የአብሮነትና የተናጥል ፍትጊያ | ዓለም | DW | 18.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአብሮነትና የተናጥል ፍትጊያ

የከፋዉ የዩናይትድ ስቴትስ ነዉ።«የናንተን አምጡ-የኔን አትኩ» ዓይነት መርሕ የሚያራምዱት የአሜሪካ መሪዎች ያቺን ትልቅ፣ሐብታም፣የዴሞክራሲያ አብነት ሐገርን ለብቻዋ እያከነፏት ነዉ።ወዳጅ ከጠላት ሳይለዩ የሚናደፉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና ሹመኞቻቸዉ የጀርመን መኪኖች ለአሜሪካ ደሕንነት አስጊ ናቸዉ እስከማለት ደርሰዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:32

የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ፣ የምዕራብ ጥብቅ ወዳጅ መንግስታት ልዩነት

ከዋሽግተን-ለንደን መሪዎችና ከጥቂት አሸርጋጆቻቸዉ በስተቀር የድፍን ዓለም መሪ-ፖለቲከኛ፣ ዲፕሎማት፣ በየቢሮ-ጓዳዉ የሚያንሾካሽከዉን ዮሽካ ፊሸር በገሐድ አፈረጡት።አስጠነቀቁም።ማስጠንቀቂያዉ፣ ለዋሽግተን-ለንደን ፖለቲከኞች በጠቀመ ነበር።ራምስፌልድ ግን አላጋጡ። ሙኒክ።የካቲት 9 2003 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የቡሽ-ራምስፌልድ እብሪት፤ የብሌር-አዝናር ጭፍን መናጆነት ካደረሰዉ ጥፋት ከማንም በላይ የአሜሪካ-ብሪታንያ ተተኪዎቻቸዉ በተማሩ ነበር።አልተማሩም።እና በ16ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ሜርክል ፊሸርን፣ ፔንስ ራምስፌልድን ሆኑ።እንደገና ሙኒክ። ታሪክ ራሱን ደገመ እንበል ይሆን? ላፍታ እንጠይቅ።

የጀርመን መራሒተ መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ  ሜርክል ለዘንድሮዊዉ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ተካፋዮች ባለፈዉ ቅዳሜ እንደነገሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም አለቅጥ የሚገፉት የተናጥል መርሕ ለዓለም አይበጅም።

ሜሪክል እንደሚሉት ሐገራት ወይም መንግሥታት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ተነጥለዉ  ሊኖሩ አይቻላቸዉምና።ሜርክል

አንዱ ከሌላዉ ጋር ተነጣጥሎ መኖር እንደማይችል ለማስረገጥ ከጠቀሱት አብነት ቀዳሚዉ የ19ኛዉ መቶ ክፍለዘመን ጀርመናዊ ሳይንቲስት፣ ምሑርና አገር አሳሽ የአሌክሳንደር ሁምቦልትን አስተሳሰብ እና ብሒልን ነዉ።

«እምነቱ፣ በ1803 ከታተመዉ የሜክሲኮ ማስታወሻ ከተባለዉ መፅሐፉ እንደምናነበዉ፣ ሁሉም ነገር አንዱ ከሌላዉ የተቆራኘ ነዉ-የሚል ነዉ።»

ይሁና የሩቁ ዓለም ዓይደለም የሁምቦልት ሐገር ጀርመንን ጨምሮ ዛሬ የ«ምዕራብ» የሚባሉት መንግሥታት እንኳን የሁምቦልትን አስተሳሰብ እምነት ደግፈዉ፣ የጋራ ጥቅማቸዉን በጋራ ለማስከበር የተባበሩት በሁለት ዘግናኝ ጦርነቶች ሚሊዮን ወገኖቻቸዉን ከቀበሩ፣ ቢሊዮነ፤ ቢሊዮናት ዶላር ከከሰሩ፤ ከሁሉም በላይ ኮሚኒዝም ሞስኮ ላይ ከተጠናከረ በኋላ ነበር።

የምዕራብ-ምሥራቅ መሪዎች በኑክሌር ቦምብ ለመጠፋፋት በሚዛዛቱበት በ1963 ሙኒክ፣ ጀርመን ላይ የተመሠረተዉ የዛሬዉ የፀጥታ ጉባኤም በሁለቱ ከባድ ጦርነቶች የደረሰዉ ጥፋት እንዳይደገም፣ ልዩነትን በድርድርና ዉይይት ለመፍታት እንዲረዳ ታስቦ ነዉ።በየዓመቱ አንዴ የሚደረገዉ ጉባኤ በተለይ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተዉን የምዕራቦችን አንድነት ለማፅናት በጅጉ ጠቅሟል።

የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ፣ የበርሊን ግንብ መናድ፣ የምስራቅ አዉሮጳ ኮሚንስቶች መጥፋትም ሆነ የሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ የምዕራቡን ዓለም አንድትም ሆነ፣ የሙኒኩን ጉባኤ ዓላማ ብዙ አልቀየሩትም።

በ2001 ዋይት ሐዉስን የተቆጣጠሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች ግን ዓለምን ብቻቸዉን «መጋለብ» ሲጀምሩ፣ በተለይም ኢራቅን ለመዉረር ሲዝቱ ብዙዎች እንደሚሉት ጠንካራዉን ይሰነጣጥቀዉ ያዘ።

ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊ ቡሽ የለንደን፣ ማድሪድ፣ሊዝበን ጭፍን ደጋፊዎቻቸዉን አስከትለዉ ኢራቅን ለመዉረር ጦራቸዉን በሚያደራጁበት መሐል በተሰየመዉ በ39ኛዉ የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ላይ የተባለዉ የሰባ ዘመኑ አንድነት የመፍረከረኩ ምልክት ነበር።

በጉባዉ ላይ የዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት ወክለዉ የተገኙት የያኔዉ መከላከያ ሚንስትር ዶንልድ ራምስፌልድ ነበሩ።ጀርመንን የወከሉት ደግሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዮሽካ ፊሸር።የካቲት 9 2003።

«ለዚሕ ነዉ አሁን ለዚሕ (ለኢራቅ ወረራ) ቅድሚያ የሚሰጥበት ምክንያት ለምድነዉ ብዬ የምጠይቀዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ለኛ ዴሞክራሲ ላደረገችዉ አስተዋፅዕ እናመሰግናለን።ዩናይትድ ስቴትስ ለነፃነትና መረጋጋት መቆምዋ አያጠያይቅም።ለጀርመን ደግሞ ልዩ ትርጉም አላት።ምክንያትም (ካለ አሜሪካ ድጋፍ) እራሳችንን

ከነትዚ ነጻ ማዉጣት ባለመቻላችንና ዴሞክራሲያችንን መገንባት አንችልም ነበርና።የኔ ትዉልድ ከዚሕ የተማረዉ ምክንያታዊ መሆንን ነዉ።በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምክንያት ለማቅረብ ደግሞ መጀመሪያ እራስሕን ማሳመን አለብሕ።ይቅርታ አድርጉልኝ እኔን አላሳመነኝም።ይሕ ነዉ ችግሬ።»

የፊሸር ምክር ማስጠንቀቂያ የአብዛኛዉ ዓለም ፖለቲከኞች፣ የዲፕሎማቶችም እምነት አቋምም ነበር።የብሪታንያና የዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የድፍን ዓለም ሕዝብ የአደባባይ ተቃዉሞ ነበር።በኃይል የታበዩት የዋሽግተን ለንደን መሪዎች ግን ምክር ተቃዉሞዉን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትንም ደንብ ጥሰዉ ኢራቅን የእብሪት ማስተንፈሻቸዉ አደረጓት።

ወረራዉ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ሺሕ የሚገመት ኢራቃዊ ገድዷል።ሐብታሚቱን ሐገር  ወደ ድንጋይ ዘመን ሐገርነት ለዉጧታል።450 አሜሪካዊ፣ 500 ግድም የብሪታንያና የሌሎች ተባባሪ ሐገራት ወታደር ሞቷል።በመቶ የሚቆጠር የአሜሪካና የተከታዮችዋ ሐገራት የኮንትራት ሠራተኛ ተገድሏል።ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ከስራለች።

ከዚያ ጥፋት ከዩናይትድ ስቴትስና ከብሪታንያ ፖለቲከኞች ቀደም የሚማር ፖለቲከኛ በርግጥ ባልኖረ ነበር።ግን የተማረ አይደለም ለመማር የፈለገ የለም።ከጥፋቱ መማር የሚገባቸዉ የብሪታንያ ፖለቲከኞች ከአዉሮጳ ወዳጆቻቸዉ ጋር ትልቅ የመሆንን የሕብረት መንገድ ተቃዉመዉ ትልቅ ሐገራቸዉን ትንሽ ለማድረግ ቁልቁል እያንደረደሯት ነዉ።

የለንደን ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች ብሪታንያ ከአዉሮጳ ሕብረት ከወጣች የሕብረቱ ፍፃሜ እንደሆነ ይናገራሉ።የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ የበላይ ኃላፊ ቮልፍ ጋንግ ኢሽንገር እንደሚሉት ግን ሐቁ ተቃራኒዉ ነዉ።«የአዉሮጳ የአንድነት ፕሮጀክት ሊናድነዉ የሚለዉ አስተሳሰብ ይሰማል።ስሕተት ነዉ።እንደዉነቱ ከሆነ የአዉሮጳ ሕብረት በብዙ ሐገራት ያለዉ ሕዝባዊ  ድጋፍ  እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም።»

የከፋዉ የዩናይትድ ስቴትስ ነዉ።«የናንተን አምጡ-የኔን አትኩ» ዓይነት መርሕ የሚያራምዱት የአሜሪካ መሪዎች ያቺን ትልቅ፣ሐብታም፣የዴሞክራሲያ አብነት ሐገርን ለብቻዋ እያከነፏት ነዉ።ወዳጅ ከጠላት ሳይለዩ የሚናደፉት ፕሬዝደንት

ዶናልድ ትራምፕና ሹመኞቻቸዉ የጀርመን መኪኖች ለአሜሪካ ደሕንነት አስጊ ናቸዉ እስከማለት ደርሰዋል።መራሔ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የዋሽግተኖችን ማንአሕሎኝነት ለማሳጣት ጥሩ ምሳሌ አደረጉት።

«እንዲያዉ እስኪ ተመልከቱ፤ በአዉቶ ሞቢሎቻችን እንኮራለን።መኩራትም እንችላለን።እነዚሕ መኪኖች የሚሰሩት አሜሪካ ዉስጥ ነዉ።ከትላልቆቹ ፋብሪካዎች አንዱ የሆነዉ የBMW ፋብሪካ የሚገኘዉ ደቡብ ካሮላይና ነዉ።ባየር አይደለም።ደቡብ ካሮላይና ነዉ።ደቡብ ካሮላይና መኪኖቹን ወደ ቻይና ትልካለች።ባየር የሚሰሩት መኪኖች ደቡብ ካሮላይና ከሚሰሩት የበለጠ የዩናይትድ ስቴትስን ደሕንነት ያስጋሉ? ይሕ ያስደንግጠናል።»

ዓለም አቀፍ ዉሎችን፣የንግድ፣የጦር መሳሪያ ምርት ቁጥጥር ስምነቶችን  ያፈራረሱት ዶናልድ ትራምፕ የአዉሮጳና የእስያ መሪዎችም ዋሽግተኖች የሚጠይቁትን እንዲከፍሉ፣የሚሉትንም እንዲያከብሩ እየገፉ፣እያስፈራሩም ነዉ።በሙኒኩ ጉባኤ ላይ ትራምፕን የወከሉት ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ በተለይ የኢራንን ደገሙት።

«የአዉሮጳ ሸሪኮቻችን በገዳዩ አብዮታዊ ሥርዓት ላይ የጣልነዉን ማዕቀብ አሳንሰዉ መመልከታቸዉ የሚያቆሙበት ጊዜ አሁን ነዉ።የአዉሮጳ ሸሪኮቻችን ከኛ፣ከኢራን ሕዝብ፤ከአካባቢዉ ተባባሪዎቻችንና ከወዳጆቻችን ጋር የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነዉ።የአዉሮጳ ሸሪኮቻችን እኛ እንዳደረግነዉ ሁሉ የኢራን (የኑክሌር) ስምምነትን የሚያፈርሱበት ጊዜ አሁን ነዉ።»

የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የመሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ አፀፋ አዉሮጳ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

«አዉሮጳ፤ የዩናይትድ ስቴትስን የተናጥል ማዕበልን ለማምለጥ መዋኘት ከፈለገች ዉኃ እንዲነካት መዘጋጀት አለበት።ለድርድር ዝግጁ መሆናችንን የማሳየታችንን ያክል፣ለደሕንነታችን፣ለመረጋጋታችንም ሆነ ለብልፅግናችን የሌሎች ጥገኞች አይደለንም።»

ከዓለም ትልቁ የፀጥታ ጉዳይ ጉባኤ ሲደረግ ዘንድሮ ሲደረግ 55ኛዉ ነዉ።

በ2003 ጀርመንኛን ከእንግሊዝኛ እየቀየጡ የተናገሩት የዮሺካ ፊሸር ማስጠንቀቂያ ጎልቶበት ነበር።የ2007ቱ ጉባኤ የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ላይ ያሰሙት ጠንካራ

ትችት መለያዉ ነበር።አምና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር ኃይል «መትቶ የጣለዉ የኢራን ሰዉ አልባ አዉሮፕላን አካል» ያሉትን የብረት ቁራጭ ለጉባኤተኞች አቅርበዉበት ነበር።ዘንድሮ የአትላንቲካ ማዶ-ለማዶ ወዳጆች ልዩነት ነዉ-የጎላበት።

የጉባኤዉ የበላይ ኃላፊ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር ከጉባኤዉ በፊት ባሳተሙት መጣጥፍ እንዳሉት የአዉሮጳ አሜሪካኖች አንድነትን የሚያሰጉት ቭላድሚር ፑቲን አይደሉም።ዶናልድ ትራምፕ እንጂ።አዉሮጶች፣ አንጋፋዉ ዲፕሎማት እንደሚሉት ዕቅድ 2 (ፕላን B) ያስፈልጋቸዋል።ሜሪክል ግን አሁንም ትብሩ ይሻላል ባይ ናቸዉ።

«እኔ አበክሬ እንደማምነዉ አንድን ነገር ለብቻ መፍሔ ለመስጠት ከመሞከር----- በጋራ መሥራቱ ይመረጣል።በዚሕም ምክንያት፣ ክቡራትና ክቡራን፣ ትናንትና ማታ ይሕን ንግግሬን ሳዘጋጅ፣ ሴናተር ሊንድሴይ ግራሐም የተናገሩትን ጥቅስ በማየቴ ደስ አለኝ።«ትብብር ዉስብስብ ጉዳይ ነዉ፣ ይሁንና በተናጥል ከመኖር ይሻላል።ለዚሕ ዘመን ዓላማ ትክክለኛዉ ነገርም ይኸዉ ነዉ።የዚሕን ትልቅ እንቆቅልሽ ሚስጥር  ማን  ይፈታዋል? እኛ በጋራ ስንሆን እንጂ።»

ተቀባይ ያገኙ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic