የአስቸኳይ አዋጁና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳሰብያ | ኢትዮጵያ | DW | 19.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአስቸኳይ አዋጁና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማሳሰብያ

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤በጋዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ መንግስት በሐገሪቱ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች አወገዙ። ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቡን ጥያቄ ስለመመለሱ ጥርጣሪ እንዳለዉ ገልፆአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:39

የአስቸኳይ አዋጁ የህዝቡን ጥያቄ አይመልስም።


የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን የተቃወመው የሐገሪቱ  የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይበልጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ወድቋል የሚለው «ጌዜልሻፍት ፍዩር በድሮተ ፎልከር» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የጀርመናውያኑ የውሁዳን ሕዝቦች መብት ተሟጋች ድርጅት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ ጥሪዉን አቅርቧል። 
ባለፈው አርብ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ኮማንድ ፖስቱ የሚያወጣው መመርያ ዝርዝር በጃችን ባይኖርም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ለሕዝቡ ጥያቄ መልስ ሊሆን አይችልም ሲል የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዉ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልፆአል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ እንደገለፁት አዋጁ ሐገሪቱ ቀዉስ ዉስጥ እንዳለች አመላካች ነዉ። 
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብዓዊ መብት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ያለበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል ያሉት አቶ ፍስሃ ተክሌ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ይገልፃል ብለዋል።
መንግሥት እፈታለሁ ባለዉ መሰረት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አንዷአለም አራጌን ጨምሮ  በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታት በጀመረ ማግሥት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈዉ ሳምንት ኃሙስ  ከስልጣን መልቀቃቸዉ እምብዛም ያልተጠበቀ አልሆነም። በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አለመረጋጋት እና የፖለቲካ ችግር ለማስወገድ የሚወሰደው ርምጃ መፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ ስልጣናቸዉን በገዛ ፈቃዳቸዉ መልቀቃቸዉን  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባስታወቁ ማግሥት በሃገሪቱ ብልጭ ያለዉ የዴሞክራሲ ጀንበር በተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅ መጨለሞ አሳስቦናል ሲል በሳምንቱ መጨረሻ  «ጌዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የጀርመናውያኑ የውሁዳን ሕዝቦች መብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ ያስታወቁት።
«በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች ይመስለኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣናቸዉ በገዛ ፈቃዳቸዉ እንደለቀቁ ፤ በሐገሪቱ ዴሞክራሲ ይሰፍናል የፖለቲካ ታኅድሶ ይጀምራል የሚል ትልቅ ተስፋን ሰንቀን ነበር። ይህ ተስፋ ግን አንድ ቀን ያህል አንኳ አልዘለቀም አርብ ምሽት በጠቅላላ ሐገሪቱ ተግባራዊ ሆንና የመሰብሰብ መብትን የሚነፍግ ዴሞክራሲና የንግግር ነፃነትን የሚገድብ፤  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ሰማን። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይበልጥ መጨመሩን እያየን ነዉ ። በዚህ በታወጀዉ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ለዉጡ አዲስ የሚያመጣዉ ነገር አለ ብለን አንጠብቅም። » 
የመንግሥት ለዉጡ የሚፈይደዉ ነገር የለም፤ ይልቅየም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድን

ገት የሚፈነዳን የነፃነት ጩኸትን ለጊዜዉ አዳፍኖ ማቆየት ያስችል ይሆናል ያሉት ጀርመናዊዉ ዴልዩስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብሎም የአዉሮጳ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫናን ሊያሳርፍ ይገባል። 
« የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ማሳረፍ ይኖርበታል ብለን እናምናለን። ይህ ዋናዉና አስፈላጊ ነገር ነዉ። በሳምንቱ መጨረሻ የአሜሪካ ኤምባሲ ተቃዉሞዉን እንዳሰማ ሁሉ ይህንኑ በተመለከተ የአዉሮጳ ኅብረትም ግልፅና ጠንካራ አቋሙን መግለፅና ማሳየት ይኖርበታል። ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የተስፋ ጭላንጭል ሲታይ እዚያ ላይ ብቻ መልስ መስጠቱ በቂ አይሆንም። ለምሳሌ ባለፈዉ ሳምንት እስረኞች ሲለቀቁ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስልክ መደዉላቸዉ ብቻ በቂ አይሆንም። እየሆነ ላለዉ ነገርም ፈጣን፤ ቀጥተኛ እና ግልጽ የሆነ ምላሽ መስጠትም ያስፈልጋል። በሐገሪቱ አዎንታዊ ነገሮች ሲታዩ ብቻ ሳይሆን ምላሽን መስጠት ያለበት ፤  እየታየ ያለዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተም የአዉሮጳ ኅብረት ነገሮች እንዲሻሻሉ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።»    

የአውሮጳ ኅብረት ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ በኢትዮጵያ የሚታየዉን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ብቸኛው መፍትሄ በሁሉም አከላት መካከል የሚደረግ ውይይት ነው ሲል ገልፆአል።  ባለፈዉ አርብ ዳግም የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን ይህን ለማድረግ እንቅፋት ይሆናል ብሏል፡፡

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሠ