የአረቦች ጠብ | ዓለም | DW | 12.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአረቦች ጠብ

የሪያድ-ዶሐ፤የአቡዳቢ ዶሐ፤የማናማ ዶሐ ጠብ፤ ግጭት፤ ዉዝግብ አዲስ አይደለም። የምዕራቦችን በተለይም  የዋሽግተኖችን «ፈገግታ» ለማግኘት ነዳጅ ዘይት እየዛቁ፤ ሕዝባቸዉን እየረገጡ፤ለምዕራቦች ዶላር ለማስታቀፍ ሲሽቀዳደሙ እርስበርስ መላተም ከጀመሩበት ከ1970ዎቹ ወዲሕ ግን የንግድ ጉዳይ አጥኚ አሊሰን ዉድ እንደሚሉት የሰሞኑ ጠንካራዉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:04

የአረቦች ጠብ

ብሪታንያዊዊ ጄኔራል ሰር ሌዊስ ፔልይ በ1868 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወደ ፋርስ ባሕረ-ሠላጤ የቀዘፉት በሐገራቸዉ መርከቦች ላይ የሚደርሰዉን ዘረፋና ጥቃት የካባቢዉ ገዢዎች እንዲያስቆሙ ለማስጠንቀቅ ነበር። ጄኔራሉ የዛሬዎቹን የቀጠር፤የባሕሬንና የአቡዳቢ ገዢዎችን አነጋግረዉ የገዢዎቹን ጠብ አቀጣጥለዉ፤ ለታላቅ ቅኝ ገዢ ሐገራቸዉ ትናንሽ ቅኝ ተገዢዎችን አትርፈዉ ተመለሱ።በ145ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ሪያድ ላይ የሙስሊም ሐገራት መሪዎችን የሠበሰቡት የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ሙስሊሞቹ መንግሥታትን በሙስሊሚቷ ኢራን ላይ ለማሳደም ነዉ። ዋሽግተን ሲደርሱ ባንድ ያደሙ-አንድ የሚመስሉ አረቦች ዉጊያ ቀረሽ ጠብ ገጠሙ። ታሪካዊ፤ የታቀደ እንበል ወይስ አጋጣሚ? 

በ2009 ከዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አፈትልኮ የወጣ አንድ ሚስጥራዊ ሰነድ፤ የያኔዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን «የአል፤ቃኢዳ፤ የታሊባን፤ የኤል ኢ ቲ እና የሌሎች አሸባሪዎች የገንዘብ ምንጭ አሁንም ሳዑዲ አረቢያ በመሆንዋ ብዙ መሠራት አለበት» ማለታቸዉን ሰነዱ ።የወይዘሮ ሒላሪ የምርጫ

ዘመቻም ሆነ የባለቤታቸዉ የቢል ክሊንተን ድርጅት (ፋዉንዴሽን) ትልቅ የገንዘብ ምንጭ ሳዑዲ አረቢያዎች ናቸዉ።ወይዘሮ ክሊንተንን የተኩት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ በበኩላቸዉ ቀጠሮች «ሰኞ ሐማስን ረድተዉ ማክሰኞ ከናንተ ጋር ነን ሊሉን አይገባም» ብለዉ ነበር።

ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ከሪያድ-ካይሮ፤ ከማናማ አቡዳቢ የሚሰማዉ ፕሮፓጋንዳ ግን እንደ ክሊተን ሳዑዲ አረቢያን  ሳይሆን እንደ ኬሪ ቀጠርን በአሸባሪነት የሚወነጅል፤ያስቀጣ እና ለሌላ ቅጣት የሚያዝት ነዉ።እርግጥ ነዉ የሪያድ-ዶሐ፤የአቡዳቢ ዶሐ፤የማናማ ዶሐ ጠብ፤ ግጭት፤ ዉዝግብ አዲስ አይደለም።

የምዕራቦችን በተለይም  የዋሽግተኖችን «ፈገግታ» ለማግኘት ነዳጅ ዘይት እየዛቁ፤ ሕዝባቸዉን እየረገጡ፤ለምዕራቦች ዶላር ለማስታቀፍ ሲሽቀዳደሙ እርስበርስ መላተም ከጀመሩበት ከ1970ዎቹ ወዲሕ ግን የንግድ ጉዳይ አጥኚ አሊሰን ዉድ እንደሚሉት የሰሞኑ ጠንካራዉ ነዉ። «እንዲሕ ዓይነት ነገር ሲከሰት ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።የንግድ ተቋማት ባሁኑ ጠብ ምን ያሕል እንደተጎዱ እያጠኑ ነዉ።በረራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፤ የመርከብ ጉዞም በተለይ የወደብ ሥራና አገልግሎትም ተጎድቷል። ይሕ ግልፅ ነዉ። ዶሐ በሚገኙ እና ከዶሐ ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸዉ በሌሎች የንግድ መስኮች ላይ  ያደረሰዉን ተፅዕኖ በቅርብ እየተከታተልን ነዉ። GCC ወይም ሳዑዲ አረቢያና ባሕሬን የሚያደርጉትን እናያለን።»

የዑመያዎች ሥርወ መንግስት ከመካከለኛዉ ምሥራቅ-እስከ ሰሜን አፍሪቃ የተዘረጋዉን ሰፊ ግዛት በሚገዛበት በሰባተኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ከፈረስና ግመል ማርቢያነት ባለፍ እንደ ግዛት የሚቆጥራት አልነበረም።

የሙስሊሞቹ ኸሊፋት ማዕከላዊ አገዛዝ እየደከመ፤ የየአካባቢዉ የጎሳ መሪዎች ሥልጣን እየጠነከረ ሲመጣ ያቺ ትንሽ ልሳነ-ምድር የአልማዝ ማዉጪያ፤ መሸጪና የሸቀጥ መተላለፊያነቷ እየጎላ የአካባቢዉ ጠንካሮችን ቀልብ  እየሳበች መጣች።ቀጠር።

በ1788 ዘዉድ የደፉት የዛሬዋ ሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ሰዑድ ኢብን አብድል አዚዝ ከኩዌት ለፈለሱት ኡታብ ለተሰኘዉ ነገድ ገዢዎች የኸሊፋ ቤተሰብ የቀጠርም፤ የባሕሬንም፤ ገዢ መሆናቸዉን ደገፉ።

ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ግን የኡስማን ቱርኮችን ጠንካራ የገዢነት አጥር ሰብረዉ ለመግባት ሲያደቡ የነበሩት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች የመጀመሪያዉን ጠንካራ ሙከራ አደረጉ።

በብሪታንያ መርከቦች ላይ አደጋ ተጥሏል በሚል ሰበብ የብሪታንያ ባሕር ኃይል ዶኻን  አወደማት፤ የኸሊፋ ቤተሰብም ቀጠር ላይ አንፈራጥጦት የነበረዉ እግሩ ተቆርጦ ማናማ ላይ ብቻ ቀረ።መሐመድ ቢን ሳኒ ቢን መሐመድ አል ሳሚር የእንግሊዝ ጦር የከመረዉን ትቢያ አራግፈዉ የመጀመሪያዉን የአሳኒ ሥርወ-መንግሥትን መሠረቱ።1825።

የብሪታንያ ቦምብ ሳዑዲ አረቢያ፤ ቀጠር እና ባሕሬንን ሰወስት ሐገራት አደረገ።ይሁን እንጂ ከ1825 ጀምሮ የተፈራረቁት የሰዑድ፤ የኸሊፋም ሆኑ የሳኒ ሥርወ መንግሥታት ሲሻቸዉ እንደ ጥብቅ ዘመድ እየተፈቃሩ፤ ሲላቸዉ እንደጠላት እየሻኮቱ ዘመን ከመቁጠር ባለፍ፤ የሕዝባቸዉን ግንኙነት፤ ድንበራቸዉን፤የፖለቲካ መርሐቸዉን በተመለከተ ለአንድነት-ልዩነታቸዉ ደርዝ አብጅተዉለት አያዉቁም።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ተሸንፈዉ የገዢነቱን ሥልጣን በብሪታንያዎች የተቀሙት ቱርኮችም ሆኑ ብሪታንያዎች ጠቡ-ሲከር ረገብ፤ ወዳጅነቱ ሲጠብቅ-ላላ በማድረግ የአገዛዝ ሥልት እስከ 1970ዎቹ ድረስ ቆዩ።

በ1971 ቀጠር ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች የሐገርነት እዉቅና ቀድማ የሰጠቻት

ሳዑዲ አረቢያ ነች።የቀጠርና የሳዑዲ አረቢያ ድንበር ግን እስከ ዛሬ ድረስ በሕግ አይታወቅም። ቀጠር ነፃ እንደወጣች ከባሕሬን ጋር የገጠመችዉ የደሴቶች ይገባኛል ጠብ የተዘጋዉ በ2001 ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ባሳለፈዉ ዉሳኔ ነዉ። ቀጠር በጣም ትንሽ ሐገር ናት።አንጡራ ዜጋዋ 4 መቶ ሺሕ አይደርስም። የጋዝና የነዳጅ ሐብቷ ግን ከምትሸከመዉ በላይ ነዉ። ትንሽ-ደካማነቷን በኃብት ጉልበቷ ለማካካስ ለአካባቢዉም ለአዉሮጳ-አሜሪካ ኃያላንም ገንዘቧን ትረጫለች።

ትንሽ ጎረቤታቸዉ በየአካባቢዉ በሚለኮሰዉ ጦርነትም፤ በየሥፍራዉ በሚደረገዉ ድርድርም በየዘመኑ በሚፈበረከዉ ቴክኖሎጂም፤ በየመስኩ በሚያከብር-በሚያነስረዉ ንግድም «አለሁ አለሁ» ማለቷ በተለይ ለሪያድ ገዢዎች እንደመቅበጥበጥ ነዉ-የሚታየዉ። አሚር ኸሊፋ ቢን ሐማድ አል ሳኒ የሪያድ ገዢዎች ቁጣ ጠጠር ሲል ሩጫቸዉን ገታ፤ ቁጣዉ ረገብ ሲል ፍጥነታቸዉን ጨመር እያደረጉ መግዛቱ ተሳክቶላቸዉ ነበር።

በ1995 አባታቸዉን ከሥልጣን አስወግደዉ የዶሐን ዘዉድ የጫኑ ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል ሳኒ ግን ለሪያዶች ተግሳፅ የሚመለሱ አልሆኑም። ሪያዶች በ1996 ሐማድን ከሥልጣን አስወግደዉ አባታቸዉን፤ በ2005 ደግሞ የአጎታቸዉን ልጅ  ለማንገስ ሁለቴ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድርገዉ ነበር። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ  አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለማጥፋት ማሴር መጠላለፋቸዉን ይበልጥ አናረዉ። እንደገና አቶ ዩሱፍ ያሲን።

                        

አሚር ሐማድ በ2013 በፈቃዳቸዉ ሥልጣን ሲለቁ ያነገስዋቸዉ የልጃቸዉ የታሚም ቢን ሐማድ አሳኒ መርሕም  «ያባቱ ልጅ» የሚያሰኝ ነዉ። በ2014 ሳዑዲ አረቢያ እና ተከታዮችዋ የያኔዉን የ34 ዓመት ወጣት አሚር ለማስደንገጥ ከቀጠር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸዉን ላጭር ጊዜ አቋርጠዉ ነበር።

የሳዑዲ አረቢያ፤የባሕሬንና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እርምጃዉን የወሰዱት ቀጠር፤ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ነገስታትን የሚቃወሙ የሙስሊም ወድማማቾች ማሕበር አባላትን ትደግፋለች የሚል ነበር። በግብፅ ሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን ይዞ የነበረዉ የሙስሊም ወድማማቾች ማሕበር፤ የማሕበሩን ፕሬዝደንት በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደዉ ሥልጣን ለያዙት ለግብፅ የጦር ጄኔራልም፤ በዉርስ ዙፋን ላይ ለተቀመጡት ለሪያድ፤ለማናማ እና ለአቡዳቢ ነገስታትም እኩል አሸባሪ ነዉ።

ለፍልስጤም ነፃነት የሚዋጋዉ ሐማስ፤ የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ፤ ሁለቱን የምትረዳዉ ኢራንም ለሪያድ፤ለማናማ፤ለአቡዳቢ ገዢዎችም ለቴል አቪቭ፤ ለዋሽግተን-ብራስልስ ገዢዎችም ልክ እንደ አልቃኢዳ፤ ልክ እንደ እስላማዊ መንግሥት አሸባሪዎች ናቸዉ። ካሁኑ ዉንጀላ ዋናዉ፤ የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አደል አል ጀባር በቀደም እንዳሉት ቀጠር ከእነዚሕ ቡድናትና ከኢራን ጋር ትተባበራለች መባሉ ነዉ።

                         

«እኛና ሌሎች በርካታ መንግሥታት በቀጠር ላይ እርምጃ የወሰድንበትን ምክንያት እዚሕ ለሚገኙ ባልደረቦቼ ገልጬያለሁ።ቀጠር ለአሸባሪ ድርጅቶች የምትሰጠዉን ድጋፍ እንድታቋርጥ ያቀረብነዉ ጥያቄ ተቀብላ ዳግም ጎረቤታችንና ሸሪካችን እንድትሆን ነዉ።»

ባሕሬንና የተባበሩት

ኤሚሬቶችን እንደ ሳዑዲ አረቢያ ሁሉ ከትንሽ ጎረቤታቸዉ ጋር በይደር የያዙት ጠብ አላቸዉ።ወታደራዊ መለዮቸዉን በሱፍ ከራቫት የቀየሩት ጄኔራል አልሲሲ ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ዶላር ከሚቆርጡላቸዉ ከሪያዶች ቃል ሊወጡ አይችሉም።በሳዑዲ አረቢያ ቦምብ ሚሳዬል ሐገራቸዉን የሚያስጠፉት፤ ርዕሠ-ከተማ እንኳ የሌላቸዉ አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ ከሪያዶች ፍላጎት ሌላ፤ ሌላ ምን ማለት-ማድረግስ ይችላሉ። ሁሉም አደሙ።አረቦቹ አረቢቱ ሐገር ላይ ሲያድሙ፤ ሁለት የአካባቢዉ ሐገራት ለቀጠር «አለሁ» ያሉ መስለዋል።

                           

የኩዌቱ አሚር ሼኽ ሳባ አል አሕመድ አ ሳባሕ ጠቡን ለማርገብ ሽምግልና ገብተዋል።ከኢትዮጵያ እስከ ሶማሊያ፤ከሱዳን እስከ ማሊ ያሉ የአፍሪቃ መንግሥታት የኩዌትን ጥረት እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል። ከአዉሮጳ ኃያላን ፈረንሳይ፤ ጀርመን እና ሩሲያ ጠቡ በድርድር እንዲፈታ ጠበኞችን እየመከሩ ነዉ። የጠበኞቹ ቱጃር ሐገራት እኩል ወዳጅ፤እኩል አስታጣቂ፤ እኩል ደጋፊ ሐገር የዩናይትድ ስቴትስ አቋም አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የሚጣረስ  ነዉ።እና ጠቡም የተጫረዉ ትራምፕ የሪያድ ጉብኝታቸዉን አጠናቀዉ ሐገራቸዉ በገቡ ሳምንት ነዉ።ታሪካዊ እንደበል፤ አጋጣሚ ወይስ ሌላ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

                                

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች