የአሮጌዉ አመት ሒደትና አዲሱ አመት | ኢትዮጵያ | DW | 15.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአሮጌዉ አመት ሒደትና አዲሱ አመት

የፖለቲካ ዉዝግብ፥ የድንበር ዉዝግብ፥ የኑሮ ዉድነት፥ የድርቅ ረሐብ ሥጋት እንዳጀለዉ የባተዉ ሁለት ሺሕ-ሁለት የሰላም፥ የእድገት ብልፅግና እንዲሆን እንደገና እንመኝ።ምኞታችን የፈረንጆቹን ምኞት ፈረስ ቢሆንን እንዳስተርትብን-እንደገና እንመኝ

default

14 09 09

የኢትዮጵያዉን የጊዜ ቀመር ሒደት የአስራ-ሁለት ወራት-ከአምስት ቀን ዓዉዱን ገጠመና አዲስ አመት አሉ።እንደ ወግ፤ ልምድ፣ እድር-ባሕላቸዉ ሁሉ አዲሱ ዘመን እኩይ፣ መጥፎዉ፤ ሐኬት ጫጭቶ-ጠፍቶበት፣ ሰናይ፣ ጥሩ፣ ሐሴት እንዲፋፋ-እንዲሞላበት በግልም በጋራም ተመኙ።ፀለዩም። ፀሎት-ምኞቱ እንዲይዝ እንደገና እንመኝ-እንፀልይም።አሜን።የአዲሱ ዘመን ሒደት-ከከሰናይ-ጥሩ፣ ሐሴቱ ይልቅ እኩይ-መጥፎዉ ባየለበት በአሮጌዉ ዘመን ፈር-የመተለሙ ሐቅ ግን የፀሎት-ምኞቱን ማሳረጊያ እንዳያረዳ-በርግጥ ያሰጋል።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የአሮጌዉን ዘመን የጎላ እዉነት እየጠቀስን፥ የአዲሱን ዘመን-ምኞት-ፀሎት የመያዝ-መሳቱን እንዴትነት ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።
ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ።በአዲሱ አመአት (ሚሊኒየም) ዋዜማ።በ1997 የተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ዉዝግብ፥ ግጭት ባንፃራዊ ምዘና በቀዘቀዘበት፥በዉዝግብ-ግጭቱ ሰበብ የታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በተፈቱበት ማግስት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዉ ያሉት-አይሆንም ብሎ መጠራጠር በርግጥ ከባድ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የግራ-ቀኝ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ለሚወዷት ሐገራቸዉ በገራ እንዲጥሩ ሲናገሩ እሳቸዉና እሳቸዉ የሚመሩት የፖለቲካ ማሕበር በአዲሱ አመአት አዲስ የተሻለ መርሕ የመየቀሱ፥ እንደ ሐገሪ መሪ የተቀናቃኞችን ቅሬታ፥ ስሞታ ለማስተናገድ የመዘጋጀቱ ምልክት መስሎ ነበር።

በአዲሱ አመአት ዋዜማ-መባቻ ከፖለቲከኞች የተሰማዉ ቃል፥ከዉጪ በተለይም ከአዉሮጳና አሜሪካ በገፍ ወዳገር ቤት የተግተለተለዉ ኢትዮጵያዊ ስሜት፥ የድግስ-ፌስታዉ ብዛት ድምቀት በርግጥም ኢትዮጵያ በአዲሱ አመአት አሮጌ ችግር-ድሕነቷ ባይጠፋ-የሚቀንስላት፥የፖለቲካ ግጭት፥ ቁርቁስ ዉዝግቡ ባይወገድ-የሚቃለልላት፥ ሰላም፥ ፍትሕ፥ እድገት ብልፅግና ባይሰርፅባት የሚጀመርባት ሐገር ትሆናለች ነበር ተስፋ-ምልክቱ።

የእስከ አሁኑ ጉዞ የተገላቢጦሹን አሳያኝ ሐቅ ማፍጋቱ እንጂ ሰቀቀኑ።ኢትዮጵያዉያን የአዲሱን አመአት ሰወስተኛ አመት የተቀበሉት በመጀመሪያዉ አመት በተጀመረዉ፥ በሁለተኛዉ አመት በጋመዉ በፖለቲከኞቻቸዉ ዉዝግብ-መወነጃጀል፥ ክፍፍል፥ታጅበዉ፥ የኑሮ ዉድነት፥ የመብራት፥ የንፁሕ ዉሐ እጦት ችግርን ተሽክመዉ በድርቅ ስጋት፥እየተሽማቀቁ ነዉ።

Premierminister Zenawi Meles von Äthiopien

ጠሚ መለስ

አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች ለማስወገድ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዉ ሥልጣን መልቀቅ አለመልቀቅ ይሕን ያሕል መሠረታዊ የሚባል ጥያቄ አልነበረም።አይደለምም።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን ከአርብ ጀምሮ አሮጌ-በምንለዉ አምና ሥልጣን ለመልቀቅ ዝግጁ መሆናቸዉን አሉት፥ አሉትና በአዲሱ አመት ዋዜማ በነበሩበት ፀኑ።የ1997ቱ ምርጫ «በኢትዮጵያ ታሪክ አቻ የማይገኝለት ዲሞክራሲያዊ» የሚል አድናቆት እንዲያተርፍ እንደተቃዋሚ ፓርሪ ጉልሕ አስተዋፅኦ ያደረገዉ የያኔዉ ዋና ተቃዋሚ የፖለቲካ ማሕበር መሪዎች፥ እስረኛ በነበሩበት ጊዜ ብዙ ብለዉ ነበር።

የእስር ቤቱ ጥበት፥ እንግልት፥የመታሰሩ ጭንቀት፥ የቁጥጥሩ ጥብቀት፥ ሳይበግራቸዉ ለነፃነት መስፈን፥ ለዲሞክራሲ ፅናት ታግለዉ እንደሚያታግሉ፥አሜሪካና አዉሮጳ የሚኖሩ ደጋፊዎቻቸዉ መከፋፈላቸዉን አቁመዉ ባንድነት እንዲቆሙ በዳጎሰ መፅሐፍ፥ በመጣጥፍ-ደብዳቤ ቃል-ሲገቡ፥ ሲመክሩ ሲያሳቡ የነሱን የአድነት ፀናት ጥያቄ የሚያስገባ ከበበረ-አንድም እነሱዉ ሁለትም ልዩ አርቆ አሳቢ ብቻ ነበር።

የአዲሱ አመአት የመጀመሪያ አመት-ሁለት ሺሕ እኒያ የዲሞክራሲ-ነፃነት ጠበቆች፥ የአንድነት መካሪ ሰባኪዎች፥ምሁሮች ሲታመሙ የማይጠያየቁ፥ ባለመጠያየቃቸዉ የሚኮራረፉ ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲያቸዉን እሰወስት-አራት ለመሰነጣጠቅ የማያመነቱ መሆናቸዉን አስመስክሮ አለፈ።የያኔዉ የቅንጅት ለአንድነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሪ ያሁኑ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መሪ ኢንጀር ሐይሉ ሻዉል በቀደም እንዳሉት ፓርቲያቸዉ ካለፈዉ አርብ ጀምሮ አምና የምንለዉን አመት ያሳለፈዉ ለዘንድሮዉ ምርጫ ተጠናክሮ ከመዘጋጀት ይልቅ ዳግም በመደራጀት ነበር-ያሳለፈዉ።

የቀድሞዋ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የፖለቲካ ማሕበር ምክትል ሊቀመንበር ከቅንጅቱ መፍረስ በሕዋላ የተመሰረተዉ የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ባለፈዉ አመት በድጋሚ ታስረዋል።የፓርቲዉ ቀሪ መሪዎች መሪያቸዉ ለማስፈታት ከመረባረብ ይልቅ እርስ በርስ ሲወዛገቡ፥ሲወነጃጀሉ፥አንድነታቸዉን አፍረሰዉ ከሌሎች ጋር ሌላ አንድነት ለመመስረት ሲባትሉ አመት ሔዶ-ሌላ አመት መጣ።

ባለፈዉ አመት የዉይይት መድረክ በሚል ስም የተደረጀዉ ማሕበር የሚያስተናብራቸዉ ስምንት የፖለቲካ ማሕበራትና ሁለት ግለሰቦች ለዘንድሮዉ ምርጫ ተቀናጅተዉ ለመወዳደር መወሰናችዉን በአዲሱ አመት ዋዜማ ማስታወቃቸዉ ለቃል-ብሒል አንድነትን፥ ለምግባር ድርጊትን ብዙነትን ለሚመርጡት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አዲስ ክስተት-የአዲሱ አመትም ጥሩ ጅምር ነዉ።

ከመድረኩ መስራች አንዱ የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንዳሉት ግን መንግሥት የሚያደርሰዉ ጫናና ወከባ የመድረኩ አባላትም ሆኑ ለሌሎቹ ተቃዋሚዎች የሚቋቋሙት አይነት አለመሆኑ ነዉ የጥሩዉ ጅምር-ፈጥፎ ፈተና።

ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን መፈታቱ ለብዙ አዲናቂዎቹ በርግጥ ብስራት ነዉ።የቴዎድሮስ አድናቂ ብስራቱን የሰማዉ፥ ባለሥልጣናትን ለመግደል፥ መንግሥትን ለመገልበጥ፥ ሐገር ሕዝብን ለማሸበር አሲረዋል የተባሉ ሰላሳ-ሰባት ሰዎች ባንድ ጊዜ መታሰራቸዉ በሰማ-በንፈቁ ግድም ነበር።

የጦር ጄኔራሎችን ጨምሮ እስር-ቤት የገቡት ሰዎች ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ከፈረሰ በሕዋላ ዉጪ ሐገር የተመሠረተዉ የግንቦት ሰባት የፍትሕ፥ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አባላት መባለቸዉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዉዝግብ ንሮ-ክርሮ ከሽብር ፀረ-ሽብር ፍልሚያ የመድረሱን አሳዛኝ ዉጤት ጠቋሚ ነዉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች ልክ እንደፖለቲከኞቹ ሁሉ ሲወዛገቡ ከርመዉ እንደተወዛገቡ አመት ሔዶ-ሌላ አመት መጣ።ሐይማኖት መቻቻል፥ አብሮ የመኖር አብነት እየተባለ ለብዙ አመታት ሲነገርለት የነበረዉ የኢትዮጵያ ሙስሊም ክርስቲያኖች ግጭት ኢትዮጵያን እንዳጠናት አዲስ አመት ተባለ።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበርሊኑ የአለም አትሌቲክስ ዉድድር በሁለት ረጅም ርቀት ሩጫዎች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ፥በብራስልስ ባሳረገዉ የአመቱ ወርቃማ ሊግ ከአራቱ አሸናፊዎች አንዱ መሆኑ ለስፖርት አፍቃሪዉ፥ ለመላዉ ኢትዮጵያዊም በርግጥ አስደሳች-ኩራት ነዉ።ኢትዮጵያ ሆነዉ የቀነኒሳን ድል ከበርሊን ወይም ከብራስልስ በሚተላለፈዉ የቀጥታ የቴሌቪዥ ስርጭት ለመመልከት ግን መጀመሪያ ቴሌቪዥን ሊኖርወት ይገባል።ወይም ጎረቤትዎ ቤት ለመመልክት ማስፈቀድ አለብዎት።

ከሁለት አንዱን ካሟሉ በቂ ነዉ።ግን መብራት አለ?

ኢትዮጵያ ጦሯን ሶማሊያ ድረስ ማዝመቷ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ደግመዉ ደጋግመዉ እንዳሉት የራሱ የአሜሪካ ሕዝብ ብዙም ላልፈቀደዉ ለፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ታማኝነት ከግለጥ ባለፉ ብዙ አለማ-ግብ አልነበረዉም።ባለፈዉ ጥር መዉጣቱ እሰየዉ ነዉ።ከሶማሊያ የሚሰሙት ዘገቦች እዉነት ከሆኑ ግን የኢትዮጵያ ጦር የደርሶ-መልስ ዘመቻ አሁን አልተገታም።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ሕዝቡ በፈቃደኝነት የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እንዲያደርግ በሞባይል ስልክ ያጭር መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር።አላማዉ ጥሩ፥ መልእክቱም አስፈላጊ ነዉ።ተንቀሳቃሽ ስልክ ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሽ ነዉ።የርስዎ ተንቀሳቃሽ ሥልክ ከርስዎ ድምፅ ይልቅ «የደወሉት ቁጥር ካገልግሎት መስጪያ ክልል ዉጪ ነዉ» የሚለዉን መልዕክት ለማሰማት መጣደፏ ነዉ-ጉዱ።

መንግታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕግ እና የፀረ-ሽብር ሕግ ፀድቀዋል።ሕጎቹን ግብረሰናይ ድርጅቶች፥ የመብት ተሟጋቾቹ፥ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አጣጥለዉ ነቅፈዋቸዋል።ኢትዮጵያዊዉ በነዚሕ ሕጎች እየተገዛ ምርጫ የሚስተናገድበትን አመት ተቀበለ።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በዋዜማዉ እንዳሉት ሥለምርጫዉ በገዢ ፓርቲያቸዉና በተቃዋሚዎች መካካል የሚደረገዉ ድርድር መቀጠል አለበት።

የጠቅላይ ሚንስትሩን መልዕክት በተለይ የቀድሞዉ የትግራይ መስተዳድር መሪና ያሁኑ የአሬና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት በሌላ ነዉ የተረጎሙት።የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄ መሪ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ እንደሚሉት ደግሞ የፓርቲያቸዉ አባላትና ደጋፊዎች ሥለ ምርጫ፥ ሥለልማት፥ እድገት የሚያስቡበት ጊዜም የላቸዉም።

Bauer bei der Arbeit in Äthiopien

ገበሬዉ

የኢትዮ-ኤርትራ ካሳ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ከወጪ ቀሪ አስር ሚሊዮን ዶላር እድትካስ ወስኗል።ዉሳኔዉ አስራ-ሁለት አመት ያስቆጠረዉ የድንበር ዉዝግብ ወደ አስራ-ሰወስኛ አመት እንዳይንከባለል-የሚያግድ ግን አይደለም።

የፖለቲካ ዉዝግብ፥ የድንበር ዉዝግብ፥ የኑሮ ዉድነት፥ የድርቅ ረሐብ ሥጋት እንዳጀለዉ የባተዉ ሁለት ሺሕ-ሁለት የሰላም፥ የእድገት ብልፅግና እንዲሆን እንደገና እንመኝ።ምኞታችን የፈረንጆቹን ምኞት ፈረስ ቢሆንን እንዳስተርትብን-እንደገና እንመኝ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic