የአብዬ ፀጥታ እና የፀጥታው ምክር ቤት | አፍሪቃ | DW | 17.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአብዬ ፀጥታ እና የፀጥታው ምክር ቤት

ማክሰኞ ዕለት የተሰበሰበው የተመድ የፀጥታ ም/ቤት በሱዳን እና በ/ሱዳን ድንበር አካባቢ ባለው የአብዬ ግዛት ስለተሰማራው ጊዜያው የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ በሰፈው ተነጋግሯል።በዚህም እዚያ የሚገኘውን ጊዜያዊ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ በስድስት ወራት አራዝሟል። አብዬ ካለው ሰላም አስከባሪ ኃይል አብዛኛውን ጦር ያሰማራችው ኢትዮጵያ ናት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:05

የሰላም አስከባሪዉ ኃይል ቆይታ ተራዘመ

በጎርጎሪዮሳዊዉ ከ1955 እስከ 1972 የተካሄደው የሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ሲያከትም አዲስ አበባ ላይ በተደረሰው ስምምነት የአብዬ ግዛት ነዋሪዎች አዲስ ከምትመሰረተው ደቡብ ሱዳን ወይም ደግሞ በሰሜን በኩል ከምትገኘው ሱዳን ጋር ለመሆን እንዲመርጡ ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል ተብሎ ነበር። ሆኖም ከአስር ዓመታት ገደማ በኋላ ዳግም የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት አገረሸ። በዚያም ላይ የወቅቱ የሱዳን ፕሬዝደንት ጃፋር ኒሜሪ የህዝበ ውሳኔውን መካሄድ አልፈቀዱም። ዳግም የእርስበርስ ጦርነቱን ለማክተም ኻርቱም እና ጁባ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2005 አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱም አብዬ ግዛት ሕዝበ ውሳኔ እስኪካሄድ በልዩ አስተዳደርነት እንድትቆይ የሚል አንቀፅ አካቶ  ለጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ቀጠሮ ቢያዝለትም ተግባራዊ አልሆነም።
በግዛቲቱ የሚገኘውን የሰላም አስከባሪ የተልዕኮ ጊዜ ያራዘመው የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እዚያ የሚገኘው ኃይል የዛሬ 13 ዓመት ሁለቱ ወገኖች የተስማሙበት አጠቃላይ የሰላም ውል ተግባራዊነት እውን እንዲሆን የበኩሉን ተሳትፎ እንዲያደርግ ይጠይቃል። እስካሁን በአብዬ ግዛት ፀጥታ አለመስፈኑም ዓለም አቀፍ ስጋት ሊሆን እንደሚችልም ያሳስባል። የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በአንድ ስፍራ ማስፈሩ በራሱ ግብ አይደለም የሚሉት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይንቴ፤ ለአብዬ ጉዳይ መፍትሄ እንዳይገኝ የደቡብ ሱዳን የውስጥ ፖለቲካዊ ችግር  እንቅፋት እንደሆነ ያስረዳሉ።

Region Abyei im Sudan

«የሰላም አስከባሪ በአንድ ቦታ ሲሰፍር በራሱ ግብ አይደለም። ለምሳሌ በሁለት ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ግጭት ካለ ያንን ግጭት አቁመው ወደድርድር እና ወደስምምነት እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው። እንግዲህ እስካሁን ባለው ሂደት በአብዬ አካባቢ በተፈጠረው ችግር ሁለቱ መንግሥታት መካከል ውይይት እና ድርድር በተወሰነ መልኩ ተጀምሮ ነበር በኋላ በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ችግሩ የሁለቱ አገሮች መሆኑ ቀርቶ የደቡብ ሱዳን የውስጥ ጉዳይ ሆነና ረጅም ጊዜ የወሰደው ዘላቂ መፍትሄ እንዳያገኙ ያደረጋቸው ይመስለኛል።»

ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የሚወዛገቡባት አብዬ 4 ሺህ ስኩየር ማይል በረሃማ ስፍራ፣ ለእርሻ የሚሆን መሬት እና የነዳጅ ክምችት ያላት በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን የድንበር አካባቢ የምትገኝ ግዛት ናት። ቦታው ሁለቱም ሱዳኖች የእኔ የሚሉት በመሆኑ ከ50 ዓመታት በላይ ሲያጋጫቸው ቆይቷል። ከምንም በላይ ሁለቱ ወገኖች በአብዬ ላይ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ የጋበዛቸው የነዳጅ ዘይት ሀብቱ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። ከቀድሞው ጀምሮ በስፍራው የሚኖረው ሕዝብ ናጎክ ዲንቃ  ጎሳ ሲሆን፣ ባህሉ እና ቋንቋው ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሚገኙት ዲንቃዎች ጋር የተሳሰረ መሆኑ ይነገራል። በስተሰሜን ሱዳን የሚገኘው የአረብ ጎሳ አባላት የሆኑት የሚስራይ አርብቶ አደሮችም በደረቅ ወቅቶች ለዉኃ እና ግጦሽ ፍለጋ እንዲሁም በንግድ ምክንያት ወደአብዬ መሄዳቸው የተለመደ ነው። አቶ አበበ እንዲህ ባለው አወዛጋቢ ስፍራ ዓለም አቀፍ ኃይል መስፈሩ ችግሩን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ ቢያደርግም ሁለቱ ወገኖች ግን ለአዎንታዊ ውጤት ተግባብተው መሥራት አልቻሉም ይላሉ።

«እንግዲህ ችግሩን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ምክንያቱም የካርቱም መንግሥት እና የጁባ መንግሥት ወደጦርነት እንዳይሄዱ አስቁሟል። አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁን ያለው ችግር ሁለቱ አገሮች ይሄን የይገባኛል ጥያቄያቸው በእንዴት ያለ መንገድ ነው መፈታት ያለበት በሚለው ላይ ተነጋግረው ተስማምተው ወደመፍትሄ መሄድ አልቻሉም። ይህ እንዳይሆን ያደረገው ደግሞ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረው የውስጥ ችግር ነው። ስለዚህ በአብዬ የሰፈረው የሰላም አስከባሪ ጦር ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ግን ይህን ምቹ ሁኔታ ወደዘላቂ ሰላም ሊወስዱ በሚችል መልኩበዚያ ቁመና ላይ አይደሉም።»

እንዲህ ባለው ሁኔታ ለቀጣይ ስድስት ወራት የተራዘመው የሰላም አስከባሪዉ ተልዕኮ ውጤት ማምጣት እንዲያስችል በተለይ ለደቡብ ሱዳን የውስጥ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ አማራጭ የሌለው ስልት መሆኑን በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይንቴ ሰጥተዋል።  የፀጥታው ምክር ቤትም ተልዕኮውን ከማራዘም የተለየ አማራጭ አልነበረውምም ባይ ናቸው።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic