የአብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ስንብት እና የአልጄሪያ ፈተና | አፍሪቃ | DW | 06.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ስንብት እና የአልጄሪያ ፈተና

አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ሲያስረክቡ እጃቸው ይንቀጠቀጣል፤ ለ20 አመታት አልጄሪያን ጸጥ ለጥ አድርገው የገዙት ሰው በተለይ ባለፉት አምስት አመታት ሕመም ተጭኗቸው ድምፃቸው ከሕዝባቸው ርቆ ቆይቷል። በተቃውሞ ተገደው ሥልጣን ሲለቁ አልጄሪያ ያቆመችው የባለአደራ መንግሥት በ90 ቀናት ምርጫ ማካሔድ ይጠበቅበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:40

አልጄሪያ በ90 ቀናት ምርጫ ማካሔድ አለባት

የ82 አመቱ አዛውንት አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለአልጄሪያ ሕገ-መንግሥታዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጣይብ ቤላይዝ ሲያስረክቡ እጆቻቸውን በአግባቡ ማንቀሳቀስ ተስኖቿዋል። የ82 አመቱ አዛውንት እንደ ወትሮው ሁሉ በተንቀሳቃሽ ወንበር ላይ ናቸው። እንዲህ ጤናቸው ከታወከ አምስት አመታት አስቆጥሯል። ድንገተኛ የደም መርጋት ከገጠማቸው በኋላ ከአደባባይ ርቀው ቆይተዋል። አምስቱን አመታት ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው አልጄሪያን የመሩት ሰው ግን ጤናቸው ቢታወክም እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም።

በአግባቡ መራመድም ሆነ መናገር የተሳናቸው ቡቶፍሊካ 42 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ያሏትን አገር እንዴት ይመሩ እንደነበር ለአልጄሪያ ዜጎች ጭምር እንቆቅልሽ ነው። የዜጎቻቸው ተቃውሞ ከማየሉ የጦራቸው ማስጠንቀቂያ ከመሰማቱ በፊት በአልጄሪያ ምርጫ ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን የመወዳደር ዕቅድ ጭምር ነበራቸው። ባለፈው ሚያዝያ እጩነታቸውን ይፋ ሲያደርጉ ለአገራቸው ሕዝብ በአካል እንኳ አልታዩም።

የማይናገሩት ፕሬዝዳንት እና የአልጄሪያ ተቃውሞ

ሰውየው በአካል ካለመታየታቸው ይበልጥ ለመወዳደር መወሰናቸው ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ጠበቆች እና ነጋዴዎችን ወደ አደባባይ መራቸው። አልጄሪያውያን ከዕይታ በራቁት ሲከፋ ደግሞ 20 አመታት አገራቸውን ጸጥ ለጥ አድርገው በገዙት ሰው የመመራት ፍላጎት አልነበራቸውም። እናም ከወትሮው የተለየ አዲስ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ተቃውሞው በርትቶ ሥልጣን የሚለቁበትን ጊዜ ይፋ ሲያደርጉ ደግሞ በአገራቸው ጦር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ጫና በረታባቸው።

ፕሬዝዳንቱ "ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ብቁ አይደሉም" ከሚል ድምዳሜ የደረሱት ሉፍቴናንት ጄኔራል አሕመድ ጋዒድ ሳላህ "የሚባክን ጊዜ የለም" ብለው በገዛ መንግሥታቸው ከሥልጣን ሊያወርዷቸው ተነሱ። የሥልጣን እህል ውሐቸው መጠናቀቁን የተገነዘቡት ቡቶፍሊካ ባለፈው መጋቢት 24 ሥልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ አደረጉ። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት በደስታ ጨፈሩ። ፍላጎታቸው ግን በዚያ የሚያበቃ አልሆነም። የአልጄሪያን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ በአልጀርስ አደባባይ ሲጨፍር የታየው አብዱልከሪም መሐመድ “በአንድ ሰው ውድቀት ከተደሰትን ርቀን አንጓዝም። ትክክለኛው ትግላችን በሕግ የምትመራ፣ ጠንካራ ተቋማት ያሏት ዴሞክራሲያዊት አገር ለመመስረት ነው” ሲል የአገሪቱ ዜጎች ፍላጎት በዚህ እንደማያበቃ ይናገራል። ከደስታው ባሻገር ስጋትም አልጠፋም። ሌላው የአልጀርስ ነዋሪ “በጦሩ ላይ ያሳደርንው እምነት እንደከዚህ ቀደሙ እንዳይካድ ተስፋ አደርጋለሁ። እምነታችንን ሰጥተናቸዋል፤ እኛው ላይ መልሰው ይነሳሉ የሚል ዕምነት የለኝም። ቀጣዩን ፕሬዝዳንታችንን ራሳችን መምረጥ እንፈልጋለን” ብሏል።

የለት ተለት ኑሮውን ከሚገፋበት የአትክልት ችርቻሮ ተነስቶ አደባባይ የወጣው አልጄሪያዊ በበኩሉ “ዋናው እና በጉጉት የምንጠብቀው ቡቶፍሊካ፣ ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው ታስረዋል የሚለውን ዜና ነው” ሲል ተናግሯል።

የአልጄሪያ ተቃዋሚዎች ቡቶፍሊካ ከችሎት እንዲቆሙ ብቻ ሳይሆን "ነጋዴ ፖለቲከኞች" የሚሏቸው ሶስት ጉምቱ ባለሥልጣናት አብረዋቸው ሥልጣን እንዲለቁ ይሻሉ።ሶስቱ ሰዎች የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አብደልበከር ቤንሳላሕ፣ የሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እና የቡቶፍሊካን የሥልጣን መልቀቂያ የተቀበሉት ጣይብ ቤላይዝ እንዲሁም ጠቅላይ ምኒስትር ኑረዲን ቤደዊ ናቸው።

ተቃውሞዎቹ በዋናነት በቡቶፍሊካ ላይ ያነጣጥሩ እንጂ በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና፣ መንግሥታዊው ሥልጣን በጥቂት ልሒቃን ቁጥጥር ሥር መውደቁ እና አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገፋታቸው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተደራጀ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተስፋፋው ተቃውሞ ቡቶፍሊካ ሥልጣን ከተቆናጠጡ ጀምሮ ከገጠሟቸው ሁሉ የላቀ ነው።

በነዳጅ ዘይት የናጠጠችውን አገር ሲመራ የቆየው  የቡቶፍሊካ መንግሥት የአልጄሪያን ምጣኔ ሐብት በማነቃቃት ፖለቲካዊ ሥልጣኑን ማስበጠበቅ ችሎ ቆይቷል። አልጄሪያ የከተማ የባቡር አገልግሎቶች እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለዜጎቿ የመኖሪያ ቤቶች ማቅረብ ችላለች። ከ30 በመቶ በላይ ዜጎቿ ዕድሜያቸው ከ30 አመት በታች የሆኑባት አልጄሪያ በቂ የሥራ ዕድል ግን መፍጠር አልቻለችም። የጸጥታ አስከባሪዎች ፅጌረዳ አበባ ላበረከቱላቸው የአደባባይ ተቃውሞዎች የሰጡት ምላሽ በሌሎች የሰሜን አፍሪካ እና የአረብ አገራት ከታየው የተለየ ነበር። የመንግሥቱ ባለሥልጣናት ተቃውሞው ሰላማዊ በመሆኑ ቢስማሙም በሒደት ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳያመራ ግን ሥጋት ነበራቸው።

አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ከሥልጣናቸው ገሸሽ ማለታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የአልጄሪያ ተቃዋሚዎች አደባባይ እና ጎዳናዎቻቸውን ማፅዳት ጀምረዋል። ድርጊቱ በተቃውሞ ባልተሳተፉ ጭምር ዘንድ ተስፋ የፈነጠቀ እና ትልቅ አዎንታዊ ትርጉም ያለው ሆኖ ይታያል።

አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ማን ናቸው?

 

አራተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ከመጠናቀቁ በፊት ያገመገመውን "ቀውስ ለማስቀረት" ሥልጣን መልቀቃቸውን ያሳወቁት አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ በአልጄሪያ የጸረ ቅኝ ግዛት የትግል ዘመን የነበሩ ፖለቲከኛ ናቸው። በጎርጎሮሳዊው 1937 ዓ.ም. ከአልጄሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የሞሮኮ ግዛት ውስጥ የተወለዱት ቡቶፍሊካ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የተባለውን ነፃ አውጪ ጦር የተቀላቀሉት በ19 አመታቸው ነው። አልጄሪያ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ስትወጣ በወጣቶች እና ስፖርት ምኒስትርነት መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ጀምረው በ26 አመታቸው የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሆኑ።

በጎርጎሮሳዊው 1981 ዓ.ም. ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አምርተው ለገዢው ሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናሕያን አማካሪ ሆነው ሰርተዋል። ምርጫ አሸንፈው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የጨበጡት በጎርጎሮሳዊው 1999 ዓ.ም. ነበር።

በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ከርስ በርስ ጦርነት ያላገገመችውን አገር መልሶ መገንባት ቀዳሚ ዓላማቸው ሆነ። የያኔውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተዘዋዋሪ መሪነትን ሲጨብጡ የኢትዮጵያን የቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለማስታረቅ በሚደረገው ጥረት እጃቸውን አስገብተው አልጄሪያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ስም ለማደስ ጥረዋል። መለስ እና ኢሳያስ የአልጀርሱን ስምምነት በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. ሲፈርሙ አጭሩ ቡቶፍሊካ የሁለቱን ባላንጦች ትከሻ አቅፈው የታዩት ያኔ ነበር።

አልጄሪያን ማን ይመራል?

ቡቶፍሊካ ከሥልጣን ሲወርዱ ለዘጠና ቀናት አልጄሪያን የሚመራ ባለአደራ መንግሥት ኃላፊነቱን ተረክቧል። የባለ አደራ መንግሥቱን የሚመሩት በአልጄሪያውያን የሰላ ትችት የሚሰነዘርባቸው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አብደልካድር ቤንሳላህ ናቸው። የ77 አመቱ አዛውንት የሚመሩት ይኸው ጊዜያዊ መንግሥት በ90 ቀናት ውስጥ ምርጫ ማካሔድ ይጠበቅበታል።

የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኙ ናስር ወዳዲ "አሁን ባለው ሕገ-መንግሥት መሰረት ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ መንግሥቱን የሚመሩት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ናቸው። ትልቁ ፈተና የሚጀምረው ከዚህ ነው። ምክንያቱም ባለፉት አስር አመታት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዳክመዋል። ፓርቲዎቹ ደካማ እና ዋጋ ቢስ እንዲሆኑ ባለሥልጣናቱ የተለያዩ አስቀያሚ ስልቶች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ትልቁ ፈተና የአልጄሪያ የሲቪክ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ታሪካዊ ወቅት የአገሪቱን ዜጎች በአንድ ዓላማ የሚያሰባስብ እና በምርጫ ድምፅ የሚሰጡበት ርዕይ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ወይ? የሚለው ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

በአንድ ወቅት ጋዜጠኛ እና አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት አብደልካድር ቤንሳላህ እምብዛም የአደባባይ ሰው አይደሉም። ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ቢቆዩም እንኳ ቃለ መጠይቅ የሰጡት ጥቂት ጊዜያት ነው። ቡቶፍሊካ በሥልጣን በቆዩባቸው 20 አመታት አብዛኛውን የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ሆነው የሰሩት አዛውንት አልጄሪያውያን እምነት የሚጥሉባቸው ሰው አልሆኑም። እርሳቸውን ጨምሮ አሁን በጊዜያዊነት ሥልጣን የጨበጠው መንግሥት ግልፅ እና ተዓማኒ ምርጫ በ90 ቀናት የማካሔዱ ጉዳይ የአልጄሪያን እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል።

ናስር ወዳዲ "ይኸ በየትኛም መንገድ ቀላል ሒደት አይሆንም። ምክንያቱም ፓርቲዎች በተከታታይ ክሶች እና እንግልቶች ተዋክበው የፖለቲካ ሥርዓቱ ተዳክሟል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአልጄሪያ ዜጎችን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ለመሆናቸው ሕዝቡ መልሶ ዕምነት እንዲኖረው በርካታ ሥራዎች መሰራት አለባቸው" ሲሉ ይናገራሉ።

ምርጫውን ማን ይመራዋል?

የአልጄሪያን የ20 አመታት ፖለቲካ የታዘቡ ተንታኞች እንደሚሉት የአገሪቱ ሥርዓተ-መንግሥት በጥቂት ልሒቃን ውስጥ ከወደቀ ቆይቷል። ተቋማት ተዳክመዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በበረታ ጫና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ለመቻላቸው ጥርጣሬ ነግሷል። ታዲያ የምርጫውን ነፃነት ማን ይቆጣጠራል? ናስር ወዳዲ  

"የአንድ ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ነው። በአሰራሩ መሰረት በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ እና በአልጄሪያ ዜጎች ቁጥጥር የሚደረግበት ይሆናል። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ-መንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ማድረግ ያለባቸው ዜጎች ናቸው። አልጄሪያውያን ከግልፅ ምርጫ እና ጠንከር ካለ ምክር ቤት ውጪ ይቀበላሉ ብዬ አላምንም። ይኸ ይሳካል አይሳካም የሚለውን ጊዜ ይፈርዳል" ሲሉ የአልጄሪያ ፖለቲከኞች እና ዜጎች የሚጠብቃቸውን ፈታኝ የቤት ሥራ ያስረዳሉ።

አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ለ20 አመታት በጤና እና በሕመም ከነገሱበት ፖለቲካ ገለል ሲሉ ለአገራቸው ባበረከቱት አስተዋፅዖ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው እንዳሉትም የአገራቸው መፃኢ እጣ-ፈንታም መልካም እንደሚሆን እርግጠኛ ናቸው። የአልጄሪያ የሥልጣን ሽግግር ሰላማዊ የመሆኑ ጉዳይ በመጪዎቹ ጊዜያት የሚታይ ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ

 

 

Audios and videos on the topic