1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአረፋ ክብረ በአል በአዲስ አበባ

እሑድ፣ ሰኔ 9 2016

1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል-አድሃ ወይም አረፋ በዓል ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ .ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከብሯል። በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰላት ስግደት፣ ተክቢራ እና መሰል ሃይማኖታዊ የፀሎት ሥነ ሥርዓት በተከበረው አረፋ፤ የሃይማኖቱ ተከታዮች ከንጋቱ ጀምሮ ንፁህ ለብሰው በመሰባሰብ አክብረውታል።

https://p.dw.com/p/4h6bY
የዒድ አል-አድሃ ወይም አረፋ በአዲስ አበባ ስታዲየም
1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል-አድሃ ወይም አረፋ በዓል ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ .ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከብሯል። ምስል Solomon Muchie/DW

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ዋለ

የአረፋ ክብረ በአል በአዲስ አበባ

1 ሺህ 445ኛው የዒድ አል-አድሃ ወይም አረፋ በዓል ዛሬ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ .ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከብሯል።

በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰላት ስግደት፣ ተክቢራ እና መሰል ሃይማኖታዊ የፀሎት ሥነ ሥርዓት በተከበረው አረፋ፤ የሃይማኖቱ ተከታዮች ከንጋቱ ጀምሮ ንፁህ ለብሰው በመሰባሰብ አክብረውታል።

ክብረ በዓሉ የመረዳዳትና የማካፈል ተግባራት የሚፈፀምበት ሲሆን፣ ከብሔራዊ ስታዲየም በተጨማሪ በዙሪያ ገባውም ሰፊ ምዕመን በተገኘበት ተከብሯል።  

ብሔራዊ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሃይማኖታዊዉ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል።

ምዕመናን ደም እንዲለግሱ ተጠየቀ 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእስልምና ሃይማኖት የአደባባይ ክብረ በዓላት ላይ ከስግደት እንዲሁም የጋራ ፀሎት በስተቀር ከሃይማኖቱ መሪዎችም ሆነ ከመንግሥት ተወካዮች ንግግር አይደረግም፤ ዛሬም በተመሳሳይ የሆነው አንደዚያ ነው።

ዛሬ የተከበረው 1445 ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ረፋድ የተከበረ ሲሆን፣ ያነጋገርናቸው የበዓሉ ታዳሚያን ሙስሊሞች እንዲህ ባለው በዓል ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው መድረሻ ያጡት የሚታሰቡበት ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።

"ወደ ሃምሳ በሬዎችን እና ሰመንያ በጎችን ከሰገድን በኋላ ለችግረኛ ለማካፈል ነው የምንሄደው" ያሉን አንድ ሰው "በየ አካባቢው ያሉ ሰዎች ይህንን እንዲፈጽሙ ነው የምናበረታታው" ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

"የዚህን ቀን ተካፍለን፣ ተዋደን ሁሉንም ማድረግ ያለብን ቀን ነው ብየ ነው የማምነው።" ሲሉም አክለዋል።

የመውሊድ በዓል አከባበር በሐረር ከተማ

ከእስልምና ሃይማኖት በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የሆነው አረፋ አቅም ያላቸው በሳውዲ አረቢያ ሃጂ በማድረግ፣ ሌሎች ደግሞ በያሉበት በመረዳዳት የሚያከብሩት ነው።

"በተፈጥሮ አደጋም፣ በሰው ሰራሽም በየቦታው ችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችንንም የምናስብበት" ነው ያሉ ሌላ የበዓሉ ታዳሚ "ለሌላቸው በመድረስ ሁሉም ደስተኛ ሆኖ እንዲያሳልፍ ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

"ሀገራችን ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። በተወሰኑ አካባቢዎች የሰላም እጦት አለ። ያሉት የሰላም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ጥሩ ነገር ማድረግ ያለብን ጊዜ ነው"

በአዲስ አበባ ስታዲየም እና ዙሪያው በሰላት ስግደት የተከበረው 1445ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል አድሃ ወይም የአረፋ በዓል ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም ተከናውኖ መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተባለው አካል አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ