የአረብ አብዮት፥ የሶሪያ አብነት | ዓለም | DW | 20.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአረብ አብዮት፥ የሶሪያ አብነት

ሊቢያ ቀን-አስከሬን ትቆጥራለች።ሰነዓ የዘመናት ገዢዋን ሸኝታም በመለወጥ-አለመለወጥ ተቃርኖ-እንደተቃረጠች ነዉ።ከሰወስቱ ቀዳሚዉን መለየት አሁንም ብዙዎችን እንዳለያየ ነዉ።ደማስቆ ግን በርግጥ ፈጥናለች።

default

ተቃዉሞ ከስደትኞች ጣቢያ

20 06 11

የቱኒስ-ካይሮዉ ድል-ዉድቀት ከራባት-አልጀርስ፣ይልቅ፣ትሪፖሊ፣ ከአማን-ሙስካት ይበልጥ ሰነዓ-ማናማ-እንደሚያሰልስ ለመስማማት ብዙ ታዛቢዎች ብዙ ምክንያት ነበራቸዉ።ማናማን በደማስቆ ለመተካትን ግን ብዙ መጠበቅ የብዙዎችን የልብ ትርታ ማድመጥ ግድ ነበረባቸዉ።ደማስቆ በርግጥ ማናማን ቀይራለች።ትሪፖሊ ዛሬም ትጋያለች።ሊቢያ ቀን-አስከሬን ትቆጥራለች።ሰነዓ የዘመናት ገዢዋን ሸኝታም በመለወጥ-አለመለወጥ ተቃርኖ-እንደተቃረጠች ነዉ።ከሰወስቱ ቀዳሚዉን መለየት አሁንም ብዙዎችን እንዳለያየ ነዉ።ደማስቆ ግን በርግጥ ፈጥናለች።የደማስቆን ፍጥነት መነሻችን፣ ሰሞናዊ እዉነቷ ማጣቀሻ፤ የአረቦች የለዉጥ ሒደት እንዴትነት መድረሻን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

እንደ ብዙዎቹ አረብ ብጤዎቹ በሙስና በተዘፈቁ፣ አምባገንን ገዢዎቹ ጭካኔ ለዘመናት የሚማቅቀዉ፤ በኑሮ ዉድነት፣ በሥራ አጥነት የሚሰቃየዉ የሞሮኮ ሕዝብ ከቱኒዚያና ከግብፅ ብጤዎቹ ለመማር ጊዜ አላጠፋም ነበር።ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ እንደ ሕዝባቸዉ ግን በተቃራኒዉ ከቱኒስ እና ከካይሮ ገዢዎች ሥሕተት ለመማር አልዘገዩም።

በገዢዎቹ ላይ ያቄመዉ ሕዝብ እንደ ደፋር፣ ጅግና ጎረቤቶቹ ለመብት ነፃነቱ ለመታገል ባለፈዉ የካቲት የካሳብላንካንና የራባትን አደባባዮች ማጥለቅለቅ ሲጀምር ንጉሱ አመፁን የሚደፈልቅ ጦር ከማዝመታቸዉ እኩል የሕዝቡን ቅሬታ ለማለዘብ በሕዝብ የተጠሉ ሹማምንቶቻቸዉን ሽረዉ ሌላ ሾሙ።የምግብ ዋጋን ቀነሱ።ሥራ አጥነትን ለመቀነስ፣ ከሁሉም በላይ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድበዉን ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል ቃል ገቡ።

ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ ባለፈዉ ቅዳሜ ያወጁት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ የሞሮኮዉ የንግድ ሚንስትር ሬዳ ቻሚ እንደሚሉት ንጉሱ ከሰወስት ወር በፊት የገቡትን ቃል ገቢር የማድረጋቸዉ ምልክት ነዉ።

«እንደማምነዉ አብዛኛዉ ሕዝብ እኛም እንደ ፓርቲ ለዉጡ በጣም አስደስቶናል።ንጉሱ የሕዝቡን ፍላጎትና እኛም የታገልንለትን ጥያቄ በድፍረትና በቁርጠኝነት መልስ ሰጥተዋል ብዬ አምናለሁ።እንደ ፓርቲ ይሕ ለዉጥ እንዲደረግ ለአርባ አመታት ያሕል ታግለናል።አሁን ግን ከጠበቅነዉ በላይ መሆኑን ልነግራችሁ እችላለዉ።»

ብዙ ተቃዋሚዎች የንጉሱን አዋጅ፥ የንጉሱ ደጋፊዎች ሥለ አዋጁ ያላቸዉን አመለካከት አልተቀበሉትም።የሕገ-መንግሥቱ ለዉጥ ያላረካዉ ሕዝብም የአደባባይ ተቃዉሞዉን እንደቀጠለ ነዉ።«የሞሮኮ ብሎገሮች ሕብረት» የተሰኘዉ ተቃዋሚ ሠልፈኛዉን በኢንተርነት የሚያደራጀዉ ስብስብ መሪ ሰዒድ ቤን ጀብሊ እንደሚሉት የሕገ-መንግሥ ማሻሻዉን አዋጅ የሞሮኮ ሕዝብ አይቀበለዉም።

NO FLASH Syrien Unruhe Krise Gewalt

ጦሩ«የሞሪኮ ሕዝብ ቃል የተገባዉን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ አይቀበለዉም።ሕዝብ የሚፈልገዉ ዘመን ያለፈበት (ሥርዓት) ለዉጥ እንጂ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ አይደለም።ይሕ በተጨባጭ ለዉጥ አያመጣም።»

ያም ሆኖ ንጉሱ ተቃዋሚዎቻቸዉን ለመከፋፋል በዉጤቱም ያገዛዝ ዘመናቸዉን ለማረዘም ዘይደዋል። ከቤን ዓሊና ከሙባረክ የተማሩት ንጉስ መሐመድ ብቻ አይደሉም።

የአል ጄሪያዉ ፕሬዝዳንት አብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃ፣ የዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላሕ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል።ወይም ለመዉሰድ ቃል ገብተዋል።የሳዑድ አረቢያዉ ንጉስ አብደላሕ የሰራተኛ ደሞዝና የተማሪ አበል ለመጨመር፥ ሥራ ለመፍጠርና መኖሪያ ቤት ለማሰራት፥ ከአንድ መቶ ሰላሳ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ መድበዋል።የኩዌቱ አሚር ሼክ ሳባሕ አል ሳባሕ ምግብ፣ መጠጥና መድሐኒት የሚቸግረዉ ዜጋቸዉን በመንግሥት ወጪ እንዲቀለብ፣ እንዲታከምም ፈቅደዋል።

ገዢዎቹ ያደረጉትና ለማድረግ ቃል የገቡት ለዉጥና ድጎማ የሕዝቡን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ የሚመልስ፣ በተለይ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያስከብር አይደለም።አመፁን ቢያንስ እስካሁን ለማዳፈን ግን በርግጥ ሰርቷል።የባሕሬኑ ንጉስ ሐሚድ ቢን ኢሳ አል-ኸሊፋ አመፀኛዉን ሕዝብ በሐይል ነዉ የደፈለቁት።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ እንደ ቢን ዓሊ እንደ ሙባረክ፥ እንደ ንጉስ አል-ኸሊፋ ሁሉ በተቃዋሚዎቻቸዉ ላይ ያነሱት ዱላ ከአለም ልዕለ-ሐያል ጦር ጋር ነዉ ያላተማቸዉ። የዓሊ አብደላ ሳሌሕ የሐይል ሙከራም አራሳቸዉን ለቦምብ አደጋ ነዉ-ያጋለጠዉ።

በአገዛዝ ዘመን፥ በበሕዝብ በመጠላትም ሌሎቹ ገዢዎች ዘግይተዉ የተቀየጡት ፕሬዝዳት በሽር ዓል አሰድ ለሕዝባቸዉ ጥያቄ የለዉጥ ቃልን ከሐይል እርምጃ የቀየጠ መልስ ነዉ-የሰጡት።አሰድ ጥር ላይ ብልጭ ብሎ መጋቢት ላይ የጋመዉን ሕዝባዊዉ ቁጣ ለማረገብ ነባር እስረኞችን ፈተዋል፥ ካቢኔያቸዉን በትነዉ ሌላ መሥርተዋል፥ከአርባ አመት በላይ የፀናዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሻሽለዋል።

አሰድ ከዛሬ በፊት ሁለቴ ባደረጉት ንግግር የገቡት ቃልም ሆነ የወሰዱት እርምጃ ግን ተቃዉሞዉን ለማርገብ የተከረዉ የለም።አርብ-ሆምስ።

የተቃዉሞ ሠልፉ በቀጠለ ቁጥር የፀጥታ አስከባሪዎችና የሠልፈኛዉ ወይም ሠልፈኛዉን የተቀየጡ ታጣቂዎች ግጭት እያየለ፥ የሚሞት የሚቆስለዉ ሰዉ ቁጥር እየጨመረ ሐገር ጥሎ የሚሰደደዉ ሕዝብም እየበረከተ ነዉ።የተለያዩ ወገኖች እንደሚገምቱት እስካለፈዉ አርብ ድረስ ከአንድ ሺሕ ሁለት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች እና ከሰወስት መቶ በላይ ፀጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል።

የደማስቆ መንግሥት ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ መቶ ሐያ ወታደሮች ተገደለዉበታል ያለዉን ሶሪያን ከቱርክ ጋር የሚያዋስነዉን አካባቢ ለመቆጣጠር በታንክ የተጠናከረ ጦር አዝምቷል። ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ጦሩ ባልደረቦቹ የተገደሉባት የጂስር አል-ሹጉር ከተማን ነዋሪ እያሰቃየ ነዉ።አንድ የአይን ምስክር ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ደግሞ የመንግሥት ጦር መስጊድ ዉስጥ የተጠለሉ ሰላማዊ ሰዎችን ሳይቀር ገድሏል።

«ባሳቲን መስጊድ ዉስጥ አስራ-ሁለት ሸማግሌዎች ነበሩ።ሁሉም ተገደሉ።ይሕ ጅምላ ግድያ ነዉ። ትናንት ሁለት ቤተ-ሰቦች ወደ ጂስር አል-ሾጉር ተመልሰዉ ነበር።አንዱ በመኪና ሁለተኛዉ በሞተር ሳይክል ነበር የሚጓዙት።ሁለቱም ተገደሉ።»

የጦሩን እርምጃ የፈራዉ የጂስር አል-ሾጉርና ከተማ የአካባቢዋ ነዋሪ ወደ ቱርክ እየተሰደደ ነዉ።የቱርክ ባለሥልጣናትና የስደተኛ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዳስታወቁት ቤት ንብረቱን ጥሎ ወደ ቱርክ የተሰደደዉ ሕዝብ አስር ሺሕ ደርሷል።ፕሬዝዳት አሰድ የብዙ ሰዎችን ሕይወት እያጠፋ የመጣዉን ተቃዉሞ ለማለዘብ እስካሁን ከወሰዱና ቃል ከገቡት እርምጃ በተጨማሪ ሌላ እርምጃ ለመዉሰድ ዛሬ ባደረጉት ንግግር ቃል ገብተዋል።

አሰድ ለመላዉ የሐገሪቱ ሕዝብ በተሰራጨ ንግግራቸዉ በለዉጥ ፈላጊዉ ሕዝብና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል በተደረገዉ ግጭት በርካታ ሕይወት፥ አካል፥ ሐብትና ንብረት መጥፋቱን አምነዋል።በፕሬዝዳንቱ ንግግር የእግሊዘኛ ትርጉም እንደተጠቀሰዉ የሰዉ ሕይወትና አካል መጥፋቱ ጉዳቱ ለሁሉም ሶሪያዊ ነዉ።

«በሁለቱም ወገን ብዙ ሕወት ጠፍቷል።ሠላማዊ ዜጎችና የፀጥታ አስከባሪ አባላት መስዋዕት ሆነዋል። ብዙ ቆስለዋል።ይሕ ለቤተ-ሰቦቻቸዉ፥ ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ለሐገሪቱም ጭምር ታላቅ ጉዳት ነዉ።ለእኔ በግሌም ቢሆን አሳዛኝ ጥፋት ነዉ።ፈጣሪ ለተሰዉት ምሕረቱን እንዲያወርድላቸዉ፥ እፀልያለሁ።ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ደግሞ ፅናቱን እመኛለሁ።»

ጥንታዊቷ፥ ታሪካዊት ሐገር ትርምስ፥ ምሥቅልቅል የማያጣዉ የመከከላኛዉ ምሥራቅ አካባቢ አባል ብቻ አይደለችም።የትርምሱም አካል ጭምር እንጂ።የአረብ-እስራኤሎች ጦርነት፥-ግጭት ዉጊያ-ግድያ የእጅ አዙር ቁርቁስ ሲወሳ ሶሪያ እንደ ዋና ተዋኝ የማትሳተፍበት፥ በዋና ተዋኝነት የማትጠቀስበት ታሪክ የለም።

በ1980ዎቹ (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በኢራን-የኢራቅ ጦርነት ገሐድ የወጣዉ የምዕራባዉያንና ለምዕራባዉያኑ ያደሩት አረቦች እና የኢራ እስላማዊ አብዮተኞች ሽኩቻ ዉዝግብ ሲንር ከቴሕራኖች የወገነችዉ ብቸኛይቱ አረባዊት ሐገር ሶሪያ የዉዝግቡ አካል ነበረች።

ሊባኖስ የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስደጋፊዎች፥ የአረቦች ታማኞች፥ የኢራን ደጋፊዎች ለሰወስትና ከዚያ በላይ ጎራ ለይተዉ ሲፋጁባት ሶሪያ ግንባር ቀደሟ ተፋላሚ ነበረች።ትንሺቷን ማራኪ አረባዊት ሐገር ከአለም ካርታ ከመጥፋት ያዳነችዉም ሶሪያ ናት።የዚያኑ ያክል በተለይ ከሁለት ሺሕ አራት ወዲሕ የደማስቆን ፍላጎትና ጥቅም የሚቃወሙ የሊባኖስ ፖለቲከኞችን በማፈራራትና በማስገደል ትወቀሳለች።

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን መዉረሩን በመቃዋሟ፥ የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ያሰማ የነበረዉ ዛቻና ፉከራ ሶሪያ ዳግማዊት ኢራቅ መሆንዋ አይቀርም የሚል ሥጋት እስከማጫር ደርሶ ነበር።ሶሪያ ዛሬም የቴል አቪቭ-ዋሽንግተን፥ የለንደን-ፓሪስ ቀንደኛ ጠላት፥የቤይሩት-ሪያድ ሐለኛ ተፎካካሪ የሆነችዉ የቴሕራን ጥብቅ ወዳጅ ነች።

በዚሕም ሰበብ ሕዝባዊዉን አመፅ ለየራሳቸዉ ጥቅም ማስከበሪያነት ለመጥለፍ የሚሻሙ የዉጪ ሐይላት የሉም ማለት ጅልነት ነዉ።ዊኪሊክስ የተሰኘዉ አምደ መረብ እንደዘገበዉ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ስዑዲ አረቢያና ሊባኖስ የፕሬዝዳት አሰድ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ያደራጃሉ፥ በገንዘብና በቁሳቁስም ይረዳሉ።ፕሬዝዳንቱ ባንፃሩ አገዛዛቸዉን የሚቃወመዉን ሕዝብ አመፅ ለመደፍለቅ አመፀኞቹን የዉጪ ሐይላት ፍላጎት የሚያፈፅሙ በማለት ያወግዙታል።

«በሶሪያ መንገዶች ያለዉ ሁኔታ ሰወስት ወገኖችን ያካተተ ነዉ።የመጀመሪያዎቹ መንግሥት ችግራቸዉን እንዲያቃልላቸዉና ፍላጎታቸዉን እንዲያሟላላቸዉ የሚጠይቁ ናቸዉ።የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ከመንግሥት ግዴታዎች አንዱ ነዉ።ይሕን ጥያቄና ፍላጎት ለማሟላት መንግሥትና አስተዳደሩ ባለዉ አቅም ችሎታ ሁሉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለበት።እነዚሕ ወገኖች ማድመጥና የርዳታ እጃችንን መዘርጋት አለብን።ሕግና ሥርዓት ማስከበር ማለት የነዚሕን ወገኖች ጥያቄ ለመዘንጋት መዋል የለበትም።እነዚሕን ወገኖች ከነዉጠኞች መለየት አለብን።ነዉጠኞቹ በቁጥር ጥቂት ናቸዉ።ችግሩን መንግሥት እንዲፈታለት የሚጠይቀዉን የዋሕ ሕዝብ ግን ለአላማቸዉ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ።»

በፕሬዝዳት አሰድ እምነት ሰወስተኞቹ ሐይላት «የሶሪያ ጠላት» ያሏቸዉ የዉጪ ሐይላትና በዉጪዎቹ ሐይላት በቀጥታ የሚታዘዙት ወገኖች ናቸዉ።በሽር አል-አሰድን ጨምሮ በስልጣ ላይ ያለዉ አላዊይ ወይም አንሳሪይ የተሰኘዉ ወደ ሺዓ የሚያደላዉ የእስልምና ሐራጥቃ ተከታይ ነዉ።ሃያ-ሰወስት ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ሰባ አምስት ከመቶዉ ግን ሱኒ ሙስሊም ነዉ።ይሕ ምጣኔ ሐብታዊና ፖለቲካዊ ቅሬታዉን ማናሩ አያነጋግርም።

NO FLASH Syrien Assad Anhänger

አሰድና ደጋፊዎቻቸዉ

አሰድ በዛሬዉ ንግግራቸዉ የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄ ለመመለስ ከዚሕ በፊት ካሉት ብዙም የተለየ ነገር አላሉም።በሰወስት ከከፈሏቸዉ የሕዝባዊዉ አመፅ ተሳታፊዎች ጋር የሚወያይ ልዩ ኮሚቴ ወይም ባለሥልጣን መሰየማቸዉ ግን አስታዉቀዋል።እራሳቸዉ ፕሬዝዳቱ «የዉይይት ባለሥልጣን» ያሉት ተቋም አባል እንደሆኑም አስታዉቀዋል።

ባለሥልጣኑ ከፕሬዝዳንቱ ሌላ የሚያስተናብራቸዉን ሰዎችም ሆነ የሚያነጋግራቸዉ ተቃዋሚዎች ማንነትን ፕሬዝዳንቱ አልጠቀሱም።የዉይይቱን ይዘትም አልተናገሩም።የወደፊቱን ግን እንይ ብለዋል።ግድያዉ ሥለ መቆም-አለመቆሙ ግን ያሉት ያለም።አመፁም መቋረጡ አለየም።

ሊቢያ ሙታንዋን ትቆጥራለች።የመን-አደባይ የወጣና የሚወጣ ሕዝቧን ታሰላለች።ሞሮኮ በንጉስዋ አዋጅ ደጋፊ ተቃዋሚዎች እሁለት ተከፍላ ትወዛገባለች።ሶሪያም ሁለት ወር እንደለመደችዉ በአመፅ-ዉዝግብ፥ በግድያ ስደት ታዘግማለች።ቱኒስ-ካይሮን ማን ያሰልስ ይሆን?ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic