የአሸባብ ጥቃትና የሶማሊያ መንግስት ድክመት | አፍሪቃ | DW | 05.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአሸባብ ጥቃትና የሶማሊያ መንግስት ድክመት

የአሸባብ ታጣቂ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኝ የደህንነት ጽ/ቤት ላይ በፈጸመው ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ።

አዲሱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊም ሆኑ የሶማሊያ መንግሥት፤ አሸባብ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች ከመኮነን ባለፈ መከላከል አለመቻላቸውን በሶማሊያ የሚገኘው የዶይቼ ቬሌ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ኦማር ሑሴን ተናግሯል።

የጎሮጎሮሳውያኑ አዲስ አመት ከገባ ይህ የአልሸባብ የመጀመሪያ ጥቃት ነው። በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኝ የደህንነት ጽ/ቤት ላይ በተፈጸመው ጥቃት አምስት ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በሞቃዲሾ የሚገኘው የዶይቼ ቬሌ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ኡመር ሑሴን አሸባብ ሃላፊነቱን ለወሰደበት ጥቃት የሶማሊያ መንግሥት ቡድኑን ከመኮነን ያለፈ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉን ይናገራል።

«ይህ መኪና ላይ የተጠመደ ቦንብ የፈነዳው ትናንት ወደ አየር ማረፊያ በሚወስደው መንገድ ላይ ነው። በጥቃቱ አምስት ሰዎች መሞታቸውን እና ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን ከሆስፒታል የሚገኙ ምንጮች ነግረውናል። የሶማሊያ መንግሥት ባለስልጣናት በከተማዋ የሚከሰቱትን ጥቃቶች ለመከላከል እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ይሁንና የአሸባብ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባትና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት መፈጸም ችለዋል።የመንግሥት ባለስልጣናት ይህንን ጥቃት አስቀድመው መከላከል አልቻሉም»
የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽ/ቤት እና በርካታ ኤምባሲዎች በሚገኙበት የሶማሊያ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ለተፈጸመው ጥቃት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ሃላፊነት መውሰዱን አሶሼየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። በቅርቡ ኦማር አብዲራሺድ አሊን በጠቅላይ ሚኒስቴርነት የሾመው የሶማሊያ መንግሥት በእርስ በርስ ጦርነት እና የጎሳ ፖለቲካ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ስትታመስ የቆየችውን ሃገር እንደገና ለመገንባት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ሳንካ ሆኖበታል። በሃገሪቱ የሚገኙት ከ22,000 በላይ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪዎችም ሆኑ ከምዕራባውያን ለሶማሊያ መንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዲራሺድ አሊ ወደ ስልጣን ሲመጡ ቅድሚያ የሰጡትን የደህንነት ችግር ለመቅረፍ አለመቻላቸውን መሐመድ ኦማር ሑሴን ይናገራል።

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ለሃገሪቱ የደህንነት ችግር ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረው ነበር። ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ካቤኔ ባለመመስረቱ ምክንያት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ስራ መስራት አልቻሉም። ስለዚህ በቃላቸው መሰረት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠትና የአሸባብ ታጣቂዎችን ከከተማዋ ለማጥፋት ጊዜ የሚወስድባቸው ይመስለኛል።»

ባለፈው ወር የአሸባብ ታጣቂዎች የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ የጦር ሰፈርን በማጥቃት ቢያንስ ስምንት ሰዎች መግደላቸው አይዘነጋም። አሸባብ በሶማሊያ የነበረውን ጠንካራ ይዞታ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ቢነጠቅም በሞቃዲሾ እና ኬንያ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች አሁንም የቀጠናው ስጋት እንደሆነ ነው።


እሸቴ በቀለ
ልደት አበበ

Audios and videos on the topic