የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላዎች እና እስር | ኢትዮጵያ | DW | 09.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላዎች እና እስር

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ሁለት ወር ሊደፍን ነው፡፡ ስድስት ወር እንደሚቆይ የተደነገገው አዋጅ በቶሎ እንዲነሳ ከተለያዩ ወገኖች ግፊት እንደቀጠለ ነው፡፡ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል በየቦታው ታስረው የሚገኙ ተርጣሪዎች በበኩላቸው አላግባብ ለእስር መዳረጋቸውን እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በግልጽ መረዳት እንደተሳናቸው ይናገራሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:40

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላዎች እና እስር

ኢትዮጵያ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን አሰናብታ ዶ/ር አብይ አህመድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተቀበለች ዛሬ አንድ ሳምንት ተቆጠረ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከገዢው ፓርቲ የተለመደ ይትባህል ወጣ ባለ መልኩ ያቀረቡት ንግግር ብዙዎች ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል፡፡ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቶሎ ማሻሻያዎችን እንዲተገብሩ የሚጠይቁ ደጋግመው የሚያነሱት አንድ ጉዳይ አለ - የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፡፡ ባለፈው የካቲት ወር የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ ለስድስት ወር እንደሚቆይ ቢቀመጥም ጠያቂዎቹ ግን አሁኑኑ ይነሳ ባይ ናቸው፡፡ 

ይህንን አቋማቸው በይፋ ካሳወቁት መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ሁነኛ አጋር የሚባሉት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ይገኙበታል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመታቸው በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀላቸው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ መግለጫ ያወጣው ተቀማጭነቱን በአዲስ አበባ ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ “ከእንኳን ደስ አልዎ” መልዕከቱ ጎን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፍጥነት ይነሳል ብሎ እንደሚጠብቅ አሳውቋል፡፡ የአሜሪካንን ፈለግ የተከተለ የሚመስለው የአውሮፓ ህብረትም አዋጁ በቶሎ እንዲነሳ ፍላጎቱን ገልጿል፡፡ 

እንደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሁሉ አዋጁ እንደሚያሳስባቸው ሲናገሩ የቆዩ ሀገራት እና ተቋማት ድንጋጌው የዜጎችን መሰረታዊ እና የሰብዓዊ መብቶችን ለመጣስ እንዳይውል ስጋታቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል በሚል በእስር ቆይተው የተለቀቁ ተርጣሪዎች የሚሰጡት የዓይን እማኝነት ግን ሀገራቱ እና ተቋማቱ የሰጉበት የመብት ጥሰት እየተተገበረ መሆኑን ያሳያል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለ12 ቀናት ያህል ታስሮ ባለፈው ሳምንት ተለቅቋል፡፡ ተመስገን ለዓመታት ታስረው የተፈቱ እስረኞችን ለማመስገን በተዘጋጀ መርኃ ግብር ላይ እያለ ነበር ከሌሎች 10 ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ አራማጆች (አክቲቪስቶች) እና ፖለቲከኞች ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡ በእስር በቆየበት የፖሊስ መምሪያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል በሚል ወደ 80 ገደማ ተጠርጣሪዎች ታስረው መመልከቱን ይናገራል፡፡ አብዛኞቹ የተከሰሱበትን ጉዳይ ግን እንኳ በቅጡ እንደማያውቁ እና ሲያዙም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እንደነገሩት ይገልጻል፡፡ ስለእስረኞች ማንነት በማስረዳት ይጀምራል፡፡

“የፉሪ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አየለ ደበላ እና የፉሪ የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊ አለ፡፡ ከዚያ በተረፈ ሌሎቹ በሙሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ዕድሜያቸውም በግምት አብዛኞቹ ከ30 ዓመት በታች ናቸው፡፡ አንድ ሽማግሌ አሉ፡፡ የፖሊስ መኪና ሲያልፍ ፎቶ አንስተሃል ተብለው የመጡ፡፡ አብዛኞቹ የመጡት ከአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አማረ የሚባል መካኒሳ ጋር የተያዘ ፌስ ቡኩን እያየ የኮሎኔል ደመቀን ፎቶ አጋርተሃል ተብሎ ነው የመጣው፡፡ በሙሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተይዘው እኛ የነበርንበት ፖሊስ ጣቢያ ያሉ ከቤታቸው፣ ከስራ ቦታቸው እና ከመንገድ ላይ የተያዙ ናቸው፡፡ እነርሱ አሁን ከእኛ የተለየ የሚያደርጋቸው ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል በተያዙበት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ቀን ላይ፡፡ ምንድነው እያሏቸው ያሉት? አሁን ሲያዩን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በአመጽ ወቅት ላይ ተሳትፎ ነበራችሁ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መጀመሪያም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ቅሬታ እና ተቃውሞ ሲያነሱ እንደበረው ለበቀል ተግባር ሊውል ይችላል፣ ላልተፈለገ ትርጉም ሊጋለጥ ይችላል የተባለው እየሆነ ነው ያለው” ይላል ጋዜጠኛ ተመስገን።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 578 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባህር ዳርም ተርጣሪዎች የተያዙበት ሁኔታ ተመሳሳይ እንደሆነ የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ እንደ እነተመስገን ሁሉ ከ18 ጓደኞቻቸው ጋራ ተሰባስበው የግል ምክክር እያደረጉ ባሉበት በጣና ሀይቅ ዳርቻ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለ12 ቀናት በእስር ቆይተዋል፡፡ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲው መምህር እና ጓደኞቻቸው በቆዩበት ፖሊስ ጣቢያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ ቁጥራቸው ወደ 50 የሚጠጉ ሰዎች እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ፡፡  

“እኛ ታስረንበት የነበረው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ይባላል፡፡ ባህር ዳር ከነማ ከደሴ ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ዕለት ረብሻ ፈጥራችኋል ተብለው ተይዘው የነበሩ ወደ 12 ወይም 13 ልጆች ነበሩ፡፡ በተጨማሪ ባህር ዳር ዙሪያ ያለ ሰማሰሚት ከተባለ አካባቢ እርሻ መሬታችሁ ላይ የኮማንድ ፖስት ፍቃድ ሳይኖረው ቤት ገንብታችኋል ተብለው የታሰሩ አርሶ አደሮች አስታውስ ነበር፡፡ እንዲዚህ አይነት በትንንሽ ጉዳዩች፣ ጽሁፍ በኪሳችሁ ይዛችሁ ስቴድየም ተገኝታችኋል ተብሎ የታሰሩ ልጆች ነበሩ፡፡ እንደዚህ አይነት ልጆች ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ብዙ እስረኛ ነው የነበረው፡፡ በተወሰነ ደረጃ እኛ ጋርም ቢሆን መደናገር ነበር፡፡ መጀመሪያ ማን እንደያዘን አልገባንም ነበር፤ እነርሱም እንዲሁ፡፡ ለምሳሌ ከኳስ ጋር ተያይዞ ተይዘው የነበሩ ልጆችም ‘በግልጽ  መጥቶ የሚያናገርን፣ ከኮማንድ ፖስቱ ነን፣ እንደዚህ ነን ብሎ መረጃ የሚሰጠን’ [የለም ሲሉ ነበር]፡፡ የተያዘክበትን ምክንያት እንኳ በትክክል አብራርቶ የሚያሳውቅህ ሰው ስላልነበረ ብዙ ሰው የተያዘበትን ምክንያት እንኳ በደንብ አልገባውም ነበር” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ ያስረዳሉ።

ዶ/ር ደሳለኝ አብረዋቸው ከታሰሩ ጓደኞቻቸው መካከል ሁለት የህግ ባለሙያዎች የነበሩ ቢሆንም የትኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ ተላልፈው እንደተያዙ ለመረዳት ተቸግረው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ አዋጁ የአደባባይ ስብሰባዎች እና ሰልፎች እንደሚከለክል እንደሚያውቁ ነገር ግን እነርሱ እንዳደረጉት መደበኛ ያልሆነ ውይይት ወይም ማህበራዊ ግንኙነት የሚያግድ መስሎ አልተሰማንም ነበር ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አዋጁ በግልጽ ክልከላዎችን አለማስቀመጡን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ በመላው ሀገሪቱ የሚተገብሩ ብሎ 16 ክልከላዎችን የዘረዘረ ሲሆን ለተወሰኑ ቦታዎች ደግሞ አራት ክልከላዎችን አስቀምጧል፡፡ አዋጁን እና መመሪያውን የፈተሹ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ክልከላዎቹ አሻሚ ትርጉም ያላቸው እና ግልጽነት የሚጎድላቸው ናቸው ሲሉ ይተቻሉ፡፡“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጣም ውስን ጉዳዮችን የሚይዝ” መሆኑን የሚያስረዱት የሰብዓዊ መብቶች ህግ ባለሙያው አቶ ዩሴፍ ሙሉጌታ “ሊከለክላቸው ያሰባቸውን ጉዳዮች በሚመለከትም በጣም ግልጽ መሆን አለበት” ይላሉ፡፡

“መመሪያ ተብሎ የወጣውን የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ስታየው ህግ በሚያረቅቁ ሰዎች ተጽፏል ብሎ ለመናገር በጣም ነው የሚያሳፍረው፡፡ ምክንያቱም ለማድረግ የታሰበ የሚመስለው፣ ያንን ረቂቅ የጻፈው ሰው ቁጭ ብሎ ሊከለክል ያሰባቸውን ነገሮች በሙሉ እንዳለ ጭንቅላቱ ውስጥ አስቀምጦ፣ ከዚያ እነርሱን ወደ ወረቀት ማስፈር [ነው]፡፡ ስለ አመክኖያዊ ትስስራቸው፣ መሬት ላይ ሲተገበሩ ስለሚያመጡት ውጤት፣ ምን ያህል ተጨባጭ ናቸው? ምን ያህል ከሰው እና ከማህበረሰብ የቀን ተቀን መስተጋብር ጋር አብረው ይሄዳሉ ስለሚለው ጉዳይ ብዙም ትኩረት የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ለህግ፣ ደንቦች አረቃቀቅ ምንም ክብር በሌለው ሁኔታ የተረቀቀ አይነት ነው፡፡ 

በአለም ላይ ያሉ ክልከላዎች አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት ብሎ አስፍሮ ከዚያ ማንም ሰው እንዳይነቃነቅ ለማድረግ ከመመኘት የመጣ ነው እንጂ የሰከነ፣ ባለሙያዎች ቁጭ ብለው ስለ ቋንቋው እና ቋንቋው ስለሚኖረው እንድምታ ያረቀቁት አይነት ደንብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለእዚያ ነው ትርጉምም ሳያስፈልግ ዝም ብለህ ተግባራዊ ስታደረገው ሁሉንም አይነት፣ ይሆናሉ ብለህ ልታስባቸው የምትችል፣ ከሁለት በላይ ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚችሉ መስተጋብሮችን፣ ከተቻለ የሰዎችን አስተሳሰብ ሳንሱር የማድረግ ፍላጎት ያለው አይነት፣ ግራ የሚያጋባ አረቃቅ ነው” ሲሉ የህግ ባለሙያው የሰላ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ። 

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑ አንድ የህግ ባለሙያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንዳንድ ገደቦች የሚያሻሙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ምን ማድረግ እንዳለበት እና እንደሌለበት በቅጡ እንዳያውቅ እንዳደረጉት ይናገራሉ፡፡ ለአስፈጻሚው አካልም እንዳሻው ክልከላዎችን እንዲፈጽም እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡ 

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ያሉ ድንጋጌዎች በስፋት የተቀመጡ እና አሻሚዎች የሆኑ ናቸው፡፡ እና የኮማንድ ፖስቱን ስልጣን በቅጡ መገደብ ያልቻሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል የታሰሩ ሰዎች የሚያወራው ድንጋጌ ላይ ወይ በምክር ይወጣሉ፣ ወይ ለፍርድ ይቀርባሉ፣ ወይ ደግሞ እንደዚህ ስልጠና ይሰጣቸዋል ይልና ለዚህ በተለይ መስፍርት ይወጣል ቢልም መስፈርቱ ግን እስካሁን ድረስ አልወጣም፡፡ ምርመራ ለምን ያህል ጊዜ ያህል ይካሄዳል የሚሉት እንደዚሁ የሉም፡፡ ሌላ እዚያ ላይ የተደነገጉትን ራሱ ተላልፎ ለተገኘ ሰው አግባብነት ያለው እርምጃዎች ይወሰዳሉ በሚል ሰፋ ያለ ድንጋጌ ኮማንድ ፖስቱ እንደ ልቡ እርምጃዎችን እንዲወስድ እድሉን የሚሰጡ አንቀጾች አሉ” ሲሉ የህግ መምህሩ ያብራራሉ።

ጋዜጠኛ ተመስገንም ሆነ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ደሳለኝ ያነጋገሯቸው እስረኞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል በሚል ቢታሰሩም የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን የሚነግራቸው አካል አጥተዋል፡፡ ታሳሪዎቹ አላግባብ መታሰራቸውን የት አቤት ማለት እንደሚችሉ ለማወቅ ተቸግረዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱ እንደዚህ አይነት እርምጃዎችን የመከታተል እና የመቆጣጠር ተግባር ያለው መርማሪ ቦርድ ግን ስራየን እያከናወነንኩ ነው ይላል። መርማሪ ቦርዱ በአዋጁ የሚወሰዱ እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊ መሆናቸውን ካመነ እርምጃውን እንዲያስተካክል ለኮማንድ ፖስቱ ሀሳብ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ 

ቦርዱ ከተሰጠው ስልጣን እና ተግባር አንዱ በአዋጁ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦችን እና የታሰሩበትን ምክንያት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ኮማንድ ፖስቱ ኮማንድ ፖስቱ በሁከት እና ብጥብጥ የጠረጠራቸውን 1‚107 ሰዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉን አሳውቀው ነበር፡፡ አራማጆች (አክቲቪስቶች) ግን በየአካባቢው የታሰሩ ሰዎች በቦርዱ ከተጠቀሰው በጣሙኑ እንደሚልቅ ይሟገታሉ። የቦርዱ ሰብሳቢ በባለፈው ሳምንት መግለጫቸው ከህብረተሰቡ ከሚደርሷቸው ጥቆማዎች ብዙዎቹ “ሰዎች እየታሰሩ ያሉት በቂም በቀል ነው” የሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡  

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያውጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ታውጆ የነበረው ተመሳሳይ ድንጋጌ ለ10 ወር ከቆየ በኋላ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት በየካቲት 9 የታወጀው የአሁኑ ድንጋጌ “ሕገ መንግስቱን እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል” በሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ አዋጁን ማውጣት ያስፈለገውም “በሕገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ በመደረሱ” እንደሆነም ተገልጾ ነበር፡፡ 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል ታስረው የተለቀቁትም ይሁን የህግ ባለሙያዎቹ መሰረታዊ መብቶችን ይጋፋል በሚል የሚወቀሰው ድንጋጌ ከቀነ ገደቡ በፊት እንዲነሳ ይሻሉ። የአምቦው ዩኒቨርስቲ መምህር ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም” ባይ ናቸው። መቀመጫቸውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት የሰብዓዊ መብቶች ህግ ባለሙያው አቶ ዩሴፍ ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic