የአስቸኳይ ግዜ አዋጅና ስራ ፈጠራ በኢትዮጵያ  | ኢትዮጵያ | DW | 06.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአስቸኳይ ግዜ አዋጅና ስራ ፈጠራ በኢትዮጵያ 

የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግስት፤«የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን» ያለዉን ዕቅድ ይፋ ያደረገዉ። ዕቅዱ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ዉስጥ ያሉ ስምንት ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር «በልማት» ለማጣመር ያለመ ነዉ ሲል መንግስት አቋሙን ገልፆ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:50

አስቸኳይ ግዜ አዋጅ

ይሁን እንጅ በስምንቱ ከተሞችም ሆነ በገጠራማ ቀበሌዎች የሚኖረዉ ሕዝብ ጉዳዩ ላይ አልተወያየም። በዉሳኔዉም አልተሳተፈም።

ከዚሕም በተጨማሪ ዕቅዱ በልማት ስም ገበሬዉን ከእርሻ ማሳዉ፤ ከተሜዉን ደግሞ ከይዞታዉ ያፈናቅላል፤ በሕዝቡ ባሕል፤ ቋንቋ እና አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚለዉ ሥጋት ሕዝብን ለተቃዉሞ ማነሳሳቱን ብዙ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

አምቦ ከተማ ዉስጥ የተጀመረዉ ተቃዉሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ተዛምቶ እና በሌሎች ቅሬታዎች ተጠናክሮ መላዉን ኦሮሚያ፤አማራንና የደቡብ መስተዳድርን በከፊል አዳርሷል።በአብዛኛዉ ወጣቶችን በአደባባይ ያሰለፈዉን ተቃዉሞ ለማቆም የመንግሥት ፀጥታ ኃይላት በወሰዱት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል።በሺ የሚቆጠሩ ቆስለዋል፤ተሰደዋል ወይም ተሰዉረዋል። በብዙ ሺሕ የሚቀጠሩ ታስረዋል።

መንግሥት ከኃል እርምጃዉ በተጨማሪ የተቃዉሞዉ መነሻ የሆነዉን «የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለዉን ዕቅድ መሰረዙን አስታዉቆ ነበር።ይሁንና ከዕቅዱ በተጨማሪ የሰብአዊ፤ ዲሞክራሲያዊ፤ አስተዳደራዊ፤ ቅሬታዎችን ያነሳዉ ሕዝብ በየአካባቢዉ የሚያደርገዉ ተቃዉሞ አልተገታም።

ተቃዉሞዉና ተቃዉሞዉን ለማፈን የሚወሰደዉ የኃይል እርምጃ ባለፈዉ መስከረም ማብቂያ «ከተራራዉ ጫፍ ሲደርስ» የኢትዮጵያ መንግስት  ለስድስት ወር የሚዘልቅ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ደንግጎ የኃይል እርምጃዉን በአዋጁ ሕጋዊ ሽፋን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በሚንስትር ማዕረግ የመንግሥት የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ኃላፊ  ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለዶቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን የደነገገዉ  ወድዶ ወይም ፈልጎ ሳይሆን ሁኔታዎች አስገድደዉት ነዉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደሳለኝ ኃይለ ማርያም መንግስታቸዉ በአዋጁ አማካይነት ሰላምና መረጋጋት ማስፈኑን ጠቅሰዉ  አዋጁን ለማንሳት ማቀዱን ይፋ አድርገዉ ነበር።ሚንስትር ነገሪ ግን አዋጁ በዚህን ቀን ሊነሳ ይችላል ወይም ሊራዘም ይችላል ብሎ ለመናገር ጥናት እየየተካሀደ መሆኑን ነዉ የገለፁት።

መንግስት አዋጁ ሰላምና ማረጋጋት አምጥቷል የሚለዉን ለመታዘብና ነዋሪዎችን  ለማነገር ከአድስ አበባ በአራቱም አቅጣቸዎች፣ ማለትም በአዳማ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታና በአምቦ መሰመሮች ተንቀሳቅሼ ነበር።

በተዘዋወርኩበት ጊዜና አካባቢ የመንገድ ላይ ተቃዉሞ  ወይም ተቃዋሚዎችን ለመበተን የፀጥታ ኃይላት መሳርያ ተኩስ ባይኖርም፤ ሰዎች አሁንም እየታሰሩ እንደሆነ፤ ሌሎች ሰባዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙባቸዉ ካነጋገርኳቸዉ ሰዎች መስማት ችያለዉ። ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ወጣት የአምቦ ነዋሪ አዋጁ ማህበረሰቡን ዉስጣዊ ሰላም ነፍጎታል ይላል፣ «ሰላም በቦታዉ የለም። የአምቦ ከተማ ነዋርዎች ዉስጣቸዉ ተጎድተዋል፣ ዉስጣቸዉ እያለቀሰ ነዉ። በዉሸት አረጋግተናል ይላሉ እንጅ አሁንም ጫናዎች አሉ። ከተሰጠዉ ሰዓት ዉጭ መሄድ አትችልም። ጥቂት ሰዎች ጋር ሆነ መቆም አትችልም። በሰዎች ዉስጥ ፍረሃት አለ።ሰዉ ኮማንድ ፖስት የሚባለዉን እንደ አዉሬ ይፈራዋል። ከመሸ በአዉሬ መበላት እንዳለ ዓይነት ሰዉ የኮማንድ ፖስቱን እርምጃ በመፍራት  በግዜ እቤቱ እየገባ ይገባል።»

ይህ ሁኔታ ባለበት ሰላም ወደ ቦታዉ ተመልሰዋል ማለት ይቻላል ወይ በማለት ሚንስትሩን ዶክተር ነገሪ ሌንጮን ስጠይቃቸዉ «ችግሮች ቀጥለዋል ለምባለዉ ነገር ምንም ችግር የለም ማለት አልችልም» ሲሉ መልሰዉልኛል።»

በሌላ በኩል ግን አስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጨርሶ መታወጅ አልነበረበትም የሚሉ አሉ።ማሕበረሰቡ ያነሳቸዉ ጥያቄዎች በአገር አቀፍ ደረጃ አዋጅ ለማወጅ የሚያደርስ አይደለም በማለት የሚከራከሩም አሉ።ተቃዋሚዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦብኮ) በበኩሉ መንግሥት የአስቸኳይ  ግዜ አዋጅ የደነገገዉ ለሚወስደዉ የኃይል እርምጃ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት እንጂ፤ በኦሮሚያ ክልል «አዋጁ ከታወጀ» ቆይቷል ይላል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ወቅት የሚፈፀሙ የሰባዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ የመርማሪ ቦርድ መቋቋሙን መንግሥት አስታዉቆ ነበር።ተጠሪነቱ ለሐገሪቱ ምክር ቤት የሆነዉ ቦርድ  በኦሮሚያ፤ በአማራም ሆነ በሌሎች ችግር ባለባቸዉ ክልሎች ይፈፀማል የሚባለዉን የሰባዊ መብት ጥሰቶች የመረመረበትን  ዘገባ እስካሁን አላቀረበም። ሚንስትሩ ዶክተር ነገር ሌንጮም ሥለ አጣሪ ቦርዱ ሥራ «ምንም የደረሳቸዉ መረጃ» እንደሌለ ይናገራሉ።

አገሪቱን የምመራዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ በአገርቱ የተፈጠረዉ የፖለትካ አለመረጋጋት የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ ጠቅሶ፣ ከዚሁ ጋር ለወጣቶች የስራ እድል አለመፈጠሩን እንደ ዋነኛ ምክንያት ጠቅሶታል። በተለይ የመልካም አስተዳደር እጦትን ለማቃለል ገዢዉ ፓርቲ፤ ከከፍተኛ እስከ ታችኛዉ የመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉ ባለሥልጣናት  «ጥልቅ ታሃድሶ» እንዳደረገ፣ ተናግሯል። የአሮሞ ፌዴራላስት ኮንግሬስ ምክትል ሊቀመንበር  አቶ ሙላቱ ገማቹ ግን ይህ ርምጃ «ፀበል ቀምሶ መመለስ»  ሲሉ ይተቻሉ።

ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መንግስት  በአገር አቀፍ ደረጃ 10 ቢሊዮን ብር ፈንድ ማዘጋጀቱንም ባለፈዉ ጥቅምት አሳዉታዉቋል። በክልል ደረጃም ኦሮሚያ 6,6 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተዘገብዋል።

የብሪታንያዉ አጥኚ ተቋም የቻተም ሃዉስ  አጥኚ ጄሰን ሞስሊ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 600,000 ወጣቶች ስራ ፈላጊዉን ማሕበረብ እንደሚቀላቀሉ፤ በፁሁፋቸዉ ይጠቅሳሉ። መንግስት ባለፉት አስር ዓመታት ሐገሪቱ ሥላስመዘገበችዉ የኢኮኖሚ ዕድገት  በሰፊዉ የሚናገረዉ በተጨባጭ ካለዉ የስራ እድል እዉነታ ጋር አለመጣጣሙ ለወጣቱ ትዉልድ ብዥታ መፍጠሩንም አጥኚዉ አብራርተዉ፤ ይሕም በወጣቱ ዘንድ ቅሬታን ኋላም ቁጣን ማስከሉን ሞስሊ ገልፀዋል።

ይህን ሃሳብ በከፊል የሚጋሩት ሚንስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የስራ እድል ፈጠራ መንግስት ዛሬ ያሰበዉ ጉዳይ እንዳልሆነና እየተማረ ያለዉ ኃይል ከልማቱ  ወይም ከኢኮኖሚ እድጋቱ ጋር ተመጣጥነዋል ብሎ መናር ይከብዳል ይላሉ።

ወጣቶቹስ ምን ይላሉ?

አለም ሙሊሳ ይባላል። የሰበታ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በባጃጅ አሽከርካርነት ይተዳደራል። አሁን መንግስት የያዘዉ የስራ እድል ፈጠራ ዕቅድ አካል መሆን እንደሚፈልግም ይናገራል።

በአምቦ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ወጣቶች ግን  ሥለ ሥራ ፈጠራ ከመናገር በፊት  የአከባብዉ ሰላም ይቀድማል ይላሉ።

«አዎ፣ ስራ አጥነት አለ። ስራ አጥነቱ እነሱ የሚያካሒዱት የፖለትካ እና  የትምህርት ስረዓት (ዉጤት ነዉ)። ሰላም ያለዉ ሰዉ፤ ያለዉን ነገር ሰርቶ ይበላል። ስራ ያለዉም ስራ የሌለዉም እየተገደለ ነዉ ። ስራ አጡ ነዉ ሁከት የምያነሳዉ ካሉ ይህ ትክክል አይደለም።»

«አሁን ይሄ የስራ እድል ፈጠራ የሚባለዉ አስቸጋሪ ነገር ነዉ። የሚፈጠር ስራ የለም። ስራ ያጣም በተቻለዉ አቅም እንደምንም ይተዳደራል። ስለዚህ ወነኛዉ ነግር የስራ ጉዳይ ሳይሆን ህዝቡ እናንተን አንፈልግም ነዉ። ህዝቡ የሚፈልገዉ ሰላም ነዉ።»

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ካሰራቸዉ በርካታ ወጣቶች 11 ሺሕ ባለፈዉ ሐሙስ በተለቀቁበት ወቅት፤ በሥፍራዉ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ቢሮ ሐላፊ አቶ አዎል አብዲ  እስረኞቹ  ወደ አካባቢያቸዉ ሲመለሱ፤ በግብርና፣ በማኑፋክቹሪንግ፣ በማዓድን፣ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ ስራ ለማስያዝ የክልሉ መንግስት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለወጣቶቹ ጥያቄ የስራ እድል ፈጠራዉ መልስ ይሁን ወይስ የአከባብያቸዉ ሰላም?  

 

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic