የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  የመብት ጥሰትን ያባብሳል መባሉ | ኢትዮጵያ | DW | 26.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  የመብት ጥሰትን ያባብሳል መባሉ

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚታየዉን አለመረጋጋት ያባብሳል ሲል ሂዉማን ራይትስ ወች አስታወቀ።  መንግስት የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል እስረኞችን መልቀቅ በጀመረ ማግስት አዋጁ መታወጁ በሀገሪቱ የታየዉን ተስፋ ሰጪ ሰላማዊ የለዉጥ እንቅስቃሴ የሚገታና መሰረታዊ የሰዉ ልጆች መብትን የሚጥስ  ነዉ ሲል ድርጅቱ በዘገባዉ አመልክቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

«አዋጁ ሰላማዊ የለዉጥ እንቅስቃሴን ይገድባል»

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቱ ባለፈዉ አርብ ባወጣዉ ዘገባ እንዳመለከተዉ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰዎች  ሀሳባቸዉን በነጻነት እንዳይገልጹ የሚገድብ ነዉ። 
በጎርጎሮሳዊዉ  2016 እስከ ነሀሴ 2017 ዓ/ም ታዉጆ በነበረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ 20 ሺህ በላይ ሰወች በጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉንና ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አስታዉሶ በአሁኑ ወቅት የወጣዉ አዋጅ የአፈጻጸም መመሪያም ቢሆን በህዝብ መብት ላይ ሰፊ ክልከላ የሚያደርግና ለመንግስት የጸጥታ አካላት ሰፊ የጥቃት መንገድ የሚከፍት ነዉ ብሎታል።
በዚህ ሁኔታ አዋጁ  በሀገሪቱ የተከሰተዉን አለመረጋጋት የሚያባብስና ከእስረኞች መፈታት ጋር ተያይዞ ሀገሪቱ ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ  ለዉጥ ትገባለች የሚለዉን ተስፋ ያቀጨጨ ነዉ ሲሉም የድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«እስረኞች  ሲፈቱ ብዙ ተስፋ ተጥሎ ነበር።እነዚህ የፖለቲካ እስረኖች እንዲፈቱ ሂዉማን ራይትስ ወችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።እናም መፈታታቸዉ በእርግጥም ጥሩ ነበር። ተስፋ ሰጭም ነበር ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለቀቁና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።ይህ የእስረኞቹ መፈታት የዋናዉ ለዉጥ መጀመሪያና  አንዱ አካል ነዉ የሚለዉን ተስፋ የሚያጠፋ ነዉ።»
እንደ ድርጅቱ ዘገባ አዋጁ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የወጡ የመሰብሰብ፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለፅና በህብረት የመንቀሳቀስ የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን  የሚጥስ ነዉ ። አዋጁ በቤት ዉስጥ የመቀመጥን፣ሱቅ የመዝጋትንና የመሳሰሉ ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴወችን የሚከለክልና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰወችን በቁጥጥር ስር ማዋልና መፈተሽን የሚፈቅድ በመሆኑም  በሀገሪቱ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ሰዎች አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ ይገድባል ሲል ድርጅቱ ተችቷል።
ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊዉ 1993 በአጸደቀችዉ በተቀበለችዉ የዓለም አቀፍ የሲቢል የሰላምና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ ስምምነት  መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት የተወሰኑ መብቶችን ብቻ ጊዜያዊ ክልከላ የሚያደርግ ቢሆንም ከህግ አግባብ ዉጭ መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ክልከላ ማድረግ ግን ከዓለም ዓቀፍ ከህጉ ጋር ይጣረሳል ሲል ድርጅቱ አመልክቷል። 

Human Rights Watch Logo


በአዋጁ የተካተቱ  ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ማድረግ ፤ ህገ መንግስቱን አጋ ላይ መጣልና መቻቻልንና አንድነትን የሚጎዱ ተግባራት መፈጸም የሚሉትና የመሳሰሉት ሀረጎችም ለትርጉም የተጋለጡና አሻሚ ናቸዉ ብሏል።የድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን እንደሚሉት አዋጁ በምክር ቤት ከመፅደቁ በፊት የሚመለከታቸዉ አካላት በተገቢ ሁኔታ ሊቃወሙት ይገባል ብለዋል።
«የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቀዉ በ15 ቀናት ዉስጥ ነዉ ብዬ አስባለሁ።ስለዚህ አሁን ሁኔታዎች እንደበፊቱ አይደሉም። የጥምር መንግስቱ አባላት ኦህዴድና ብአዴን ህዝብ በአደባባይ የሚገልጸዉን የለዉጥ ፍላጎት አቅጣጫ እንደሚያስይዙ ለማሳየት ለእነርሱ አስፈላጊ ጊዜ ይመስለኛል።እናም አዋጁ አላስፈላጊና ሀገሪቱን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የሚወስድ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑ ይቃወሙታል ብዬ አስባለሁ።»
የአዋጁን  ዝርዝር አፈጻጸም መመሪያ በተመለከተ ኢትዮጵያ የሚገኜዉ የአሜሪካ ኢምባሲ ያወጣዉን መግለጫም ተገቢ ጠንካራና ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሩ መልዕክት ያስተላለፈ ነዉ ሲሉ  ተመራማሪዉ ገልጸዋል። 
«አዋጁን በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት ያወጣዉ መግለጫ ጠንካራና ጥሩ ነዉ።ኢትዮጵያ ተጨማሪ ዉይይቶችና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስፈልጋት ሀገር መሆኗ የታወቀ ነገር ነዉ።ነገር ግን የአሜሪካ ኢምባሲን መግለጫ የተለዬ ያደረገዉ ባለፉት 3 ዓመታት በሀገሪቱ አለመረጋጋትና ተቃዉሞ እየጨመረ ቢመጣም  የሀገሪቱ አጋር የሆኑት የምዕራብ መንግስታት በአደባባይ መተቸተን ችላ ብለዉ ነዉ የቆዩት።እንደማስበዉ መግለጫዉ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሩ መልክት ያስተላለፈ በመሆኑ ጥሩ ነዉ።» 
ካሉ በኋላ  ሌሎች መንግስታትም አዋጁን በመቃወም ድምጻቸዉን ሊያሰሙ እንደሚገባ ተመራማሪዉ አስምረዉበታል።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic