የአረብ ሊግ የሶርያ መንግስትን ተጠያቂ አደረገ | ዓለም | DW | 27.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአረብ ሊግ የሶርያ መንግስትን ተጠያቂ አደረገ

ባለፈዉ ሳምንት ደማስቆ ዉስጥ ደርሷል ለተባለዉ የአደገኛ ኬሚካል መሳሪያ ጥቃት የአረብ ሊግ የሶርያ መንግስትን ተጠያቂ አደረገ። በመቶዎች የተገመቱ ሰዎችን ሕይወት ያሳለፈዉ የኬሚካል መሳሪያ ጥቃት ተጠያቂዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ድርጅቱ ጠይቋል።

ሊጉ ዛሬ ባካሄደዉ አስቸኳይ ስብሰባም የተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት አባላት ልዩነታቸዉን አስወግደዉ ይህን ወንጀል በፈጸሙ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ዉሳኔ እንዲያሳልፉም ጥሪ አስተላልፏል። በተጨማሪም በቀጣዩ ሳምንት በሚኒስትሮች ደረጃ ስብሰባ በማካሄድም የሶርያን ሁኔታ መከታተሉን እንደሚቀጥልም አመልክቷል። ስዑድ አረቢያ በበኩሏ ባለፈዉ ሳምንት ተፈጽሟል ለተባለዉ የኬሚካል መሳሪያ ጥቃት ሶርያ መንግስት ላይ ጠንካራና የማያወላዉል ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቃለች። አገዛዙ የአረብ ማንነቱን አጥቷል ያሉት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ሳዑድ አልፋይሰል በሰዎች ላይ የሚፈጸመዉን አሳዛኝ ድርጊት ለማስቆም ቆራጥ ርምጃ ያስፈልጋል ማለታቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የሶርያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመከላከል ያላትን ሁሉ ስልት ስራ ላይ ለማዋል መዘጋጀቷን አስታወቁ።

Syrien Arabische Liga 27.08.2013

የአረብ ሊግ ጉባኤ

አሶሲየትድ ፕረስ እንደዘገበዉ ዋሊድ አል-ሞአለም ዋሽንግተን የሶርያ መንግስት መርዛማ ንጥረ ነገር ለእርስ በርስ ጦርነቱ ሳይጠቀም አይቀርም ማለቱ ሃሰት ነዉ ሲሉ አስተባብለዋል። አያይዘዉም ይህን ክስ የደማስቆ መንግስት ላይ የሚሰነዝሩ ኃይሎች ተጨባጭ መረጃ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል። ቀደም ሲልም የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ደማስቆ ዉስጥ ሲቪሎችን ለማጥቃት በርከት ያለ መርዘኛ ጋዝ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያረጋግጥ የማይካድ መረጃ መገኘቱን እንዲህ ጠቁመዋል።
«ባለፈዉ ምሽት ከመላዉ ዓለም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋ ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ከተነጋገርኩ በኋላ ቪዲዮዉን ተመልክቻለሁ። ቪዲዮዉን ማንም ሰዉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሊያየዉ ይችላል። ደግሜ ተመለከትኩ። የአንድ መላ ቤተሰብ ደም እንዲሁም ቁስል የሌለበት አስከሬን። መርማሪዎች ስለሁኔታዉ ተጨማሪ መረጃዎች ከስፍራዉ እየሰበሰቡ ባሉበት ሁኔታ ለማስረገጥ የምፈልገዉ በህሊናችን ተመርተንና ሊሆን የሚችለዉን በመገመት ሶርያ ዉስጥ ምን እንደተደረገ በእዉነታ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ መያዝ እንደምንችል ነዉ።»

Syrien syrischer Außenminister 27.08.2013

የሶርያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ሙአለምሁለት የመንግስታቱ ድርጅት መርማሪ ቡድኖች ትናንት ወደተባለዉ ስፍራ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል። ሆኖም አንዱ በአልሞ ተኳሾች ጥይት ወደመጣበት እንዲመለስ መገደዱ ተገልጿል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊሙን ቡድኑ አቤቱታዉን ለደማስቆ መንግስት እንዲያቀርብ የጠየቁ ሲሆን ለደህነቱም ዋስትና እንዲሰጠዉ ሶርያን አሳስበዋል። ጆን ኬሪ ጥቃቱን «እብደት የተጠናወተዉ ስነምግባር» በማለት የአሳድ መንግስት መርማሪዎች ወደአካባቢዉ እንዳይቀርቡ ያግዳል ሲሉ ተችተዋል። የሶርያ መንግስትና ተቃዋሚዎቹ አማጽያን አንዳቸዉ ሌላቸዉን አደገኛ ኬሚካል በመጠቀም ሲቪሎች ላይ ጉዳት በማድረስ ይወነጃጀላሉ።

ሶርያ ዉስጥ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን በተመለከተ ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ሊወስድ ስላቀደዉ የኃይል ርምጃ ነጋሽ መሐመድ አበበ ፈለቀን ከዋሽንግተን ዲሲ አነጋግሯል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic