የአሸባብ ጥቃት፤የኬንያ አፀፋና ሰብአዊ መብት | አፍሪቃ | DW | 25.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአሸባብ ጥቃት፤የኬንያ አፀፋና ሰብአዊ መብት

አልሸባብ በማንዴራ ከተማ 28 ሰዎችን ከገደለ በኋላ የኬንያ መንግስት የወሰደው የበቀል እርምጃ ለትችትና ወቀሳ አግልጦታል።የኬንያ መንግስት ችግሩን ለማስወገድ የጸጥታ ተቋማትን እንዲያጠናክርም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እያሳሰቡ ነዉ።

በኬንያ ሰሜን ምስራቅ ከምትገኘው ማንዴራ ከተማ ወደ ናይሮቢ ይጓዝ የነበረው አውቶቡስ ስድሳ ሰዎችን አሳፍሮ ነበር። ከመነሻው አርባ ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዘ በኋላ ግን ያልተጠበቀው ተከሰተ። አውቶቡሱን ያስቆሙት ታጣቂዎች 19 ወንዶች እና ዘጠኝ ሴቶችን መንገደኞችን ገደሉ። ከሟቾቹ መካከል ሃያ አራቱ መምህራን ሶስቱ የህክምና ባለሙያዎች እንደነበሩ ተነግሯል። ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደው አልሸባብ እርምጃውን በሞምባሳ መስጊዶች የኬንያ ወታደሮች ለፈጸሙት ድርጊት የአጸፋ ምላሽ ነው ሲል አስታውቆ ነበር።

የኬንያ መከላከያ ሰራዊት በተዋጊ ጀቶችና ሄሊኮፕተሮች ጭምር ባደረጋቸው ሁለት የበቀል ዘመቻዎች የአሸባብ ታጣቂዎች ያላቸዉን ከ100 በላይ ሰዎች መግደሉን እና አራት የጦር ካምፖች ማውደሙን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ ተናግረዋል።

አል-ሸባብ በኬንያውያን ላይ -የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ደግሞ በአል-ሸባብ ላይ የፈጸሙት ጥቃት ግን በሃገሪቱ ዜጎች ላይ ስጋት ፈጥሯል። የሙያ ማህበራት አባሎቻቸው ጥቃቱ ከተፈጸመበት የሰሜን ምስራቅ ኬንያ ግዛት እንዲወጡ ማስጠንቀቃቸውን ኤ.ኤፍ.. የዜና ወኪል ዘግቧል።የኬንያ መንግስት ወሰድኩት ያለው የበቀል ዘመቻ ደግሞ በሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ለተቃውሞ ወደ ናይሮቢ አደባባይ እንዲወጡ አስገድዷቸዋል። 'ዩሪያ' የተባለውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በኃላፊነት የሚመሩትና በተቃውሞው የሚካፈሉት ይሱፍ ሉሌ በኬንያ መከላከያ ሰራዊት የተወሰደው የበቀል እርምጃ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

''ለእኛ የሚጠቅመን በመንግስትና በአል-ሸባብ መካከል የሚደረገው የበቀል እርምጃ አይደለም ብዬ አምናለሁ። እንደ ማህበረሰብና እንደ ህዝብ የሃገሪቱ ደህንነት ሁኔታ የሚደረግበት መንገድ ነው ሊያስጨንቀን የሚገባው።አለበለዚያ በአል-ሸባብ ላይ የምንወስደው የበቀል እርምጃ መቀጠል ምንም አይጠቅመንም። ባለፈው አንድ አመት ከስድስት ወር ተመሳሳይ ነገር ነው ሲፈጠር የነበረው። በመኖሪያ አካባቢያችን ደህንነት ላይ ምንም የቀየረው ነገር የለም።''

የኬንያ ፖሊስ በሞምባሳ መስጊዶች ባደረገው አሰሳ ከ350 በላይ ሰዎችን ማሰሩንና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን መያዙን አስታውቋል። ኬንያ ወደ ሶማሊያ እ... 2011 ወታደሮቿን ከላከች ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ይሱፍ ሉሌ የኬንያ መንግስት አል-ሸባብ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች ተከትሎ የበቀል እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የሃገሪቱን የደህንነት ተቋም ማጠናከር እንደሚገባ ይናገራሉ።

«እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሃገሪቱን የጸጥታ ስጋት በተመለከተ በቂ መረጃ መሰብሰብ በሚያስችል መንገድ ኬንያ የጸጥታ ጥበቃዋን እንድታጠናክር አሳስባለሁ። ከፍተኛ ገንዘብ የተመደበለት የደህንነት ተቋም አለን። ይህ የደህንነት ተቋም እንዲህ አይነት የደህንነት ስጋቶችን አስቀድሞ መለየት እና ማምከን መቻል አለበት።የማህበረሰቡ እና የኬንያ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከታች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ሹማምንት ድረስ ልናሳትፍ ይገባል»

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic