የአረብ ሊግ ጥምር ጦር ለማቋቋም አሰበ | ዓለም | DW | 29.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአረብ ሊግ ጥምር ጦር ለማቋቋም አሰበ

በመካከለኛዉ ምሥራቅ ዉጥረት እያየለ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የአረብ ሊግ የዓለም ዜና ጥምር ጦር ለመመሥረት እንደሚፈልግ ተገለፀ። የሚቋቋመዉ ጥምር ወታደራዊ ጦር ሃገራቱ አካባቢ እየጨመረ የመጣዉን ሥጋት እና ደህንነት ያስጠብቃል ተብሎአል።

በመካከለኛዉ ምሥራቅ ዉጥረት እያየለ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የአረብ ሊግ ጥምር ጦር ለመመሥረት እንደሚፈልግ ተገለፀ። በየመን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር በግብጽ ሻርማልሼክ ጉባኤ ያካሄዱት የአረብ ሊግ አባል ሀገራት የመንግሥታት ተጠሪዎች በጉባኤአቸዉ መጨረሻ ባሳለፉት ዉሳኔ የሚቋቋመዉ ጥምር ወታደራዊ ጦር ሃገራቱ አካባቢ እየጨመረ የመጣዉን ሥጋት እና ደህንነት ያስጠብቃል። እንደ ግብፅ ባለሥልጣናት የሚቋቋመዉ ጥምር ጦር ወደ 40 ሺ ወታደሮች ሲኖሩት በዉግያ አዉሮፕላኖች እና መርከቦችም ድጋፍን ያገኛል። ይመሰረታል ሥለተባለዉ የሃገራቱ ጥምር ጦር ዉሳኔ በሚቀጥለዉ ወር በቀጣይ በጋራ እንደሚመከርበት ተመልክቷል።

በሌላ በኩል በሳዉዲ ዓረብያ የሚመራዉና በየመን የሁቲ አማፅያንን በአየር የሚደበድበዉ ጥምር ኃይል የመን ሰንዓ የሚገኘዉን ዓለም አቀፍ የአየር ጣቢያ መደብደቡ ዛሬ ተገለፀ። በዚህ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸዉም ተያይዞ ተጠቅሷል። ሰንዓ የሚገኘዉ የአዉሮፕላን ጣቢያ ግልጋሎት እንደማይሰጥም ተመልክቷል። የመን ዉስጥ የሚንቀሳቀሱትን የሁቲ አማጽያን በአየር የሚደበድበዉ የአረቡ ጥምር ኃይል በሰንዓ በርካታ አማጽያን የሚገኙበት ቦታ ላይ ጥቃት አድርሶ 15 ሰዎች መገደላቸዉን የየመን ወታደራዊ ኃይላት ዛሬ አስታዉቋል። በየመን የሚገኝ ወታደራዊ ሆስቲታል አንድ ሃኪም እንደገለፀዉ ደግሞ በጥቃቱ የተገደሉት 18 ሰዎች ናቸዉ። በሌላ በኩል የመንግሥታቱ ድርጅት በየመን የሚገኙን ሰራተኞቹን ማዉጣቱን መቀጠሉ ተመልክቷል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ