የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጣዊ መግለጫ | ኢትዮጵያ | DW | 17.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጣዊ መግለጫ

የመከላከያ ሚንሥትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 18 ንዑሣን አንቀጾች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ6 ወራት እንደሚዘልቅ ገልጠዋል። በርካታ ገደቦች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጠናቀቅ ከስድስት ወሩ በተጨማሪ ለአራት ወር እንደገና ሊራዘም ይችላል ተብሏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል እንደሚችልም ተገልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መግለጫ

የመከላከያ ሚንሥትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 18 ንዑሣን አንቀጾች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት እንደሚዘልቅ ገልጠዋል። በርካታ ገደቦች ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጠናቀቅ ከስድስት ወሩ በተጨማሪ ለአራት ወር እንደገና ሊራዘም ይችላል ተብሏል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣል እንደሚችልም ተገልጧል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር" የተደነገገው አዋጅ ለስድስት ወራት እንደሚዘልቅ አስታውቀዋል። በአዋጁ መሰረት "ይፋ ወይም የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀትና ማተም" አይቻልም።

አዋጁን የሚያስፈፅመው ኮማንድ ፖስት ርምጃ ይወስድባቸዋል ተብለው ከተዘረዘሩ ድርጊቶች መካከል "የአደባባይ ሰልፍና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት እንዲሁም በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስ" ይገኙበታል። ለአዋጅ አስፈጻሚው ''በሕገ መንግሥቱና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን የመራ፣ ያስተባበረ የጣሰ ወይም በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የተጠረጠረ ማንኛውንም ግለሰብ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ሥር" የማዋል ሥልጣንም ተሰጥቶታል።

ትናንት ምሽት በኢትዮጵያ ሚንስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ15 ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ የመከላከያ ሚንስትሩ ተናግረዋል። አቶ ሲራጅ የአገሪቱ የጸጥታ መዋቅር አካላት የመንግሥትን ውሳኔ እንዲያስፈፅሙ መታዘዛቸውን አክለው ገልጠዋል። የጸጥታ ኃይሎች አገሪቱን በሚያውኩ ላይ ርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን እና ለዳኝነት ልዩ ፍርድ ቤት መቋቋሙንም ገልጸዋል።

የአገሪቱ ጦር ኃይል የመንግሥቱን አስተዳደር እንደማይረከብ፣ የሽግግር መንግሥትም እንደማይቋቋም አቶ ሲራጅ ተናግረዋል። በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች "ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ የኹከት የብጥብጥ ተግባራት" መከሰታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለመደንገግ እንዳስገደዱ አቶ ሲራጅ ገልጸዋል።መግለጫውን ከስፍራው የተከታተለው ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር ቀጣዩን ዘገባ ከአዲስ አበባ ልኮልናል።

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic