የአሸባሪ ጥቃት በፓሪስ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 14.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአሸባሪ ጥቃት በፓሪስ

ፓሪስ ፈረንሳይ ዋና ከተማ በደረሰ የአሸባሪ ጥቃት ከ 128 ሰዎች በላይ ተገደሉ። በጥቃቱ ቢያንስ ወደ 200 ሰዎች ተጎድተዋል። ከሰማንያ የሚበልጡት በጽኑ መቁሰላቸዉም ተገልጿል። እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ትናንት አርብ ምሽት ለደረሰዉ ጥቃት ተጠያቂዉ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን መሆኑ ገልፀዋል። አሸባሪዉ ቡድን ጦርነት ርምጃ ማካሄዱን ፕሬዚዳንት ኦሎንድ ተናግረዋል። በፈረንሳይ የአስቸካይ ጊዜ አዋጅም ተደንግጓል። ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጉዳይ ሊያደርጉት ያቀዱት ማንኛዉም ጉዞ እንዲሰርዙም ተደርጓል። በሃገሪቱ የሦስት ቀናት የሃዘን ጊዜ ታዉጇል።

እንደ ብዙኃን መገናኛዎች ዘገባ ጥቃቱ እንዲጣል የተሴረዉ ከፈረንሳይ ዉጭ ነዉ። በፈረንሳይ ዉስጥ ተባባሪ ወንጀለኛ ስለመኖሩ እንደሚጣራም ተመልክቶአል።

ትናንት አርብ ምሽት አሸባሪዎቹ ፈረንሳይ ፓሪስ በሚገኙ በተለያዩ ስድስት ቦታዎች ማለትም በርካታ ሕዝብ በተሰበሰበባቸዉ ቡና ቤቶች፤ የቀጥታ ሙዚቃ ማሳያ አዳራሽ፤ እንዲሁም የምግብ ቤት አዳራሽ ዉስጥ ነበር የያዙትን ቦንብ ያነጎዱት ሕዝብ ላይ ዙርያዉን ተኩሰዉ ግድያም ፈጽመዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድና የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ትናንት ምሽት ፓሪስ ዉስጥ በሚገኘዉ የብሔራዊ ስታዲዮም ዉስጥ የፈረንሳይና የጀርመን የብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን ጨዋታ በቀጥታ ለመመልከት በስታድዮሙ ዉስጥ ሳሉ ነበር በመጀመርያ ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ከፍተኛ ፍንዳታ ያደረሱት። የብዙኃን መገናኛዎች ፍንዳታዉ በከፍተኛ ሁኔታ እስከ ስቴዲዮሙ መሰማቱን ዘግበዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦሎንድ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ የተባለዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ፈረንሳይ ማወጃቸዉ ተነግሮአል። በተጨማሪም ሀገሪቱ ድንበርዋን በሙሉ እንድትዘጋ አዘዋል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ