የአርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም የጥበብ አሻራዎች | ባህል | DW | 09.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የአርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም የጥበብ አሻራዎች

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም ያለፈዉ ሀምሌ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።ይህ አንጋፋ የጥበብ ሰዉ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም በርካታ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ስራዎችን ትቶ ነዉ ያለፈዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:53 ደቂቃ

አርቲስት ፍቃዱ ሲታወስ

 

ትዉልዱና እድገቱ አዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ በተለምዶ ባሻ ወልደችሎት እየተባለ በሚጠራዉ ስፍራ ነዉ።የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም የተከታተለዉ እዚያዉ አዲስ አበባ ከተማ ሚያዚያ 27 እና አፄ ናኦድ ትምህርት ቤቶች ነዉ።በትምህርቱ ጥሩ ተማሪ እንደነበር የሚነገርለት  ፈቃዱ በልጅነት ዕድሜዉ ነበር ወደ ኪነ ጥበብ ሙያ  የመግባት ዝንባሌ ያደረበት።ይህንን የጥበብ ጥሪዉን እዉን ለማድረግም በትምህርት ቤት ዉስጥ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችን ለጓደኞቹ ያቀርብ ነበር።

የያኔዉ ወጣት የጥበብ አፍቃሪ  ፈቃዱ ተከለማርያም ከዚህ በኋላ ያመራዉ በዚያን ዘመን የነበሩ አብዛኛዎቹ የጥበብ አፍቃሪና ተሰጥኦ ያላቸዉ  ወጣቶች የትወና ጥበብ ይሰለጥኑበት ወደ ነበረዉ «ተስፋዬ አበበ የቲያትር እድገት ክበብ» ነበር ።

በዚህ ሁኔታ የወጣትነት  ዕድሜዉ የነብስ ጥሪዉ ወደ ሆነዉ የጥበብ ስራ ከመጣ  በኋላ ላለፉት 43 ዓመታት  በርካታ  የጥበብ ስራዎችን ያከናወነበትን  የትወና ብቃትና ለጥበቡ ያለዉ ተሰጦ የተረጋገጠበትም በዚሁ ጊዜ ነበር ይላሉ  የሙያ አባቱ ክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ።

በስልጠና ወቅት ያሳየዉ  ድንቅ የትወና ብቃትና ተሰጦዉም  በ1967 ዓ/ም በተለምዶ መዘጋጃ እየተባለ በሚጠራዉ በአዲስ አበባ የባህል አዳራሽ በተዋናይነት ተቀጥሮ ስራዉን ለመጀመር አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም  ጊዜ አልፈጀበትም ነበር።በትያትር ቤቱ ተቀጣሪ ከመሆኑ በፊት ፤   ወጋየሁ ንጋቱ፤ መሪ ተዋናይ ሆኖ በተጫወትበት «የወሬ ፈላስፋ»በተሰኜ  ትያትር  ላይ ባለጉዳይን  ወክሎ  ለመጀመሪያ ጊዜ ተወኗል።በዚህ ተዉኔት  ያሳየዉ ብቃት እንደ አንድ ስልጠና ላይ እንዳለ ጀማሪ ተዋናይ ሳይሆን ብዙዎችን  ያስገረመ  እንደ ነበር   ያስታዉሳሉ።

 የትያትር ስልጠና ከወሰዱ ሶስት ጓደኞቹ ጋር የአዲስ አበባ ባህልና ትያትር ቤት ተቀጣሪ ሆኖ የጥበብ ጉዞዉን የጀመረዉ   አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም ፤በትያትር ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ  « ባላ ካባና ባለዳባ»በተሰኜ ትያትር ላይ  የመተወን ዕድል አገኜ። ቀጥሎም ወቅቱ አብዮት የፈነዳበት ስለነበር ይህንኑ የሚመለከት «እሳት ሲነድ» የሚል ትያትር ላይ የተወነ ሲሆን በሁለቱ ትያትሮች ያሳየዉን ድንቅ ብቃት ያስተዋሉ የትያትር ቤቱ አዘጋጆች ብዙም ሳይቆይ  በብዙዎች ዘንድ ተደናቂነት ያተረፈለትን አፄ ቴድሮስን ወክሎ የተጫወተበትን ትያትር በመሪ ተዋናይነት እንዲሰራ መረጡት።

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በትወናዉ  ዓለም ከአፄ ቲዎድሮስ በተጨማሪ ኦዲስ ንጉስ ፣ንጉስ አርማህና ሀምሌት ትያትሮች ላይ ንጉስ ሆኖ በመጫወት ይታወቃል።በነዚህ የመድረክ ስራዎቹም የሙያ ንግስናዉን አሳይቷል  ሲሉ ብዙዎች ይናገራሉ።በዚህ ትያትር አፄ ቲዎድሮስ ሽጉጥ ጠጥተዉ ራሳቸዉን በሚያጠፉበት የመጨረሻ ትዕይንት ላይ ይጠቀምበት የነበረዉ የሽጉጥ ድምፅ ጀሮዉ ላይ አድርሶበት  በተደጋጋሚ ህክምና ማድረጉም ይነገራል።ነገር ግን በገጠመዉ ችግር ወደ ኋላ ሳይል ትያትሩን ለበርካታ ጊዜ የተወነ ለሙያዉ ፍቅር ያለዉ አርቲስት ነበር።

ከአዲስ አበባ የትያትርና የባህል አዳራሽ ወደ ብሄራዊ ትያትር ተዛዉሮ መስራት ከጀመረበት ከ1985 ዓ/ም ወዲህ በሰራዉ «ንጉስ አርማህ «ትያትር ላይ የጵጵስና ገፀ ባህሪ ወክለዉ  አብረዉት የተወኑት አንጋፋዉ አርቲስት ጌታቸዉ ደባልቄ ፤ አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም  ንጉስ አርማህን በታሪክ ለሚያዉቋቸዉ ሁሉ ከነ ግርማ ሞገሳቸዉ በእዉኑ ዓለም ያሳዬ  ግሩም አርቲስት ነበር ይሉታል።

አርቲስቱ ንጉስ ሆኖ ከተጫወታቸዉ ገፀ ባህሪያት በተጨማሪ የህግ ጠበቃ፤ተራ ባለጉዳይና ሌሎች የተለያዩ ባህሪያትን ወክሎ ተዉኗል።የሚያሳዝኑና የሚያስቁ ባህሪያትንም እንዲሁ።ሁሉንም ግን በብቃት እንደየባህሪያቸዉ መስሎ ሳይሆን ሆኖ ሰርቷል።

ፈቃዱ ለሙያዉ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት ያለዉ በሙያዉ የማይደራደር የኪነጥበብ ፈርጥ እንደነበርም የሚያዉቁት ይመሰክሩለታል።በዚህ የትወና ብቃቱና ለሙያዉ በሚሰጠዉ ከበሬታና  ፍቅር በርካታ ወጣት ተዋንያን የእሱን ፈለግ እንዲከተሉ መንገድ ጠርጓል።በእነዚህ ስራዎቹም በ1996 ዓ/ም ከኢትዮጵያ የሥነ ጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በትወና ዘርፍ የየረዥም ጊዜ  ተሸላሚ ሆኗል።በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴርም የሳንባ ነቀርሳ በሽታን ለመከላከል አምባሳደር በመሆን አገልግሏል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ከሁለት ዓመት በላይ ትምህርቱን የተከታተለዉ እንዲሁም  በስራ  አመራር ዲፕሎማ ያገኜዉ ፈቃዱ፤  በህይወት ዘመኑ በበርካታ ትያትሮች ላይ  የተወነ ሲሆን  ከነዚህም መካከል ቤቱ፣ የሰርጉ ዋዜማ ፣መርዛማ ጥላ፣መልዕክተ ወዛደር፣የሬሳ ሳጥን ሻጩ ፣ ኦቴሎና የቃቂ ዉርደት ጥቂቶቹ ናቸዉ። ከመድረክ ትያትሮች በተጨማሪ  በኢትዮጵያ ሬዲዎ ይቀርቡ በነበሩ የሬዲዮ ድራማወች ላይ የተወነ ሲሆን  የመፅሀፍት ዓለም ትረካ ፕሮግራም ላይም ሞገደኛዉ ነዉጤ፣ ሳቤላና ጥቁር ደም  የተሰኙ መፃህፍትን ተርኳል።በእነዚህ ስራዎቹም  ሁለገብ አርቲስትነቱን አሳይቷል።

በወጥ የአማርኛ ፊልሞችና  በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ ባለ ጉዳይ፣ገመና እንዲሁም ከህመም ጋር እየታገለ በሰራዉ መለከትን በመሳሰሉ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይም የጥበብ አሻራዉን አሳርፏል።ሙያዉን ለማሻሻል ተግቶ ከመስራቱ ባሻገር በንባብ ራሱን ለማሳደግ የሚጥርና የዉጭ ሀገር ፊልሞችን ሳይቀር ከነ ኋላ ታሪካቸዉ አበጥሮ የሚያዉቅም ነበር።ለዚህም ይመስላል የህግ ባለሙያ ሆኖ  በተጫወተበት የመጨረሻ ስራዉ በሆነዉ«መለከት» ድራማ ላይ አብረዉት የተጫወቱት የሙያ አጋሩና የመጀመሪያ አሰልጣኙ ክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ ፤ ፈቃዱ የትኛዉምንም ገፀ ባህሪ ወክሎ ቢጫወት እርሱ ሰርቶት ደካማ የሆነ ስራ የለም የሚሉት ።

አንጋፋዉ የጥበብ ሰዉ አርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም ሙያዉን ከጀመረበት ከ1967 ዓም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ያለፈዉ ሰኞ ሀምሌ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ድረስ ላለፉት 43 ዓመታት ከ150 በሚበልጡ  የጥበብ ስራዎች ላይ በብቃት ሰርቷል።እነዚህን የጥበብ ስራዎቹን ከሀገር ዉስጥ በተጨማሪ በምስራቅ ጀርመን በስዊድን በካሜሩንና ሌሎች ሀገሮች የማቅረብ ዕድል አጋጥሞት እንደነበርም ይነገራል።

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic