የአብዴፓ ክፍፍል በአፋር | ኢትዮጵያ | DW | 16.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአብዴፓ ክፍፍል በአፋር

አፋር ካለፉት ሦስት ሣምንታት አንስቶ ውጥረት እንደነገሰባት አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። የውጥረቱ መንሥዔ በገዢው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በምኅፃሩ አብዴፓ የሥራ አመራር ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ እና ክፍፍል እንደሆነ አንድ የአፋር ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:46

የአብዴፓ ከፍተኛ አመራር ክፍፍል በአፋር

የኢሕአዴግ አጋር ድርጅት በሆነው በአብዴፓ መካከል ክፍፍሉ የተፈጠረው በአፋር መስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው ለበርካታ ዓመታት በቆዩት አቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ እና በአብዴፓ ሊቀመንበር አቶ ጠሃ መሐመድ ቡድኖች መካከል እንደሆነም አክለዋል።

የአብዴፓ ሊቀመንበር አቶ ጠሃ እና ቡድናቸው በአፋር መንግስት ይመስረት ሲሉ የእነ አቶ እስማኤል ዓሊ ሴሮ ቡድን ደግሞ ጉባኤ አለያም ግምገማ ተደርጎ ነው መንግስት የሚመሰረተው በሚል መጋጨታቸውን እኚሁ ነዋሪ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት በአፋር መንግሥት ማቋቋም እንዳልተቻለ እና የቀድሞው የአብዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አወል አርባ በጊዜያዊነት ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተመረጡ ነዋሪው ተናግረዋል።

ውጥረቱን ተከትሎ የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት የአፋር ልዩ ኃይልን ለተወሰነ ቀን ከቦ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎት እንደነበረም የአፋር ነዋሪው ተናግረዋል። በአብዴፓ መካከል በተፈጠረው መከፋፈል አለመግባባት በመፈጠሩ የአፋር መስተዳደር አፈ-ጉባኤን ጨምሮ አንዳንድ የአብዴፓ አባላት ስብሰባ ረግጠው መውጣታቸውን ነዋሪው አክለው ጠቅሰዋል። የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሐለቶ መሐመድ በፓርቲው የለውጥ ሒደት ጥያቄ እንጂ ክፍፍል የለም ብለዋል።

የአፋር የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ሥዩም አዲስ አበባ ለስብሰባ ተጠርተው በሄዱበት ወቅት መኖሪያ ቤታቸው እንደተበረበረ፣ የተወሰነ ገንዘብ እና ሽጉጥጣቸው እንደተወሰደባቸውም መረጃ ደርሶናል ሲሉ ነዋሪው ለዶይቼቬለ ተናግረዋል። ቀደም ሲል መኖሪያ ቤታቸው በልዩ ኃይል ተከቦ ይጠበቅ ነበረም ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ እስማኤል ዓሊ ሴሮ ከሥልጣናቸው ወርደው የአፋር መስተዳደር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸውን አንድ ማንነታቸው እንዲገለጥ ያልፈለጉ የአብዴፓ ካድሬ ተናግረዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአፋር ነዋሪ ይኽንኑ ነው የደገሙት።

ማንነታቸው እንዲገለጥ ያልፈለጉት የአብዴፓ ካድሬ በበኩላቸው በቀድሞው የአፋር ፕሬዚዳንት እና ሊቀመንበሩ መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ፓርቲውን በኹለት ቡድን እንዳለያየው ገልጠዋል። ይሁንና የአብዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ሐለቶ መሐመድ የሥልጣን ሽኩቻ ሳይሆን «ትንሽ መሳሳብ» ነው ያለው ብለዋል።የአብዴፓው ካድሬ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ባለመስማማታቸውም በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ ወደ አዲስ አበባ ለአንድ ቀን ተጉዘው መመለሳቸውን ተናግረዋል። የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ተገማግመው ችግሩን እንዲፈቱ ሦስት የኢህአዴግ አባላት አብረዋቸው ወደ አፋር እዳቀኑ ጉዳዮን በቅርብ እከታተላለሁ ያሉ የአፋር ነዋሪው ተናግረዋል። የአብዴፓ አባላት ከሰኞ አንስቶ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን፤ ስብሰባው ዛሬ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ቀጥሎ እስከ ዐርብ ድረስ የሚዘልቅ መኾኑንም ነዋሪው እና የአብዴፓ አባሉ ተናግረዋል። ወጣቱ አዲስ ፊት፣ የተማረ ኃይል ማየት ይፈልጋል፣ ሕዝቡ ለውጥ ይሻልም ብለዋል።

ላለፉት ሃያ ኹለት አመታት በአፋር ሥልጣን ላይ የቆየው አንድ ፓርቲ ማለትም የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በምኅፃሩ አብዴፓ ብቻ ነው። አብዴፓ በአፋር የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ፓርቲዎችን ሆን ብሎ እንዳዳከማቸው የፓርቲው ካድሬ ገልጠዋል። በአፋር አብዴፓ አመራር መካከል የተከሰተው የሥልጣን ሽኩቻ የጎሣ መልክ የያዘ መሆኑ እንዳሰጋቸውም የአካባቢው ነዋሪ እና የፓርቲው ካድሬ ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic