የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የጋዜጦች ፈተና | አፍሪቃ | DW | 17.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የጋዜጦች ፈተና

“የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ይጥሳል” የሚል ትችትን እያስተናገደ የሚገኘው ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ተጽእኖው ከወዲሁ በግልጽ ከታየባቸው መስኮች መካከል የጋዜጠኝነት እና የመገናኛ ብዙሃን ስራ ይገኝበታል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:06 ደቂቃ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ

 በሳምንቱ መጨረሻ ለንባብ የሚበቁ ጋዜጣ እና መጽሄቶቻቸውን አሰናድተው ወደ ማተሚያ ቤት የሄዱ አሳታሚዎች ከግል ማተሚያ ቤቶች በተሰጣቸው የ“አናትምም” ምላሽ ምክንያት እትሞቻቸውን አንባቢዎቻቸው ዘንድ ሳያደርሱ ቀርተዋል፡፡

የግል ማተሚያ ቤቶቹ ጋዜጣ እና መጽሄቶችን ላለማተም የሚሰጡት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህትመት ውጤቶች ላይ ያስቀመጠውን ክልከላ እንደሆነ አሳታሚዎች ይናገራሉ፡፡ ከሳምንት በፊት ይፋ የተደረገው አዋጅ በደፈናው “የማይፈቀዱ ተግባራት” ሲል ከዘረዘራቸው ውስጥ “ሁከት እና ብጥብጥ የሚፈጥር ጽሁፍ ማዘጋጀት፣ ማተም እና ማሰራጨት” አንዱ ነው፡፡

የማተሚያ ቤት ኃላፊዎች ይህን የአዋጅ ክፍል ተተንተርሰው የህትመት አገልግሎት ሊሰጧቸው እንደማይችሉ እንዳሳወቋቸው የሳምንታዊው ኢትዮ- ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ይናገራሉ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከማተሚያ ቤት ስልክ ተደውሎ “አናትምም” መባላቸውን ለዶይቸ ቨለ ያስረዱት አቶ ጌታቸው ከዚያ በኋላ ከዚህ ቀደም በስራ ወደሚውቋቸው አራት ማተሚያ ቤቶች ሄደው ተመሳሳይ ምላሽ ማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ቀደም ሲል የቆንጆ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ባለቤት የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ “የሀበሻ ወግ” የሚል መጽሔት ለማሳተም ዝግጅታቸውን ጨርሰው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ካሳም ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ ቢሮ ተከራይተው፣ ሰራተኛ ቀጥረው፣ ለሶስት ወራት ህትመት የሚሆን የጽሑፍ መጠባበቂያ ዝግጅት አድርገው ወደ ህትመት ለመግባት ሲዘጋጁ የማተሚያ ቤት ችግር እንዳደቀናፋቸው ይገልጻሉ፡፡ በመጀመሪያ ከፍተኛ ዋጋ እንደተጠየቁ በስተኋላ ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት “ማተም አንችልም” እንደተባሉ ያብራራሉ፡፡

 “የሀበሻ ወግ” በፊት ገጹ ይዟቸው ከነበሩ ይዘቶች መካከል በማተሚያ ቤት ኃላፊዎቹ ያልተወደዱት ከኦሮሞ የፖለቲካ አቀንቃኝ አቶ ጃዋር መሐመድ ለሌላ የመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ቃለ ምልልስ ነው ። መጽሔቱ ይህንኑ ቃለ ምልልስ ምንጭ ጠቅሶ ሊያትም እንደነበረ አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ፡፡ በኢሬቻ በዓል አከባበር ወቅት ከደረሰው እልቂት እና ጉዳት ጋር በተያያዘ ከሟች ቤተሰቦች እና ወገኖች ጋር የተደረገ ቃለ መጠየቅ እና በባህር ዳር የመስቀል ደመራ በዓል ላይ አቡነ አብርሃም ባሰሙት ንግግር የደረሰባቸው ተግሳጽ በመጽሄቱ ፊት ለፊት ገጽ ተካትተው እንደነበር አክሎ ገልጿል፡፡

የማተሚያ ቤት ኃላፊዎች “የፖለቲካ ጽሁፎች ያስጠይቁናል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ጋዜጠኞች ይናገራሉ፡፡ ዶይቸ ቨለ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ የማተሚያ ቤትም ሆነ የመንግስት ኃላፊዎችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሁከት እና ብጥብጥ የሚያስነሳ የሚላቸውን መልዕክቶች በኢንተርኔት፣ በሞባይል፣ በጽሁፍ፣ በቴሌቪዝን፣ በሬድዮ አሊያም በማህበራዊ ሚዲያ መለዋወጥ የከለከለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የመለዋወጥ መብት እንደሚጥስ አየተተቸ ይገኛል፡፡ አቶ ጌታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን “አፋኝ” ሲሉ ይገልጹታል፡፡

የኢትዮ-ምህዳር ዋና አዘጋጅን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ ቴዎድሮስ በበኩላቸው በአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ ላይ የተጠቀሰው እና “እንደ ኢሳት እና ኦኤም ኤን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን ማሳየት፣ መከታተል እና ሪፖርት ማድረግ የተከለከለ ነው” የሚለው አንቀጽ እንዳስገረሟቸው ይገልጻሉ፡፡

የሁለቱን የጋዜጣ አዘጋጆች አስተያየት ሌሎች ጋዜጠኞች በተለያዩ መንገዶች ሲያሰተጋቡት ታይተዋል፡፡ እንደ ጸረ-ሽብር እና ፕሬስ ህግ ያሉ ማነቆዎች አሽመድመደውታል የሚባልለት የጋዜጠኝነት ሙያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ከድጡ ወደማጡ ይሸጋገራል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ አንዣብቧል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች