የአርቲስት በሃይሉ መንገሻ መታሰቢያ | ባህል | DW | 07.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የአርቲስት በሃይሉ መንገሻ መታሰቢያ

የአርቲስት በሃይሉ መንገሻ ስርዓተ-ቀብር ሐሙስ የካቲት 28 ቀን፣ 2005 ዓም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተፈፅሟል። አርቲስት በሃይሉን በቅርበት ከሚያውቁት የሙያ አጋሮቹ መካከል አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆን ጨምሮ የተለያዩ የቴአትር ባለሙያዎችና አርቲስቶች ስለ በሃይሉ መንገሻ የሚሉን ይኖራል።

አብረውት ለመስራት የታደሉ የሙያ አጋሮቹ፤ ሲበዛ ተጫዋች፣ ቀልደኛ፣ ገራገር እና እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ ከቴአትር ሙያው ያልራቀ ታታሪ ሰው ነበር ሲሉ ይገልፁታል፤ አርቲስት በሃይሉ መንገሻን። በቅርበት የሚያውቁት የሙያ አጋሮቹንና የቴአትር ጠቢባንን ከሀገር ውስጥም ከውጭም አነጋግረን ቀጣዩን ዝክር አሰናድተናል።

ሙዚቃ፦ ሙዚቃ ዋሽንት

አርቲስት በሃይሉ መንገሻ በአዲስ አበባ ከተማ ከአባቱ ከአቶ መንገሻ ከበደና ከወይዘሮ አየለች ተክለወልድ የካቲት 1 ቀን1948 ዓም ተወለደ። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃት ምህርቱን በአዲስ አበባ መድሐኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቆ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የ2 ዓመት የቴአትር ሞያ ሥልጠናን ተቀበለ።


በማከታተልም በታንዛንያ በሚሊተሪ ሣይንስ ትምህርት የሁለት ዓመት ኮርስ ወሰደ። ወደ ሶቪየት ህብረት በመጓዝም በሞስኮ የቴአትር ኪነጥበብ አካዳሚ ለ5 ዓመታት ትምህርቱን በመከታተል በቴአትር ዝግጅት (ማስተርኦፍአርትስ) ዲግሪውን አግኝቷል ይላል ዓለም ፀሐይ ወዳጆ ለንባብ ያበቃችው አጭር የህይወት ታሪክ መግለጫ።

አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ከልጅነት ዘመን አንስቶ አብሯት የተማረውን የጥበብ ወዳጇን በማጣቷ የተሰማት ሀዘን ጥልቅ እንደሆነ በመጥቀስ ስለ በሃይሉ ማንነት እንዲህ ታብራራለች።

አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ

እስኪ አርቲስት በሃይሉ መንገሻ በህይወት በነበረበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአርቲስት ዓለምፀሐይ የሚንቀሳቀሰው «ጣይቱ የባህል ማዕከል» ውስጥ ካቀረባቸው ስራዎች ውስጥ የሚከተለውን እናድምጥ።

አርቲስት በሃይሉ መነባንብ

አርቲስት በሃይሉ ቀንጭቦ ያቀረበውን «ቴዎድሮስ የመቅደላ ስንብት» የተሰኘውን መነባንብ ነበር ያስደመጥናችሁ። አርቲስት በሃይሉ በትወና «የክትነሽ» ቪዲዮፊልም አባውቃውና ጋዜጠኛው፣ በመድረክ ቴአትር ደግሞ የአርባቀኑ መዘዝ፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ አፅም በየገፁ፣ አቦጊዳ ቀይሶ እና ሐምሌት ላይ በተዋናይነት ተሣትፏል። በቴአትር አዘጋጅነት ሞያው የእጮኛው ሚዜ፣ አንቺን አሉ፣ ቅኝት፣ ውጫሌ17፣ ፍቅር በእሜሪካ፣ የደም ቀለበት፣ የከርቸሌው ዘፌኝ እና የምሽት ፍቅረኞችን አዘጋጅቶ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈውለታል። አርቲስት ዓለምፀሐይ አርቲስት በሃይሉ መንገሻ አብሯት እንደተማረና አብረው እንዳደጉ በመጥቀስ፤ በተለይ አሜሪካን ሀገር ከመጣ ወዲህ በጣይቱ የባህል ማዕከል የነበረውን ተሳትፎ በዚህ መልኩ ትገልፃለች።

አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ

ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ በበኩሉ አርቲስት በሃይሉ መንገሻ በአንድ ወቅት የስራ ባልደረባው እንደነበረ ይገልፃል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ስለ በሃይሉ መንገሻ ጤንነት እና የአሜሪካን ሀገር የጥበብ እንቅስቃሴ በቅርበት ይከታተልና ይሰማ እንደነበር በመጥቀስ ማረፉ በርካታ የጥበብ ሰዎችን እንዳስደነገጠ ገልጿል።

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ

አርቲስት ጌታቸው አያይዞ ለአርቲስት በሃይሉ መንገሻ መታሰቢያ የሻማ ማብራት ስነስርዓት በብሔራዊ ቴአትር በዛሬው ዕለት እንደተከናወነ ጠቅሷል። ከበሃይሉ ጋ አብረው ከሰሩ አርቲስቶች መካከል አርቲስት ወለላ አሰፋ አንዷ ናት፤ ስለ በሃይሉ እንዲህ ትላለች።

Kerze Kerzenschein

አርቲስት ወለላ አሰፋ

አርቲስት በሃይሉ መንገሻን ከ1982 ዓ ም አንስቶ እንደሚያውቀው የሚያስታውሰው አርቲስት ተስፋዬ ሀይሌ አብሬው ከመስራትም አልፎ ቅርበታችን ጥልቅ ነበር ይላል።

አርቲስት ተስፋዬ ሀይሌ

አርቲስት በሃይሉ በቴአትር ዝግጅት ወቅት ተዋንያንን ከማጨናነቅ ይልቅ ዘና እያደረገ የተሰጣቸውን ገፀ ባህሪያት በቀላሉ እንዲላበሱ ያደርግ የነበረውን ጥረት እንደሚያደንቅ ጠቅሷል። ሌላኛው አርቲስት ካሳዬ ገበየሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ረዘም ያለ ቴአትር ላይ የተሳተፈው በበሃይሉ ዝግጅት እንደሆነ በመግጠቆም በሃይሉን ልዩ በሆነ አጋጣሚ ያስታውሳል።

አርቲስት ካህሳዬ ገበየሁ

በእርግጥም ከአርቲስት በሃይሉ ጋ አብረው የሰሩ አርቲስቶች ብዙዎቹ ይህን ዘና የማድረግ ባህሪውን ያስታውሱለታል። እስኪ አሁን ደግሞ ጣይቱ የባህል ማዕከል ውስጥ የባለቅኔ እና ደራሲ መንግስቱ ለማ «ባሻ አሸብር ባሜሪካ» ግጥምን ለታዳሚያን እንዴት እንዳቀረበው በከፊል እንከታተል።

አርቲስት በሃይሉ መንገሻ የቴአትር ክፍል ሀላፊ፣ ከፍተኛ የቴአትር አዘጋጅ፣ ፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ሀላፊ እንዲሁም አርቲስቲክ ዳይሬክተር ሆኖ ሰርቷል። በቴአትር፥ በሙዚቃ በሥዕልና ሥነጽሁፍ የሥነጥበባት ማስትባበሪያ ቡድን መሪ፣ በሥነጥበባት ዋና ክፍል ሃላፊነት፣ በፊልም ትምህርት መምህርነት፣ በትወናሞ የወጣቶች አሰልጣኝነት አገልግሏል። በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለ6 ዓመታት ተኩል የቴአትርና የባህል አዳራሽን በዋና ሥራአስኪያጅነት መርቷል። አርቲስት በሃይሉ መንገሻ የአንድ ልጅ እና የሁለት ልጅ ልጆች አባት ሲሆን፤ ባደረበት ሕመም ሲረዳ ቆይቶ ባለፍነው እሁድ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የአርቲስት በሃይሉ መንገሻ ስርዓተ-ቀብር በዛሬው ዕለት አሜሪካን ሀገር በፎርት ሊንኮልን መካነ-መቃብር ተከናውኗል።

የአርቲስት በሃይሉ መንገሻ ዜና ረፍትን አስመልክቶ ያሰናዳንላችሁ ጥንቅር በዚሁ ይጠናቀቃል። አዘጋጅቼ ያቀረብኩላችሁ ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ፤ መልካም ጊዜ፤ ጤናይስጥልኝ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic