የአሮጌ አልባሳት ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 02.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአሮጌ አልባሳት ንግድ

በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም በረድዔት ስም የሚሰበሰቡ ወይም በዜጎች ልገሣ የሚገኙ አሮጌ አልባሳት በታዳጊ ሃገራት ለድሆች በነጻ የሚታደሉ የሚመስላቸው እስከ ቅርብ ድረስ ጥቂቶች አልነበሩም።

default

ኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም በረድዔት ስም የሚሰበሰቡ ወይም በዜጎች ልገሣ የሚገኙ አሮጌ አልባሳት በታዳጊ ሃገራት ለድሆች በነጻ የሚታደሉ የሚመስላቸው እስከ ቅርብ ድረስ ጥቂቶች አልነበሩም። እርግጥ ሃቁ ይህ አይደለም። ሃቁ በኪሎ እየተመዘኑ ለሽያጭ ገበዮች ላይ መቅረባቸው ነው። የአንዳንድ የዕርዳታ ድርጅቶች፤ ለምሳሌ የቀይ መስቀልማሕበር መለያ በመንገድ በሚቀመጡ የአሮጌ ልብስ ሰብሳቢ ኩባንያዎች ማከማቻዎች ላይ እንዲለጠፍ ከመደረጉ በስተቀር እነዚህ ንግዱን በቀጥታ አያካሂዱም።

ንግዱ ቀላል የማይባል ሲሆን አብዛኛው ከሕዝብ የተሰበሰበ አልባሳት የሚቸበቸበውም አፍሪቃ ውስጥ ነው። ባለፈው ዓመት በዚህ በጀርምን የተሰበሰበው የአሮጌ አላባሳት ክምችት 700 ሺህ ቶን ይጠጋ ነበር። ታዲያ እነዚህ አሮጌ አልባሳት ርካሽ በመሆናቸው አገሬውን የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ክስረት ላይ አይጥሉም ወይ? በመጨረሻ ይበልጥ ተጎጂውስ የድሃ ድሃው አይደለም ወይ? ይህ ዛሬ በጉዳዩ ያተኮሩ ታዛቢዎችን ጭምር ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

በዚህ በጀርመን በሕዝብ የሚለገሰው የአሮጌ አልባሳት ክምችት መጠን በጎ አድራጎት ድርጅቶች በአገሪቱ ለሚያካሂዱት ማሕበራዊ ተግባር ከሚያስፈልጋቸው በጣሙን ይበልጣል። ይሄም ነው ለአሮጌው ልብስ ንግድ ዋና ምክንያት የሆነው። ቀይ መስቀልን የመሳሰሉት የረድዔት ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ አሮጌ አልባሳቱን የሚሰበስቡት ራሳቸው አይደሉም። ሆኖም ሰብሳቢ ድርጅቶች ስማቸውን እንዲጠቀሙ ያደርጋሉ። የእነዚህ ዓላማ ደግሞ ንግድ ነው። ሻል ያለው ዕቃ ወደ ምሥራቅ አውሮፓና ወደ ሩሢያ ሲላክ ዝቅተኛው በተለይም ለአፍሪቃ የተመደበ ነው።

የተሰበሰበው አልባሳት በተመደበለት ማከማቻ ስፍራ በመጀመሪያ እንደ ጥራቱ መጠንና እንደ አስፈላጊነቱ፤ ማለት በጥሬ ዕቃነት ወይም በአሮጌ ልብስነት በመልክ በመልኩ እንዲለይ ከተደረገ በኋላ ለሽያጭ ይቀርባል። አልባሳቱን መሰብሰቡ፣ በዓይነት መለያየቱና ከቦታ ቦታ ማጓጓዙ ወጪን እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር በመሠረቱ ለሽያጭ መቅረቡ የከፋ ነገር ሆኖ አይታይም። ሆኖም ይህን የሚሉት የጀርመን የአብያተ-ክርስቲያን ማሕበራት ጣራ ድርጅት የፌየር ቬርቱንግ ስራ አስኪያጅ አንድሬያስ ፎገት በሌላ በኩል በአለባሳት ስብሰባው ረገድ ግልጽ አሠራርና ሃላፊነት እንዲኖር አጥብቀው ያሳስባሉ።

«ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለአሮጌ ልብሶች መክፈል ይፈልጋሉ። ይህ በአፍሪቃም የክብር ጉዳይ ነው። ከተለያዩ ሸሪኮቻችን፤ የአብያተ-ክርስቲያን የሆኑትን ጨምሮ አዘውትረን የምንሰማው ሰዎች ጥራት ያለውን ዕቃ ፍትሃዊ በሚሆን ዋጋ መግዛት የሚፈልጉ መሆናቸውን ነው። ልብስ በነጻ እንዲሰጠው የሚጠይቅ የለም»

የዋጋው አመቺነት፣ ጥራትና የምርጫው ብዛት ናቸው በአፍሪቃ ሃገራት ሰው ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ የገቡ አሮጌ አልባሳትን እንዲገዛ ምክንያት የሚሆኑት። በአንጻሩ በአገር ውስጥ የተመረተው ጨርቃ-ጨርቅም ሆነ ከቻይና የሚገባው የአልባሳት ምርት ከዚህ ለመፎካከር አይችሉም። በብዙዎች የአፍሪቃ ሃገራት ሕዝብ ከሚያስፈልገው አልባሳት ከ 60 እስከ 80 በመቶ የሆነውን ድርሻ አሮጌው እንደሚይዝ ነው የሚገመተው። አንድሬያስ ፎገት እንደሚሉት በዚሁ በተለይ ጥቂት ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ሁኔታ መሻሻሉ በግልጽ ያታያል።

«በዓለምአቀፍ ደረጃ የአሮጌ ወይም የሰከንድ-ሃንድ አልባሳት ፍላጎት፤ ከድህነት የተነሣ እያደገ በመሄድ ላይ ነው። እንግዲህ ጥቅም ላይ የዋለ ልብስ እንዲህ በሰፊው ለመፈለጉ ዋናው ምክንያት የብዙ ሕዝብ የገቢ ዝቅተኝነትና የመግዛት አቅም ደካማነት ነው»

በሌላ በኩል ግን አሮጌ አልባሳትን የሚገዙት ድሆች ብቻ ይሁኑ ወይም የመካከለኛው የሕብረተሰብ መደብ ዓባላትም ጭምር ጉዳዩ ብዙ ያነጋግራል። ብዙዎች የታዳጊው ዓለም ታዛቢዎች ታዲያ ወደነዚህ ሃገራት እንዲገቡ የሚደረጉ አሮጌ አልባሳት በአፍሪቃ የውስጡ የጨርቃ-ጨርቅ ምርት ለመዳከሙ ዓቢይ መንስዔ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። በዚህ በጀርመን ዙድ-ቪንድ የተሰኘው ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ባልደርባ ፍሪድል-ሁትስ-አዳምስ እንደሚሉትም አሮጌ አልባሳትን ማስገባቱ ጎጂ ተጽዕኖ አለው።

«በብዙ ሃገራት በ 1980 እና 90ኛዎቹ ዓመታት ይታይ የነበረው የውስጡ ጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ውድቀት የደረሰው ግማሽ በግማሽ አሮጌ አልባሳትን በማስገባቱ የተነሣ እንደነበር አንድ በጉዳዩ የተካሄደ ጥናት አመልክቷል። ለተቀረው አጋማሽ ደግሞ ደካማ የአመራረት ዘይቤ፣ የጥሬና መቀያየሪያ እቃዎች አቅርቦት ድክመት ወይም የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ምክንያቶቹ ነበሩ። አስገራሚው ነገር ግን አሮጌ አልባሳት ለአፍሪቃ የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ክስረት መንስዔ እስከመሆን መድረሳቸው ነው። ለነገሩ የተለገሱት ድሆችን ለመርዳት ነውና»

ሁትስ-አዳምስ አክለው እንደሚያስረዱት በአገሬው ኢንዱስትሪ ማቆልቆል ደግሞ የአፍሪቃ መንግሥታት የልማት ዕርምጃቸውን እንዲያጡ ማድረጉ አልቀሩም። በዚሁ የተነሣም ናይጄሪያና ሌሎች መሰል የአፍሪቃ ሃገራት አሮጌው ምርት ወደ አገር እንዳይገባ አግደዋል፤ ወይም ገደብ ለማድረግ እየተወያዩ ነው።

«ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃና ኢትዮጵያ በጥሩ ምክንያት አሮጌ አላባሳት ወደ አገር መግባቱን አግደዋል። ጋና፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳም እንዲሁ በቀረጥና በግብር የዕቃውን መግባት ለመገደብ ለማቅማማታቸው ጥሩ ምክንያት አላቸው። የውስጡን ኢንዱስትሪ ዘላቂነት ባለው መልክ መልሰው ለማነጽ ይፈልጋሉ»

ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ደግሞ በአሮጌው አላባሳት ንግድ ላይ አንዳች ዕርምጃ አልወሰዱም። እንደነዚሁ ወደ አፍሪቃ ሃገራት የሚደረገውን የጨርቃ-ጨርቅ ምርት ማስገባት በዚህ መልክ የሚመለከቱ ታዛቢዎች በዚህ በጀርመንም አሉ።

«አሮጌው አላባሳት ባይኖሩ ምርቱን በሚያስገቡ የአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሊያብብ ይችል እንደነበር የማስመሰል ሁኔታ አለ። ይህ ከተጨባጩ ሁኔታ ጨርሶ የራቀ ተረት ነው። የሚያስገርም ሆኖ በዚህ በጀርመን አሮጌውን አላባሳት አስመልክቶ ንግዱን በመደገፍ ወይም በመቃወም የሚካሄደው ክርክር በአብዛኞቹ ምርቱን በሚያስገቡት የአፍሪቃ ሃገራት ጨርሶ አይሰማም። በቀላሉ የሚጠቀሰው ጥቂት ገንዘብ ላላቸው ሰዎች አሮጌው ልብስ ርካሹ አማራጭ እንደሆነ ነው። ለዚህም ነው አቅራቢዎቹ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከአሢያ ነጋዴዎች ልብሱን እየገዙ ወደ አፍሪቃ የሚያስገቡት»

ፎገት የአሮጌ አልባሳቱን ንግድ በከፊልም ቢሆን ዛሬም ካለው ከአገሬው ምርት ይዞታ አንጻር አማራጭ እንደሆነ አድርገው ይመለከታሉ። እነዚህ አፍሪቃዊ አምራቾች በበኩላቸው የመግዛት አቅም ባላቸው ደምበኞች ላይ ያተኮሩ ሲሆን ምርቶቻቸውን ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካም የሚልኩ ናቸው።

Altkleider in der Kleiderkammer

የጀርመን መንግሥትም አሮጌ አልባሳት ወደ ታዳጊ አገሮች እንዳይላኩ መደረጉን አይቀበልም። ይሄው ለውስጣዊው የጨርቃ-ጨርቅ ምርት ማቆልቆል ከፊል ምክንያት ብቻ መሆኑን ያመለክታል። ከዚሁ ሌላም የኤኮኖሚና የንግድ ፖሊሲ ችግሮች ለአዳጊው ሃገራት የምርት ማቆልቆል መንስዔ መሆናቸውን ነው የሚናገረው። በዝርዝሩ ደካማ ሁለንተናዊ የኤኮኖሚ ይዞታ፣ የፋብሪካዎች ምርታማነት ዝቅተኛ መሆንና መንግሥት በግል ዘርፍ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ፤ እንዲሁም የጨርቃ-ጨርቅ ጥሬ ዕቃ ዋጋ በከፍተኛ ቀረጥ የተነሣ ካለቁ ምርቶች እንዲወደድ በማድረግ በሚፈጠር ሁኔታ የፉክክር ዕድልን የማዛባት ችግሮቹ ናቸው።

በሌላ በኩል በውስጣዊው የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ መውደቅ የሥራ ቦታዎች መዘጋት ብቻ ሣይሆን ወደ ሌላ መሸጋሸጋቸውም አንድ ሃቅ ነው። ብዙ አሮጌ አልባሳት ለአፍሪቃውያን ለአፍሪቃዊው ቁመና ጎላ ያሉ ሲሆኑ ተስተካክለው መሰፋት ስለሚኖርባቸው በዚሁ የሥራ መስክ መከፈቱም አልቀረም። የአሮጌው አልባሳት ንግድ እንግዲህ በብዙዎቹ አዳጊ ሃገራት ጠቃሚ የኤኮኖሚ ዘርፍና የሥራ ገበያ ምንጭም ሆኗል ሊባል ይችላል።

ግን ጥያቄው በዚህ ንግድ የሚገኘው ገንዘብ በአልባሳቱ ልገሣ እንዲጠቀሙ ለታሰበው ሰዎች ይደርሳል ወይ ነው። የአልባሳቱ ንግድ ለብዙ አትራፊዎች አጓጊ የገቢ ምንጭ እየሆነ መሄዱ አልቀረም። ጀርመን ውስጥ ባለፈው ዓመት የአንድ ቶን አሮጌ ልብስ ዋጋ በአማካይ 300 ኤውሮ ደርሶ ታይቷል። አብዛኛውን ጊዜ ከጀርመን ውጭ በሚደረገው ጊዜ የሚፈጅ ልብሱን ለያይቶ የማከማቸት ሥራ ደግሞ ዋጋው እንደገና የሚጨምር መሆኑ ግልጽ ነው።

«ወደ አፍሪቃ ገበዮች ዕቃውን መላኩ እንደ ጥራቱና እንደሚገባበት አገር ሁኔታ እንዲያውም በቶን እስከ 1000 ወይም ደግሞ እስከ 1500 ኤውሮ ያወጣል። ገንዘቡም በከፊል የሚቀረው ንግዱን እዚህና እስከ አፍሪቃ ድረስ በሚያካሂዱት የጀርመን ድርጅቶች ዕጅ ነው። በአሮጌው አልባሳት የሚነግዱ ወገኖች ሲካብቱ ይታያል። እንግዲህ ገንዘቡ ለጋሾቹ እንዳሰቡት ለድሃው አይደለም የሚደርሰው። ማንም ካልጠበቃቸው ነጋዴዎች ዕጅ ይገባል እንጂ»

በዚህ በጀርመን የመስኩ ታዛቢዎች የሚስማሙበት አንድ ሃሳብ አለ። ይሄውም በየቦታው በሕግ-ወጥ መንግድ ከሚቆሙት የዕርዳታ አልባሳት ማከማቻዎች ባሻገር አሮጌ ልብሶችን በመሰብሰቡ ረገድ ያለው የግልጽነት ጉድለት መወገድ የሚኖርበት ትልቅ ችግር ነው። የጀርመን ለጋሽም ቢሆን ባበረከታቸው አልባሳት ንግድ እንደሚካሄድ መረጃ ሊቀርብለት ይገባል። በስሙ ዕርዳታው የሚሰበሰብበት የታዳጊው ዓለም ሕዝብም እንዲሁ መጠቀሚያ መሆን የለበትም።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 02.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14nfA

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 02.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14nfA