የአሥመራ ደስታ፤ፌስታ ምክንያት እና ዘላቂነት | ኢትዮጵያ | DW | 09.07.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአሥመራ ደስታ፤ፌስታ ምክንያት እና ዘላቂነት

ቃል ተገብቶ ቃል ሲታጠፍበት፤ ሰላም ተሰብኮ ጦርነት ሲለኮስበት ለኖረዉ ሕዝብ ግን አዲሱ ቃል፤ ተስፋ፤ ፌስታ ፈንጠዝያ እንደ 1952ቱ  ወይም እንደ 1985ቱ ባጭር እንዳይቀጭ ዶክተር ዳንኤል እንደሚሉት ሕጋዊ መሠረት፤ ዴሞክራሲያዊ መደላድል ሊበጅለት ይገባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:41
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:41 ደቂቃ

የ1944ቱ ወይም የ1985ቱ ዓይነት እንዳይሆን

አሥመራ እንደገና አጌጠች፤ ዘፈነች፤ ጨፈረች፤ ተደሰተች። የአዲስ አበባ እንግዶችዋን በደስታ፤ ፌስታ መቀበል በርግጥ አዲሷ አይደለም። ኤርትራ ከአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች እና የበላይ ጠባቂዎች አገዛዝ ተላቅቃ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን ስትጣመር አስመራ ጨፍራ ነበር።1944። ደስታ ፌስታዉ 6 ዓመት ሳይሞላዉ የኤርትራ በረሐ ከጦርነት መማገዱ ነዉ-ዚቁ። ከሰላሳ-ሰባት ዓመት በኋላ በ1985 ያዲስ ሐገር አዲስ ርዕሠ-ከተማነትን አክሊል ደፍታ የአዲስ አበባ አዳዲስ እንግዶችዋን ለመቀበል አሥመራ እንደገና ፈነደቀች። ከአምስት ዓመት በኋላ የጠብ፤ ጥላቻ፤ የዉጊያ ጦርነት መሰለቂያ፤ የመርዶ ሙሾ ማንጎራጎሪያ መሆንዋ እንጂ ሰቀቀኑ። ትናንትም ጨፈረች። ከእስከ ትናንቱ ይለይ ይሆን? ወይስ--።

የሚያዚያ 1985 ኤርትራ ዉስጥ የተደረገዉን ሕዝበ-ዉሳኔ ከአስመራ እንዘግብ የነብርን ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ ከብዙ የኤርትራ ባለሥልጣናትን የማነጋገር  እጋጣሚ ነበረን። ከብዙዎቹ አንዱ አንድ ቀን እንዲሕ ማለታቸዉን አስታዉሳለሁ። «ኢሳያስ ከልቡ ሲስቅ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ አየሁት»

ባለስልጣኑ «ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ» ያሉት ሕዝበ ዉሳኔዉ የተጠናቀቀበት ዕለት ነበር።ሚያዚያ 25 1993 እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር።የመጀመሪያዉ፤ ባለሥልጣኑ እንዳሉት፤ ኢሳያስ የሚመሩት ሸማቂ ቡድን ምፅዋን የተቆጣጠረበት ዕለት ነበር።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሁለተኛ ጊዜ ከልብ ሳቁ ከተባለበት ዕለት እስከ ትናንት ድረስ በተቆጠረዉ 25 ዓመት ብዙ ጊዜ ስቀዉ ብዙዎችን አስቀዉ ይሆናል።ትናንት የጠቅላይ ሚንስንር ዐብይ አሕመድን ንግግር ሲሰሙ ግን አልሳቁም።ተንከተከቱ እንጂ።

                                  

«ክቡር የሐገረ ኤርትራ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ።በአሥመራ (አጠራር ደግሞ) የአፌይ ልጅ---»

አቶ ኢሳያስም አሳቁ፤ አስጨበጨቡም።«ይሕን የዶክተር አብይን ጉዞ (ሕዝቡ እስኪዘጋጅ ድረስ) ያዘገየነዉ ሆን ብለን ነዉ።ከሕዝቡ ስሜት መረዳት ትችላላችሁ።እኔ መናገር አያስፈልገኝም።»

ኤርትራዊዉ የሕግ ባለሙያ እና የሠብአዊ መብት አቀንቃኝ ዶክተር ዳንኤል ረዘነ ትናንት አስመራ የታየዉን ዉይይት-ንግግር፤ ፌስታ፤ፌንጠዚያ፤ ሳቅ ፈገግታን ለሰላም ፈላጊ ሁሉ አስደሳች ይሉታል።የዚያኑ ያክል ከዚሕ ቀደም የታዩት አይነት እንዳሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ባይ ናቸዉ።በ1985 አስመራ  ከነበርን ኢትዮጵያዉን ጋዜጠኞች አንዱ አንጋፋዉ የኢትዮ-ሚዲያ አምደ-መረብ ባለቤት  አብረሐ በላይ የያኔዉ የኤርትራ ባለሥልጣን ስለኢሳያስ የነገሩንን ማስታወስ አለማስታወሱን አላዉቅም።አልጠየቅሁትምም።የያኔዉን የአሥመራ ደስታ-ፌስታን ግን በአካል፤ የትናንቱን በቴሌቪዥን ተከታትሏል።

                                     

አብረሐ እንደሚያስታዉሰዉ ያኔ አስመራ ስትቦርቅ፤ አዲስ አበባ ከገዢዎችዋ በስተቀር አብዛኛ ነዋሪዋ ከደስታ ይልቅ ሐዘን፤ ከተስፋ ይልቅ ሥጋት፤ ከሳቅ ይልቅ ሰቀቀን ተጫጭኖት ነበር።

                                      

እንዲያዉም ያኔ ከአስመራ የምዘግበዉ ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች (የኤርትራን ጉዳይ ምስኪኖቹ ጋዜጠኞች የወሰን ይመስል)  ከአዲስ አበባ ከሚደርሱን ምስጋና፤ምርቃት፤ትችት ዉግዘቶች መሐል «የዛምቢያ እግር ኳስ ቡድን ዕጣ ይግጠማችሁ» የሚል እርግማንም ነበረበት።

እርግማኑ በርግጥት አልያዘም።ለያኔዉ የኢትዮጵያ የሽግግር ፕሬዝደንት መለስ ዜናዊ አቀባበል የነበረዉ ደስታ-ፌስታም ዳር አልዘለቀም። የአዲስ አበባ እና የአሥመራ መሪዎች ቃል-ተስፋም በአምስት አመቱ በነነ።ፍቅር፤ ወዳጅነቱ፤ የመተባበር ጥሪ፤ ስብከቱ፤ የመሪዎቹ የልማት፤ዕደገት፤ የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ልዕልና ሰበካ የጦርነት ትቢያዉን ያላራገፈዉን ሕዝብ ከሌላ ጦርነት ከመዘፈቅ አለማዳኑ ነዉ ቁጭቱ።

ጦርነቱ ጋዜጠኛ አብረሐ በላይ እንደሚለዉ ለሩቁም፤ለቅርቡም ታዛቢ ዱብዕዳ፤ ለሁለቱም ሐገራት ሕዝብ አስደንጋጭ ነበር።ጦርነቱ በርግጥ አስደንጋጭ ነበር።

ከ80 ሺሕ እስከ መቶ ሺሕ የሚገመት ወጣት ያለቀበት፤በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የተፈናቀለበት።በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት የወደመበት።የልማት ዕደገት፤ የዴሞክራሲ-ፍትሕ ተስፋ የተጨናጎለብት።መዘዙ ለዛሬዉም ትዉልድ የተረፈ ጥፋት ነዉ።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግንኙነት በተመለከተ «ከሐገር በስተጀርባ» የሚል ርዕስ መፅሐፍ ያሳተመዉ የፖለቲካ ተንታኝ አስራት አብራሐ ዘግናኙ ጦርነት የሕወሐት ድብቅ «ሴራ» ዉጤት ነዉ።ጋዜጠኛ አብረሐ በላይም ተመሳሳይ አስተያየት አለዉ።ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትጣመር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ

የወሰነዉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1952 ነበር።ዉሳኔዉ አዲስ አበባ እና አስመራን ባስፈነደቀ በስድስተኛ ዓመቱ ኤርትራን ነፃ ለማዉጣት የሚዋጋዉ የኤርትራ ነፃነት ግንባር (ELF) መመስረቱ ታወጀ።

አሁን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች በ20 ዓመት ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥለ ሠላም መምከር፤ መወሰናቸዉ፤ ዶክተር ዳንኤል ረዘነ እንዳሉት ለሰላም ወዳዶች በሙሉ አስደሳች ነዉ።ሁለቱ መሪዎች የሰበኩት ፍቅር፤ በፍቅር ድልድይ ተተካ ያሉት የልዩነት ግንብ፤ ድንበር የለም ያሉት ቃል በርግጥ ተስፋ ሰጪ ነዉ።ቃል ተገብቶ ቃል ሲታጠፍበት፤ ሰላም ተሰብኮ ጦርነት ሲለኮስበት ለኖረዉ ሕዝብ ግን አዲሱ ቃል፤ ተስፋ፤ ፌስታ ፈንጠዝያ እንደ 1952ቱ  ወይም እንደ 1985ቱ ባጭር እንዳይቀጭ ዶክተር ዳንኤል እንደሚሉት ሕጋዊ መሠረት፤ ዴሞክራሲያዊ መደላድል ሊበጅለት ይገባል።

                             

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመሩት የኢሕአዲግ ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራን የሰላም ዉል እና የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትን ዉሳኔ ኢትዮጵያ ገቢር እንደምታደርግ ካስታወቀች ወዲሕ የሁለቱ መንግሥታት የወሰዷቸዉን እርምጃዎች በርካታ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በደስታ ተቀብለዉታል።

ሁለቱ ሐገራት ትናንት በተፈራረሙት ዉል መሠረት

አሥመሮች «ጤና ይስጥልኝ»ን፤ አዲስ አበቦች «መርሐባን» በስልክ ይለዋወጣሉ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሥመራን ከ114 መድረሻዎቹ ጋር አገናኛለሁ እያለ ነዉ።የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነም ይመሰረታል።

ደራሲ እና የፖለቲካ ተንታኝ አስራት አብረሐም ግን ልክ እንደ ኤርትራዊዉ የሕግ አዋቂ ሁሉ የአዲሱ ግኙነት ግብ በግልፅ መታወቅ አለበት ባይ ነዉ።

                                        

አንጋፋዉ ጋዜጠኛ አብረሐ በላይም ዶክተር አብይ አሕመድ ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማዉረድ የሚያደርጉት ጥረትም ሆነ በሐገር ዉስጥ የጀመሩት የለዉጥ እርምጃ እንዳይደናቀፍ የሕወሐትን ተፅዕኖ ማስወገድ አለባቸዉ ባይ ነዉ።በተለይ ከትግራይ።አስራት አብረሐም እንደሚለዉም  የሕወሐት ባለሥልጣናት ለሥልጣናቸዉ ከሠጉ የኢትዮ-ኤርትራን ስምምነትም ሆነ ዶክተር ዓብይ የሚመሩትን የለዉጥ ኃይል እርምጃ «ይረብሻሉ።»

            

ኤርትራዊዉ የሕግ ባለሙያ እና የሰብአዊ መብት አቀንቃኝ ዶክተር ዳንኤል ረዘነ መኮንን ደግሞ የኤርትራዉ አገዛዝ ራሱ አዲሱን ተስፋ እንዳያጨናጉለዉ ይሰጋሉ።ስጋት፤ እንቅፋቱ በርግጥ አልጠፋም። መቀራረብ-ስምምነቱ፤ የለዉጥ እርምጃ፤ ቃል ተስፋዉም እንደቀጠለ ነዉ። ወዳቂ፤ ጣዩ ለማወቅ  ግን ያዉ ጊዜ ነዉ በያኙ። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች