የ“አቤና ከቤ” ፈጣሪዎች | ባህል | DW | 11.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የ“አቤና ከቤ” ፈጣሪዎች

የኢትዮጵያ መንግስት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን ማህበራዊ ድረ-ገጾች ከአልሚነታቸው ይልቅ አጥፊነታቸው ጎልቶ እንዲታይ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ማህበራዊ ድረ-ገጾች በወጣቶች ዘንድ የፈጠራ ክህሎታቸውን ማዳበሪያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በፌስቡክ ቀልዶችን በማቅረብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያፈሩ ወጣቶች ለዚህ አብነት ናቸው ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:44
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:44 ደቂቃ

ቀልዶችን ለ1 ሚሊዮን የፌስቡክ ተከታዮች

ሁለቱም ወጣቶች ናቸው፡፡ የ15 እና የ19 ዓመት አዳጊዎች፡፡ አንደኛው በሥተ-ምስራቅ በሐሮማያ ሌላኛው ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሚዛን ተፈሪ ይኖራሉ፡፡ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀትን ንደው በፌስ ቡክ ተዋወቁ፤ ጓደኛ ሆኑ፡፡ በአካል ሳይገናኙ፣ ቀልዶች ብቻ የሚስተናገዱበት ገጽ ከፍተው ሚሊዮን የተሻገረ ተከታታይ አፈሩ፡፡ አማኑኤል እና ያሬድ ይባላሉ፡፡ ተዋወቋቸው፡፡ የ“አቤና ከቤ” የፌስቡክ ገጽ ጠንሳሽ እና መስራቾች ናቸው፡፡

“አቤና ከቤ” ገጸ ባህሪዎች ናቸው፡፡ ቀልደኞች፡፡ እጥር ምጥን ያሉ አስፈጋጊ ምልልሶችን በማቅረብ በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ በድምጽ እና በቪዲዮ ከመምጣታቸው በፊት ተከታታዮቻቸው የሚያውቋቸው በምስል ብቻ ነው፡፡ ሀጫ በረዶ የመሰለ ጥርሶቻቸውን እና አፍሮ ጸጉራቸውን በትልቁ የሚያሳየው ምስላቸውም ቢሆን በ“ካርቱን” መልክ የተሳለ እና በግራፊክስ የተቀናበረ ነው፡፡ ሊያውም በኢትዮጵያ አይደለም በምስራቅ አውሮፓዊቷ ሀገር ዩክሬን እንጂ፡፡  

የ15 ዓመቱ አማኑኤል በላይነህ “አቤና ከቤ” እንዴት እንደተጀመረ ከስር መሰረቱ ጀምሮ ያስረዳል፡፡ “ያሬድ አስቂኝ የሆነ ልጅ ነው፡፡ ሰውን ማዝናናት፣ መሳቅ የሚወድ ልጅ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሌላ ሀገር የተለመደ ነገር ነበር፡፡ የሆነ [የፌስቡክ] ገጽ ነበር፡፡ እርሱ ገጽ ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ አይመጣም? ለምን እኛ በምንረዳው ቋንቋ ጥሩ ጥሩ ቀልዶችን ፖስት ማድረግ አንጀምርም? በሚለው ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ እኔም ፍላጎት አደረብኝ” ይላል እንዴት ከያሬድ ጋር እንደተጣመረ ሲያስረዳ፡፡

ገጸ-ባህሪያቱ እንዴት እንደተቀረጹ ሲያብራራ ደግሞ  “ልብወላዳዊ ገጸ-ባህሪያቱን የፈጠረችልን ዩክሬናዊት ናት፡፡ በእርግጥ ለእኛ አይደለም የፈጠረቻቸው፡፡ ለዓለም አቀፍ [ጥቅም] ብላ ነው፡፡ እኛ አነጋግረናት ገዝተናት ነው የወሰድነው” ይላል፡፡

እንዲህ መልክ መልክ የያዙት “አቤና ከቤ” ሳቅ የሚያጭሩ ጉዳዮችን የሚያነሱ ዋዘኛ ወጣቶች ተደርገው ተቀርጸዋል፡፡ መስራቾቹ ከትምህርት ቤት ውሎ እስከ ፍቅር ግንኙነት፣ ከማህበራዊ እስከ ሀገራዊ  ጉዳዩችን እየመዘዙ ያዝናናሉ፣ይሳለቃሉ ሲላቸው በጎን ይተቻሉ፡፡ ወቅታዊ መነጋገሪያዎችን ቀልድ ቀላቅለውበት እና አዋዝተው ወደ ፌስ ቡክ ገጻቸው ያመጣሉ፡፡ ራሳቸው የሚፈጥሯቸው ቢኖሩም ብዙዎቹን ግን የቀልድ ተሰጥኦው ካላቸው ተከታዮቻቸው ይቀበላሉ፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ የደረሳቸውን ሁሉ ለቀልዶቻቸው ግብዓትነት ይጠቀሙበታል ማለት እንዳልሆነ አማኑኤል ይናገራል፡፡

“እኛመድረኩን ነው የፈጥረነው፡፡ ሙሉ ቀልዶቹን የምንጽፈው እኛ አይደለንም፡፡ የተለያዩ ቀልዶችን ሰዎች ይልኩልናል፡፡ እኛም እንፈልጋለን፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ላይ አቀናጅተን፣ አርትኦት ሰርተን፣ ፖስት እንደርጋለን፡፡  ሁሉም የቡድኑ አባላት የሚከተሉት መመሪያ አለን፡፡ ከወሲብ፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነገር እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የሚያስከፉ ነገሮችን በሙሉ ላለማካተት የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከሚደርሰን ሃምሳ በመቶው ፖስት የማናደርጋቸው ነገሮች ናቸው” ሲል ያብራራል፡፡  

 

አንድ ቀልድ ለአቅመ ዕይታ ከመብቃቱ በፊት ይህን ማለፍ ቢጠበቅበትም መስራቾቹ እና የገጹ አንቀሳቃሾች “አቤና ከቤ”ን ከአዳዲስ ቀልዶቻቸው ጋር በየቀናት ልዩነት ውስጥ ይዘው ከተፍ ይላሉ፡፡ አስገራሚው ነገር ይህን የሚያደርጉት ሰዎች በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ እና በአይን እንኳ ተያይተው የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ በዚያው በፌስ ቡክ እና በኢንተርኔት መልዕክት መለዋወጫዎች በመታገዝ ስራቸውን ያቀላጥፉታል፡፡

ሁለቱ መስራቾች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት ስራቸው እውቅና አግኝቶ ለሽልማት አዲስ አበባ የተጠሩ ጊዜ ነበር፡፡ የ19 ዓመቱ ያሬድ አያሌው ያን ጊዜ ሲያስታውስ ፈገግ ይላል፡፡

“ፌስ ቡክ ላይ ብቻ ነበር የምንተዋወቀው፡፡ በ‘ድሬ ቲዩብ አዋርድ’ በኩል ልንገናኝ የቻልነው፡፡ ስንገናኝ ልክ የማውቀው ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ አጠገቡ ስሆን አዲስ ሰው አልሆነብኝም፡፡ ትንሽ ቁጭ ብለን ተጫወተን፡፡ ከቡድናችን ጋር አውርተን ቀጥታ ወደ ሸራተን ነበር ያመራነው፡፡ እዚያ ስንገባ ብዙ ሰው አላወቀንም፡፡ ምክንያቱም ‘አቤና ከቤ’ ሲባል የሚያስቡት ሁለት አፍሮ፣ ፀጉራቸው ጉፈሬ የሆኑ [ሰዎችን] እንደዚያ ነበር የሚያስቡት፡፡ ‘አቤና ከቤ’ አሸናፊ ናቸው ተብሎ [ወደ መድረክ] ስንወጣ፤ በአካል ስለማያውቁን፤ ሰው ሁሉ ተገርሞ ነበር፡፡ ‘አቤና ከቤ’ ሲባል በጣም ትልልቅ ሰው ነበር የጠበቁት” ይላል ያሬድ ባለፈው ዓመት የካቲት በተካሄደው የ‘ድሬ ቲዩብ’ ሽልማት ስነስርዓት የገጠመውን ሲተርክ፡፡   

ሁለቱ ወጣቶች ለእውቅና እና ሽልማት የበቁት ፈጥነው ቢመስልም በብዙ ውጣ ውረድ አልፈዋል፡፡ ገና ሀሳቡ ሲጠነሰስ የያሬድ የግል ሙከራ ብቻ ነበር፡፡ ቀልድ የሚያዘወትረው ያሬድ የራሱንም ሆነ ከሌሎች ቦታዎች ያገኘውን ቀልዶች በግል ገጹ ላይ ይጽፍ ነበር፡፡ ይህን ጥረቱን ያደንቅለት የነበረው ትንሹ አማኑኤል “ለምን አብረን እየሰራን ቀልዶችን በተከታታይ አናወጣም” ሲል የአጋርነት ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ ያሬድ ይስማማል፡፡ ያኔ “አበበ እና ከበደ” የተባለው ገጽ ይወለዳል፡፡

“ስሙን እንዴት መረጣችሁት?” ሲባሉ “ትምህርት ቤት እንኳ ምሳሌ ሲሰጥ አበበ እና ከበደ መች ይቀሩና” ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በወቅቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢሆኑም፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያንደረድራቸው የመሰናዶ ትምህርት ቤት ትልቅ ፈተና ከፊታቸው ቢደቀንም በትርፍ ጊዜያቸው ቀልዶችን ከማጋራት አልተቆጠቡም፡፡ በአጭር ጊዜ ወዳጃቸው በዛና የፌስ ቡክ ተከታያቸው ቁጥር መቶ ሺህ ደረሰ፡፡ ሆኖም ይጠቀሙበት የነበረው የገጸ ባህሪያቱ ምስል ከኢንተርኔት ያለፍቃድ የወሰዱት ነበርና ፌስ ቡክ የቅጂ መብት (ኮፒ ራይት) ደንቤን ጥሳችኋል ሲል ይዘጋባቸዋል፡፡

ሌላ ገጽ ከፍተው ሲመለሱ መላ ይዘይዳሉ፡፡ ከፌስቡክ ተሻግረው በመደበኛ ድረ ገጽ ቀልዶቻቸውን ለማቅረብ ሰዎች ሲያነጋግሩ እነርሱ ከሚጠቀሙበት ስም ጋር የሚመሳሰል ገጽ ቴዎድሮስ ደለለኝ በተባለ ወጣት በባለቤትነት እንደተያዘ ይረዳሉ፡፡ ቴዎድሮስን አፈላልገው በኢ-ሜይል እና ፌስ ቡክ ያነጋግሩታል፡፡ ስማቸውን ከ“አበበ እና ከበደ” ቀለል ወዳለው እና ለአጠራር ወደሚመቸው “አቤና ከቤ” እንዲቀይሩት ይመክራቸዋል፡፡ የራሱን መደበኛ ድረ-ገጽ ይዞ አብሯቸው ሊሰራ እንደሚችልም ይገልጽላቸዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ ከ“አቤና ከቤ” ገጽ ጀርባ ያሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ ሶስት እንዲያድግ ምክንያት ሆነ ፡፡       

“አቤ እና ከቤ” ከጹሁፍ እና ከካርቱን ስዕል ተሻግረው በድምጽ መደመጥ እና በተንቀሳቃሽ ምስል መታየት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ነበር፡፡ እስካሁን ሰባት አጫጭር ቪዲዮዎች ለአድናቂዎቻቸው ጀባ ብለዋል፡፡ ከዚህ ጉልህ እመርታቸው ጀርባ የ20 ዓመቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ዘአማኑአል አበራ አለ፡፡ አራተኛ የ“አቤና ከቤ” ቡድን አባል የሆነው ዘአማኑኤል ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሚያቀናብራቸው ቪዲዮዎች በራሳቸው የ“ዩ-ቲዩብ ቻናል” እና ድረ ገጽ አማካኝነት ይታያሉ፡፡ በፌስ ቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም እና ጉግል ፕላስ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ገጾቻቸው ላይም ያጋሯቸዋል፡፡

የኢንተርኔቱን አለም ከተቀላቀሉ ዓመት ሊደፍኑ ቀናት የቀራቸው “አቤና ከቤ” አንድ ሚሊዩን ተከታይ ያፈሩት ገና መስከረም ሳይጠባ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የፌስቡክ ገጾች ይህን ያህል ተከታይ ማግኘት የተለመደ አይደለም፡፡ በአብዛኛው ክህዝብ በተሰበሰበ ድምጽ “አቤና ከቤ”ን በአመቱ የምርጥ ኮሚዲያን ዘርፍ የሸለማቸው ድሬ ቲዩብ እንኳ አንድ ሚሊዮን ተከታይ ለማግኘት ሰባት አመት ወስዶበታል፡፡ የድሬ ቲዩብ መስራች እና ባለቤት ቢኒያም ገረሱ ከ“አቤ እና ከቤ” ፈጣን እድገት ጀርባ ያሉትን ምክንያቶች እንዲህ ይዘረዝራቸዋል፡፡

“የአቀራረብ ስታይላቸው፣ የሰጧቸው ልብ-ወለዳዊ ገጸ-ባህሪያት፣ እነዚያ ሰዎች የሚነጋገሩት ለየት ይላል፡፡ እኛ ከለመድነው ውጭ በመሆኑ ያ በእርግጠኝነት ከፍተኛ ቦታውን ያሰጣቸው፡፡ ፌስቡክ [ገጻቸውን] የከፈቱት በቅርብ ነው፡፡ ከእኛ ጋር ሲነጻጸር እኛ ፌስቡክን የጀመርነው [እ.ኤ.አ] በ2008 ነው፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ 500 ሺህ እንኳ የሚሆኑ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አልነበሩም፡፡ አሁን ግን በዝተዋል፡፡ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች አራት ሚሊዮን አልፈዋል፡፡ በፈጣን ሁኔታ ለማደጋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ስራቸው ነው” ሲል 2.4 ሚሊዩን ተከታታዮች ያሉትን የ“ድሬ ቲዮብ” የፌስቡክ ገፅ የሚያንቀሳቅሰው ቢኒያም ይተነትናል፡፡ 

የ“አቤና ከቤ” ተወዳጅነትን የተመለከተ ዩናስ አለማየሁ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ባለሙያ የመስራቾቹን ጥረት ወደሌላ ደረጃ የሚያሸጋግር በረከት አምጥቶላቸዋል፡፡ በሰበብ አስባቡ ማህበራዊ ድረ ገጾች በሚዘጉባት ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለመጎብኘት ፍቱን መፍትሄ የሆነውን ራሱን የቻለ “አፕልኬሽን” ሰርቶላቸዋል፡፡ ይህ አበርክቶቱም የ“አቤና ከቤ”ን ቡድን በአምስተኛነት እንዲቀላቀል አድርጎታል፡፡ እስካሁን ድረስ ሃምሳ ሺህ ያህል ሰዎች “አንድሮይድ” ለሚጠቀሙ ዘመናዊ ሞባይሎች የተሰራውን “አፕልኬሽን”በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው መጫናቸውን የቡድኑ አባላት ይናገራሉ፡፡

መንግስት በኢትዮጵያ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ እንኳ “አቤና ከቤ” በመቶ ሺህዎች ከመጎብኘት አሁንም አላገደውም፡፡ በሳምንት አንድ ሚሊዩን ገደማ ሰዎች የሚመለከቱት ገጽ አሁን ላይ በ350 ሺህ ብቻ መወሰኑን መስራቾቹ ይናገራሉ፡፡ ሁሉ ነገር ወደነበረበት ሲመለስ ግን የጎብኚያቸው እና የተከታያቸው ቁጥር እንደሚያሻቅብ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ እስከዚያው ከቀርፋፋው እና እንደልብ ከማይገኛው የኢንተርኔት አገልግሎት ጋር እየተንገታገቱም ቢሆን ቀልዶችን ከማጋራት ወደኋላ አላሉም፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ

 

Audios and videos on the topic