተሸላሚዎች ዐሥራ አንዱም ወንዶች ናቸው። በሽልማቱ አንዲትም ሴት ተመራማሪ አለመኖሯ በአንዳንድ ተንታኞች ትችት አስነስቷል።  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1901 የመጀመሪያው የኖቤል ሽልማት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 833 ወንድ ተመራማሪዎች ለሽልማት በቅተዋል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው የሽልማት አሰጣጥ ላይ  48 ሴት ተመራማሪዎች ብቻ ናቸው የተሸለሙት።

ከኬሚስትሪው ዘርፍ ባሻገር ዘንድሮ በአምስት ዘርፎች ስምንት ሊቃውንት ለሽልማት በቅተዋል። የኖቤል ሽልማት ስድስት የሽልማት ዘርፎች አሉት። ስነ-ጽሑፍ፣ ኢኮኖሚ፣ ሠላም፣ ሕክምና፣ ፊዚክስ እንዲሁም ኬሚስትሪ ናቸው ዘርፎቹ። 

 የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ በፊዚክስ ዘርፍ አሸናፊ ያደረገው ሦስት ጠቢባን ነው፤ ዴቪድ ጀይ ቱለስ፣ ኤፍ ዳንካን ኤም ሀልዴን እና ጄይ ማይክል ኮስተርሊትዝ። ሦስቱ ተመራማሪዎች የተሸለሙት የቁስ ኢ-ይዘታዊ  ቅርጽ የባሕሪ ሽግግር  (topological phase transitions) እና  የቁስ ኢ-ይዘታዊ ባሕሪ (topological phases of matter) ላይ የላቀ እመርታ በማሳየታቸው እንደሆነ ተገልጧል። 

በህክምናው ዘርፍ ጃፓናዊው ተመራማሪ ዮሺኖሪ ዑሱሚ  «አውቶፈጊ» በተሰኘው ምርምራቸው ለሽልማት በቅተዋል። ጃፓናዊው ሊቅ ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ደቂቅ፥ ረቂቅ ክፍል ማለትም ኅዋስ (Cell) ራሱን በራሱ እንዴት እንደሚበላ የቃኙበት ጥልቅ ጥናት ለሽልማት አብቅቷቸዋል። 

በሥነ-ጽሑፍ ዘርፍ ታዋቂው የፖፕ አቀንቃኝ ቦብ ዲለን በአሜሪካ የዘፈን ባሕል አዲስ ምጡቅ አቀራረብን በማስተዋወቅ አሸናፊ መሆኑ ተገልጧል። ኾኖም ቦብ ዲለን የስዊድን ሮያል የሣይንስ አካዳሚያ ላቀረበለት ጥሪ እስከ አሁን ድረስ መልስ አለመስጠቱ ታውቋል።  ቦብ ዲለን አሸናፊነቱ ይፋ ከተደረገ ከስድስት ቀናት በኋላ ዛሬም አሸናፊ በመሆኑ ምን አይነት ስሜት እንደተሰማው ማንም ሰው ሊያውቅ አልቻለም፤ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ዳኞቹም ጭምር ቢኾኑ ማለት ነው። 

የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ የኮሎምቢያዊው ፕሬዚዳንት ዡዋን ማኑዌል ሳንቶሽን የኖቤል የሠላም ዘርፍ ተሸላሚ አድርጓቸዋል። 32ኛው የኮሎምቢያ ፕሬዚዳንት ዡዋን ማኑዌል ሳንቶሽ በሀገራቸው ለ50 ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያበቃ ማድረግ በመቻላቸው ነው የተሸለሙት።  የኖቤል ሽልማት የኢኮኖሚ ዘርፍ አሸናፊዎች ሁለት ባለሙያዎች ናቸው። የብሪታንያው ኦሊቨር ሐርት እና ፊንላንዳዊው ቤንግት ሆልምሽትሮይም። ሁለቱም ለሽልማት ያበቃቸው ሥራ  ሕጋዊ የውል አያያዝ ነባቤ ቃል በማበጀት ያደረጉት የላቀ ምርምር ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic