1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአብዲ መሐመድ ዑመር መንገድ እና የሶማሌ ፖለቲካ 

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8 2010

በሶማሌ ክልል "ተግባራዊ የተደረጉ የተወሰኑ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም ክልሉ ለአስር አመታት ይመደብለት ከነበረው በጀት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ላለፉት አስር አመታት የክልሉ በጀት ተደማጭነትን ለመግዛት፤ ሰዎችን ለማፈን ሲውል ቆይቷል"

https://p.dw.com/p/336as
Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

የአብዲ መሐመድ ዑመር መንገድ እና የሶማሌ ፖለቲካ

የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ አሕመድ ሽዴን ሊቀ-መንበር  አድርጎ መሾሙ ተሰምቷል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የክልሉ ሰዎች እንደሚሉት በፓርቲው ውስጥ የሚገኙ የቀድሞው ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ደጋፊዎች የአመራር ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ አልነበሩም። ከሶስት ቀናት ግምገማ እና ከፌደራል መንግሥት ጫና በኋላ ሶሕዴፓን ለመምራት የተመረጡት አቶ አሕመድ አሁን የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው። አቶ አህመድ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ምኒስትር እንዲሁም የፋይናንስ እና ኤኮኖሚ ትብብር ምኒስትር ድዔታ ሆነው አገልግለዋል። የኢሳ እና የኦጋዴን ጎሳ ፖለቲከኞች ላቅ ያለውን ሚና በሚጫወቱበት እና ተንታኞች ስሱ እና አወዛጋቢ በሚሉት የሶማሌ ፖለቲካ ከገሬ ጎሳ ወገን የሚወለዱት አቶ አሕመድ ሽዴ ያላቸው ተደማጭነት አጠያያቂ ነው። የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ግለሰብ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራል የሚል ጭምጭምታ መሰማቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 
ሶሕዴፓ እና የሚመሩትን ክልል እንዳሻቸው ሲዘውሩት አስር አመታት ሞላቸው የሚባልላቸው የቀድሞው ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር ዛሬም የት እንዳሉ አይታወቅም። ክልሉን ለማስተዳደር በተከተሉት ሥልት እና ተፈፅመዋል በሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አብዝቶ የሚተቻቸው መሐመድ ኦላድ አቶ አብዲ ከሥልጣን ገለል በማለታቸው እፎይታ ተሰምቶታል። ጅጅጋ ትሪቢዩን የተባለው ድረ-ገጽ ባለቤት የሆነው መሐመድ  "በአንድ በኩል ተመልሰው የክልሉ ፕሬዝዳንት መሆን ስለማይችሉ አልቆላቸዋል። ነገር ግን እርሳቸው ያዋቀሩት ሥርዓተ-አስተዳደር አሁንም እንዳለ ነው። ለምሳሌ በጊዜያዊነት ክልሉን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙት አሕመድ አብዲ መሐመድ ኢልክአሴ እርሳቸው የመረጧቸው ተተኪያቸው ናቸው። አቶ አብዲ አሁን በእስር ላይ ናቸው፤ የሆነ ጊዜ ከፍትኅ ፊት ይቀርባሉ ቢባልም ሥርዓታቸው ግን እንዳለ ነው።  ለአስር አመታት የገነቡት ጨቋኝ እና ጨካኝ ሥርዓት እስካለ ድረስ አሁንም ሥልጣን ላይ ናቸው ማለት ይቻላል" ሲል ተናግሯል። 

Deutschland Äthiopien Abkommen
ምስል DW/G. Tedla

መሐመድ ኦላድም ይሁን የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የተከታተሉ እንደሚሉት የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት መዋቅር እና የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አደረጃጀት በአቶ አብዲ መሐመድ ዑመር የጥቅም ተካፋዮች የተሞሉ ናቸው። ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ የዛሬው ሶሕዴፓ በቦታው አልነበረም። በቅርቡ ከሽብርተኝነት ዝርዝር ስሙ የተፋቀው የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር በክልሉ ፖለቲካ ከፍ ያለ ሚና ነበረው። በ1984ቱ ምርጫ አሸንፎ የኦብነግ ተባባሪ መሥራች አብዲላሒ መሐመድ ሳዲ በርዕሰ-መሥተዳድርነት መንግሥት ቢመሰርቱም ከሁለት አመታት በላይ አልዘለቁም። በ1986 ዓ.ም. የመገንጠል ጥያቄ ያነሳው ኦብነግ ከፌደራል መንግሥቱ ተገፍቶ ወጣ። ኦብነግ ጫካ ወርዶ ነፍጥ ሲያነሳ የኢሕአዴግ ድጋፍ የተመቻቸው ሌሎች ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግን (ኢሶዴሊ) መሥርተው ሥልጣን ተቆናጠጡ። ከአራት አመታት በኋላ ስሙን ወደ የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሲቀይር የኦብነግ የደፈጣ ውጊያ አይሎ ይፈታተነው ነበር። በ1997 ዓ.ም. ደገሐቡር አካባቢ በሚገኘው የአቦሌ የነዳጅ ፍለጋ ላይ የኦብነግ ታጣቂዎች የፈጸሙት ጥቃት ግን የክልሉን ፖለቲካ እንዳይመለስ አድርጎ ቀየረው። በዚያ ጥቃት 65 ኢትዮጵያውያን እና ዘጠኝ ቻይናውያን ተገደሉ። የክልሉን ፖለቲካ በጥልቀት የመረመሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሔግማን እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የሰርጎ-ገብ ጥቃቱን በመደበኛው ሰራዊት ሊቋቋም እንደማይችል የተረዳው ያኔ ነበር። 

"የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጠንካራ እየሆነ በሔደ ጊዜ በተለይ በጎርጎሮሳዊው 2007 ዓ.ም. በአቦሌ የነዳጅ ፍለጋ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ነገሮች እጅግ ተባባሱ። መንግሥት የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ብቻ መዋጋት እንደማይችል ተገነዘበ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ቦታው ሔዶ የሆነ ነገር ያወድማል እንጂ የሰርጎ-ገብ ጥቃትን መመከት አልቻለም። በዚያን ወቅት አብዲ መሐመድ ዑመር በደገሐቡር የጸጥታ ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ። ምኅረት የለሽ የነበሩት ሰው ልዩ ፖሊስን አቋቋሙ። በሒደት የኢትዮጵያ መንግሥት የሰርጎ-ገብ ጥቃቱን የመዋጋቱን ሥራ ለልዩ ፖሊስ አሳልፎ ሰጠ። ልዩ ኃይሉ እጅግ ጨካኝ ሆኖ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቢፈፅምም አባላቱ የኦጋዴን ሰዎች በመሆናቸው እና እያንዳንዱን ሰው ያውቁ ስለ ነበር ስኬታማ ሆነ። የሰርጎ-ገብ ጥቃቱን ለመመከት ከሌላ የኢትዮጵያ አካባቢ ሰው መምጣቱ ቀረና ራሳቸው ተሰማሩበት። በዚህም ምክንያት የርስ በርስ ጦርነት መልክ ያዘ። አብዲ መሐመድ ዑመር ኦብነግን በተወሰነ መጠን ለማጥፋት ተቻላቸው። ነገር ግን እጅግ አስቀያሚ ነበር"

Äthiopien Stadt Jijiga
ምስል DW/T. Waldyes

የሶማሌ ልዩ ፖሊስ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት

በዴንማርክ ሮስኪልድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ልማት እና ፖለቲካ ተመራማሪው ሔግማን የጠቀሱት ልዩ ኃይል የመጀመሪያ 800 አባላት ጅጅጋ በሚገኝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የተመረቁት በታኅሳስ ወር 2000 ዓ.ም. ነበር። በወቅቱ አቶ ዳውድ መሐመድ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር ደግሞ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ። ሒውማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ ተቋማት እና በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች "የልዩ ፖሊስ ሕጋዊ አካልነት ግልጽ አይደለም" ይበሉ እንጂ የገንዘብ ምንጩ የክልሉ መንግሥት በጀት እንደነበር ይነገራል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ከስድስት አመታት በፊት ባወጣው ዘገባ "በክልሉ መሥተዳድር አማካይነት የኃይሉ አባላት ከማዕከላዊ መንግስት የስልጠና፣ የጦር መሣሪያ፣ የመለያ አልባሳት አቅርቦት እና ደመወዝ " እንደሚሰጣቸው ገልጾ ነበር። በሐምሌ 2002 ዓ.ም. የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድርነትን ሥልጣን የጨበጡት እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ እዝ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው አብዲ በጉልበትም ቢሆን የክልሉን ጸጥታ ማረጋጋት መቻላቸውን ሔግማን ይናገራሉ። 

"ለተወሰኑ አመታት በተለይም በጎርጎሮሳዊው ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት የተከተሉት ስልት ጭካኔ የተሞላበት ቢሆንም የሰርጎ-ገብ ጥቃቱን ለመመከት ሥኬታማ አድርጓቸዋል። ለረዥም ጊዜ የጸጥታ መዋቅሩ በተለይም የመከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ እዝ የሚሰጣቸውን ሥራ ያስፈፅሙ ነበር። ከፍ ከፍ ያደረጓቸው እነዚሁ የመከላከያ ሰራዊት ሰዎች ነበሩ። በሂደት ግን ልዩ ፖሊስ እና አብዲ ኢሌ ከፌድራል መንግሥቱ ራሳቸውን አላቀቁ። ሰውየው እጅግ ጠንካራ ሆነው እውነተኛ ራስን የማስተዳደር ነፃነት  ኖራቸው"
የአብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደር በሥልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት በክልሉ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ባወጧቸው ተደጋጋሚ ዘገባዎች ጠቁመዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሰኔ ባወጣው ዘገባ በጅጅጋ ከተማ በሚገኘው ኦጋዴን እስር ቤት "ዘግናኝ እና ያልተቋረጠ ሰቆቃ፣ ድብደባ፣ ማዋረድ" እንደሚፈፀም አትቷል። ሒውማን ራይትስ ዎች ያነጋገራቸው እና በኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አባልነት ተጠርጥረው ታስረው የተፈቱ በእስር ቤቱ ስቅየት እንደሚፈጸምባቸው፤ በጭለማ ቤት እንደሚታሰሩ እና ተገደው የተደፈሩ መኖራቸውን ጭምር ተናግረዋል። በኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር አባልነት ተጠርጥረው ለእስር የሚዳረጉ ዜጎች ከሚፈፀምባቸው ቁም ስቅል ባሻገር በቂ ምግብ፣ ሕክምናና እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የጉብኝት ጊዜ እንደማይፈቀድላቸው የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ ገልጿል። የክልሉን ጸጥታ ለማስጠበቅ የአብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳደር የተከተለው እና የኢትዮጵያ መንግሥት ይሁንታ አግኝቷል የሚባለው ይኸው ስልት የሕግ የበላይነትን የሻረ እንደነበር ሔግማንም ይስማማሉ። መሐመድ ኦላድ እንደሚለው ለአስር አመታት በሶማሌ ክልል የታዩ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ግን የከፋ ነበር። 

"ተግባራዊ የተደረጉ የተወሰኑ የልማት ሥራዎች ቢኖሩም ክልሉ ለአስር አመታት ይመደብለት ከነበረው በጀት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ላለፉት አስር አመታት የክልሉ በጀት ተደማጭነትን ለመግዛት፤ ሰዎችን ለማፈን ሲውል ቆይቷል። በሌላ በኩል ሰዎችን ለማሰቃየት ኃይል ይጠቀሙ ነበር። ወንድምህ አንዳች ነገር ፌስቡክ ላይ ስለፃፈ አንተ ትገደላለህ። በውጭ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ስለ አብዲ ኢሌ ወይም ስለሚመሩት አስተዳደር አንዳች ነገር ከፃፈ የቤተሰቦቻቸው ንብረት ይወረሳል፤ ከመኖሪያ ቤታቸው ይፈናቀላሉ፤ ሲከፋ ወንድሞቻቸው አብዲ ኢሌ የማይወዱት ነገር በመናገራቸው ብቻ ሊገደሉ ሁሉ ይችላሉ። ይኸ በየትኛውም የዓለም ክፍል የማይታይ እብደት ነው"

አብዲ መሐመድ ዑመር የተከተሉት መንገድ

ቶቢያስ ሔግማን አብዲ መሐመድ ዑመርን ከቺቺኒያው መሪ ራምዛን ካዲሮቭ ጋር ያነፃጽሯቸዋል። የ41 አመቱ ካዲሮቭ የመገንጠል ጥያቄ የሚነሳባትን ቺቺኒያ በጉልበት ጸጥ ለጥ አርገው እየመሩ ናቸው። የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ የቺቺን ሰዎችን ድምጥማጣቸውን ሲያጠፉ ግን ሥራቸው በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይሁንታ የተቸረው እንደነበር ተንታኞች ይናገራሉ። ሔግማን እንደሚሉት አብዲ በትምህርት ባይገፉም የጎሳ ፖለቲካ እና ኃይልን አጣምረው ክልሉን መምራት ችለዋል። 

"አብዲ ኢሌ እጅግ ልዩ ሰው ናቸው። ባይማሩም የጎሳ አወቃቀሩን ለራሳቸው እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ የማስታወስ ችሎታቸው እንደ ኮምፒውተር ያለ ነው። ማን የማን ዘመድ እንደሆነ ያውቃሉ። ከደገፍከኝ ሥራ እሰጥሀለሁ፤ ከተቃወምከኝ አጠቃሃለሁ እያሉ ነው ስራውን ያከናወኑት"  

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በሶማሌ ክልል ይህ ሁሉ ሲፈፀም የፌድራል መንግሥት ለምን ቸልተኝነትን መረጠ? እንደ መሐመድ ኦላድ ያሉ ተቺዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈፅመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያወቀ ለጸጥታ ሥራው ቅድሚያ ሰጥቶ ቸል ብሏቸዋል እያሉ ይወቅሳሉ። መሐመድ "ለአስር አመታት እየገደሉ ፤ እያፈናቀሉ እና ተቃዋሚዎችን እያፍኑ ቆይተዋል። በሕወሓት የሚመራው የቀደመው መንግሥት የክልሉን ጸጥታ እስካስጠበቁ ድረስ የጭካኔ ድርጊታቸው አላሳሰበውም። ማንንም ቢገሉ እና ቢያፈናቅሉ ጸጥታው እስከተጠበቀ ድረስ አያሳስበንም ባዮች ነበሩ" ሲል ይተቻል። 

ቶቢያስ ሔግማን እንደሚሉት ግን የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እና በፌድራል መንግሥቱ ውስጥ የሚገኙ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም አብዲ መሐመድ ከሥልጣን እንዲወርዱ ፍላጎት ነበራቸው። ፍላጎታቸው ግን ሰውየው ከአገሪቱ ወታደራዊ ሹማምንት ጋር በነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት አልተሳካም። 

"በፌድራል መንግሥቱ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ሰዎች አልወደዷቸውም። ኃይለ ማርያም እና ሌሎች ሰዎች ከሥልጣን ገሸሽ ሊያደርጓቸው ቢሞክሩም በመከላከያው ከለላ ስለሚደረግላቸው አልቻሉም። ሰውየው ላይ ጫና ማሳደር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ፌድራል መንግሥቱ ለዘለዓለም ሊታገሳቸው አይችልም።  እንዴት ከሥልጣን ይወርዱ ይሆን የሚለው ጉዳይ ለብዙዎች አሳሳቢ ጉዳይ ነበር። አሁን በተመለከትንው መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሆኗል። እጅግ ዋናው ጉዳይ የተለየ የማሻሻያ ሐሳብ ይዘው ብቅ ያሉት እና እንደ አብዲ ኢሌ ያሉ ሰዎችን ማስወገድ የሚፈልጉት የጠቅላይ ምኒስትር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት ነው። የሒውማን ራይትስዎች ዘገባ፤ በሶማሌ-ኦሮሞ ግጭት በርካታ ሰዎችን ማስቀየማቸው እና ከኦጋዴን ጎሳ ውጪ ያሉ የሶማሌ ፖለቲከኞችን መግፋታቸው ተጨማሪ ጉዳዮች ናቸው"

ቶቢያስ እንደሚሉት በየትኛውም ስሌት ቢሆን የአብዲ መሐመድ ዑመር አወዳደቅ የከፋ እንደሚሆን የሚገመት ነበር። አብዲ መሐመድ ዑመር ከሥልጣናቸው ከመውረዳቸው ባለፈ ክልሉን በመሩባቸው አመታት ለተፈጸሙ ጥፋቶች ተጠያቂ የመሆናቸው ጉዳይ እስካሁን አለየለትም። እርሳቸው የሚያዙት ልዩ ኃይል እጁን አስገብቶበታል እየተባለ በሚወቀስበት የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል። ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማም ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። ጅጅጋ፤ ቀብሪ ደሐር እና ደገሐቡርን በመሳሰሉ ከተሞች ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው ኹከት ለተጨማሪ ሰዎች ሞት፤ መፈናቀል እና መዘረፍ ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ 

ሒሩት መለሰ