የአርጎባ ማህበርስብ ባህልና ቋንቋ | ባህል | DW | 29.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የአርጎባ ማህበርስብ ባህልና ቋንቋ

በመጥፋት ላይ እያለ መሆኑ ሲነገርለት የነበረ የአርጎባ ቋንቋ፣ በአንጻሩ በመበልጽግ ማህበረሰቡም የጽሑፍ ቋንቋን በመቅረጽ ከፊደል ቀረጻዉ በመቀጠል አርጎብኛ ለጀማሪዎች የማስተማርያ መጽሃፍ አዘጋጅቶአል። ከሁለት ከሶስት ሳምንታት በፊት ደግሞ አርጎባ አማርኛ መዝገበ ቃላት ለተጠቃሚዎች ቀርቦአል። በዚህም በማንሰራራት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነዉ።

default

የስነ-ህንጻ ጥበብ ያረፈበት ባህላዊዉ የአርጎባ ቤት በሾንኬ

በመጥፋት ላይ እያለ መሆኑ ሲነገርለት የነበረ የአርጎባ ቋንቋ፣ በአንጻሩ በመበልጽግ ማህበረሰቡም የጽሑፍ ቋንቋን በመቅረጽ ከፊደል ቀረጻዉ በመቀጠል አርጎብኛ ለጀማሪዎች የማስተማርያ መጽሃፍ ተዘጋጅቶአል። ከሁለት ከሶስት ሳምንታት በፊት ደግሞ አርጎባ አማርኛ መዝገበ ቃላት ለተጠቃሚዎች ቀርቦአል። በዚህም የአርጎባ ቋንቋ ከመምት ይልቅ እያንሰራራ ያለ ቋንቋ በማንሰራራት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነዉ።  የአርጎባ ልማት ማህበር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሰይድ ይመር  አርጎባ የብሄረሰቡም ሆነ የቋንቋዉ መጠርያ በቅድምያ በመግልጽ ማህበረሰቡ በመጀመርያ የእስልምና ሃይማኖትን የተቀበለ መሆኑን ያስርዳሉ።

Argobba – Shonke Dorf Äthiopien

በሾንኬ ብዙዉ የሚኖርዉ ተራራማ ቦታ ላይ ነዉ

 

«በተለይ በ 13ኛዉ ክፍለ ዘመን የይፋት ወላስማ ሥርወ መንግስት ንግድን መስርቶ ይኖር የነበረ በኢትዮጵያ የመጀመርያዉን እስላማዊ መንግስት የመሰረተ ከዝያም በሁለተናዉ ሂጅራ በነብዩ መሃመድ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከቁርሾች ጋር በነበረዉ ግጭት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ አረቦችን ተቀብሎ ያስተናገደ ሃይማኖታቸዉንም የተቀበለ የኢትዮጵያ የመጀመርያዉ የሙስሊም ማህበረሰብ ነዉ ማለት ይቻላል።»

ዛሪ አርጎቦች በደቡብ እስከ ባሌ በምስራቅ እስከ ሐርር፣ አፋር ሰሜን ሸዋ ትግራይ ድረስ እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ሰይድ የአርጎባ ልማት ማህበር በ1997 ከተቋቋመ በኋላ አርጎብኛ ቋንቋ ጨርሶ እንዳይጠፋ ሚና ተጫዉቶአል ይላሉ «በማህበረሰቡ ምን ክፍተት አለ የሚለዉን ለማጥናት በ1997 ዓ,ም ህብረተሰቡ የሰፈረባቸዉን አካባቢዎች ጥናት አድርገን በታሪክ በባህል በቋንቋ፣ በጤና እና በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ለማወቅ ቻልን። ቋንቋ የአንድ ብሄረሰብ ማንነት መገለጫ እሴቶች መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ የአርጎባ ቋንቋ ጠፋ ማለት የብሄረሰቡ ማንነትም ሆነ መገለጫዉ እንደሚጠፋ ተረድተን ፣ ይህን በመጥፋት ላይ ነዉ የተባለ ቋንቋን በመጀመርያ ፊደል ቀረጽንለት እራስን ማስተማርያ የሚሆን ለጀማሪዎች ቋንቋ ማስተማርያ የሚሆን መጽሃፍ አዘጋጀን፣አሁን በቅርቡ ደግሞ አርጎብኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ለተጠቃሚ አደረስን። »

Argobba - Tollaha Dorf_Äthiopien

በጠልሀ ህጻናት ቁራሃን የሚማሩበት ቦታ

አርጎብኛ የጽሁፍ ቋንቋ አልነበረም፥ ከፊደል ቀርጻዉ በኋላ ለጀማሪዎች ማስተማርያ መጽሃፍ እንደታተመ ተነግሮአል። የአርጎብኛ ፊደል ምን ይመስላል ስንል  አቶ ሰይድን ጠይቀናቸዉ ነበር። «ፊደሉ አማርኛ ፊደል ነዉ፥ ግን ፊደሉ የሳባ ፊደል በመባል ነዉ የሚታወቀዉ። በልምድ አማርኛ ፊደል በመባል ይታወቃል እንጂ አማርኛም እንደሌላዉ ቋንቋ ተዉሶ ያገኘዉ ነዉ። ስለዚህ ለአርጎባ ቋንቋ ጽሁፍ የምንጠቀመዉ በልምድ አማርኛ የምንለዉን የሳባን ፊደል ነዉ።» ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ  የቋንቋዎች ጥናት ተቋም ተጠሪ ሆነዉ ያገለገሉት እና  በአሁኑ ወቅት በዩኤስ አሜሪካ ፕሪስተን ኒዉጀርሲ በሚገኝ የሴሜቲክ ቋንቋ ጥናት ማዕከል ዉስጥ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር  ግርማ አዉጋቸዉ፥ በአርጎባ ማህበረሰብ ዙርያ ሰፊ ጥናትን በማካሄዳቸዉ ይታወቃሉ ስምወኑን የተመረቀዉንም የአርጎባ አማርኛ መዝገበ ቃላት የጻፉ ናቸዉ፣ ይህን መዝገበ ቃላት ለመጻፍ ስንት ግዜ ፈጀብዎት ላልናቸዉ 4 አመት ብለዉናል ። አርጎብኛ መዝገበቃላቱን ለማዘጋጀት የበቃነዉ አሉ ዶክተር ግርማ በመቀጠል  

«ቢያንስ ቋንቋዉን ለማይናገሩት ወይም በትንሽ ደረጃ ለሚናገሩት ሰዎች ማስተማርያ የሚሆን መጽሃፍ አዘጋጅተን ማስተማር ከጀመርን  በኋላ ለሱ አጋዥ የሚሆን መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት ስለነበረብን ነዉ የተዘጋጀዉ።»

Argobba - Tollaha Dorf

የጠልሀ መንደር ገበሪ

 

አዲሱ አርጎብኛ  አማርኛ መዝገበ ቃላት ስንት ቃላቶችን ይዞ ይገኛል፣ ዶክተር ግርማ አዉጋቸዉ በመቀጠል «እዉነት ለመናገር አስቸጋሪ ጥያቄ ነዉ። ይህን ያህል ቃላት አሉት ማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም የሲሜቲክ ቋንቋዎች በአንድ ቃል ስር በርካታ የሚመሰረቱ ቃላት ስላሉት ነዉ። ስለዚህ መዝገበ ቃላቱ ይህን ያህል ቃላት አሉት ብይ መግለጽ ባልችልም ወደ 535 ገጾችን እንደያዘ አዉቃለሁ። »

የአርጎባ ቋንቋ ከመጥፋት ድንዋልን? ለሚለዉ ጥያቄ ዶክተር ግርማ አዉግቸዉ ሲመልሱ፣ «ባለንበት የግሎባላይዜሽን ማለት በአጽናፋዊዉ ትስስር ዘመን ቋንቋን ከሞት ማዳን ይቻላል ማለት ትንሽ ይከብዳል ቢሆንም ስለ አርጎባ ቋንቋ አንድ ነገር እርግጠኛ ሆነን መናገር እንችላለን። ሙሉ በሙሉ ከሞት ድኖ አንሰራርቶ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ለሚለዉ ወደፊት በሂደት የምናየዉ ቢሆንም  በጽሁፍ ለታሪክ መቀመጥ ችሏል። እዚህ ላይ ቋንቋዎችን እንዳይጠፉ ማድርግ ባይቻል ቀርጾ መረጃዎችን ሰብስቦ ለትዉልድ ማቆየት ይቻለል። በዚህ ነገር የአርጎባ ቋንቋ ትልቅ እርምጃን አድርጎአል። ወደፊት አርጎባ ጠፋ ቢባል እንኳ መረጃ ሳይተዉልን ጠፋ የምንለዉ አይደለም። ለምርምር የሚሆኑ እሴቶችን እያስቀመጠልን ነዉ። ስለዚህም አንድ ቋንቋን ሙሉ በሙሉ ከመጥፋት ማዳን ይቻላል ለማለት ይከብዳል ግን የቋንቋን እድሜ ማራዘም ይቻላል፣ የአርጎባ ቋንቋን እድሜ ማራዘም ችለናል።»

    

የአርጎባ ልማት ማህበር የብሄረሰቡ ጉዳይ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሰይድ ይመር አርጎባ የሚለዉ ስያሚ ይላሉ «በወቅቱ የነበሩ አፄዎች አረብ ገባ ብለዉ የአርጎባ ማህበረሰብን መጠርያ ከአርጎባ ጋር ያያልዙታል። ይህ የብሄረሰቡ ትክክለኛ መጠርያ ሳይሆን ሊሉ የፈለጉት ዉጫዊ ናቸዉ ለማለት ነዉ። አርጎባዎች  መቶ በመቶ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸዉ። በእርሻ በንግድና በሽመና ይተዳደራሉ። እንደጠቀስኩት በኢትዮጵያ የነበሩት የአፄ መንግስታት የእስልምና ሃይማኖትን የማይቀበሉ ስለነበሩ ወይም ደግሞ እንደሌላዉ ሃይማኖት እኩል የማያራምዱ ስለነበሩ መጤ ናቸዉ የዉች ሰዎች ናቸዉ በማለት አረብ ገባ {አርጎባ }የሚል ስያሚ ሰጥዋቸዉ። ትክክለኛዉ ታሪክ ግን አርጎባ በኢትዮጵያ ይኖር የነበረ ጥንታዊ ህዝብ ነዉ።»በአርጎባ ብሄረሰብ፣ ባህል፤ ቋንቋ ዙርያ ከዶክተር ዶክተር  ግርማ አዉግቸዉ  እና ከአቶ ሰይድ ይመር ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ዉይይት ያደምጡ!

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ         

Audios and videos on the topic

 • ቀን 29.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14UbK
 • ቀን 29.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14UbK